የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ
የምስሉ መግለጫ,የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ

ከ 5 ሰአት በፊት

የግብጽ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እየገቡ መሆኑ መዘገቡን ተከትሎ የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር በአገራቸው የየትኛውም አገር መንግሥት ወታደሮች እንደሌሉ በመግለጽ አስተባበሉ።

የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ ማክሰኞ ጳጉሜ 5/2016 ዓ.ም. ሞቃዲሾ ውስጥ ባደረጉት ንግግር፤ የትኛውም አገር ወደ ሶማሊያ ወደታሮቹን እያስገባ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ ሶማሊያ እና ግብጽ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ግብጽ ወታደሮቿን ሶማሊያ ውስጥ እንደምታሰማራ በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል።

ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ባለው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ለዓመታት ውዝግብ ውስጥ የቆየችው ግብጽ፣ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ወታደሮቿን በሶማሊያ ልታሰማራ መሆኑ ከተነገረ በኋላ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ውጥረት ተባብሷል።

ከሳምንት በፊት የጦር መኮንኖችን እና ወታደራዊ አቅርቦቶችን የጫኑ ሁለት የግብጽ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ ማረፋቸው በስፋት የተዘገበ ሲሆን፣ ይህም ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከሶማሊያውን ጭምር ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ሶማሊያ የውጭ ኃይሎችን ወደ ግዛቷ እንዲገቡ መፍቀዷ የአካበቢውን ሰላም እንደሚያናጋ በመግለጽ እርምጃውን ኢትዮጵያ በይፋ ተቃውማለች።

በተጨማሪም የሶማሊያ የተለያዩ ግዛቶች ባለሥልጣናት እና የፌደራል መንግሥቱ ፓርላማ አባላትም መንግሥት የግብጽ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እንዲገቡ መፍቀዱን በይፋ ተቃውሞው ከፍተኛ ውዝግብ አስከትሏል።

የግብጽ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ መግባት ከተነገረ እና በአገሪቱ ውስጥ እና ከውጪ ተቃውሞ መሰማት ከመጀመረ ከሳምንታት በኋላ የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ “የትኛውም አገር ወደ ሶማሊያ ወታደሮቹን እያስገባ አይደለም” በማለት አጥብቀው አስተባብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት “ወታደሮቹን ወደ ሶማሊያ የሚያመጣ መንግሥት የለም፤ የጠየቀንም መንግሥት የለም” በማለት ነገር ግን “ነጻ አገር እንደመሆናችን [ሶማሊያ] የፈለግነውን ለማድረግ መብቱ አለን” ብለዋል።

ጨምረውም “አረብ አገራትን እንዲረዱን ብንጠይቅ እና ጥያቄያችንን ቢቀበሉት፤ ይህ ማለት ሌላ አገርን ለማጥቃት ነው ማለት አይደለም” በማለት ሶማሊያም ሆነች ሌላ አገር ወታደሮቹን በአገሪቱ ውስጥ ለማስፈር ጥያቄ አለማቅረባቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት ተከትሎ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ሲካሄድ የከረመ ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረትን በማስከተል እስካሁን ድረስ ዘልቋል።

ከ15 ዓመታት በላይ ወታደሮቿን በሶማሊያ አሰማርታ የአገሪቱን መንግሥት ስትደግፍ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ ከግብጽ ጋር የደረሰቸውን ወታደራዊ ስምምነት ተከትሎ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ልታስገባ ነው መባሉ አስቆጥቷታል።

ነገር ግን ሶማሊያ ወታደራዊ ድጋፍን የምትፈልገው ከአረብ አገራት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ ፈቃደኛ ከሆኑ ከሌሎች አገራት ጭምር መሆኑን የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል።

“ድጋፍ ሊያደርጉልን ከሚችሉ አገራት ሁሉ እንፈልጋለን፤ ከእነሱ [ኢትዮጵያ] ጋርም ብዙ ሥራዎችን ሠርተናል፤ አሁንም ድጋፍ የሚሰጡን ከሆነ ለመቀበል ዝግጁ ነን” ብለዋል ሐምዛ አብዲ ባሬ።

የግብጽ ወታደሮች ረጅም ድንበር በምትጋራት ሶማሊያ ውስጥ መስፈሩ በኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ ጉዳዩን አንስተው አገራቸው ለሚከሰት ማንኛው ነገር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ የተነገረለት እና ኃይል ማመንጨት የጀመረው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለመግባባት ምንጭ ሆኖ ከአስር ዓመታት በላይ ቆይቷል።

ግብጽ ኢትዮጵያ የምትሳትፍበት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ ወታደሮቿን ለማሰማራት ፍላጎት እንዳላት ገልጻ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነትን ከተፈራረመች በኋላ በቅርቡ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ወደ ሞቃዲሾ ልካላች።

ይህ ከሆነ ከጥቂት ሳምንታት በኋላም የሕዳሴ ግድብ ከተገነባበት የአባይ ወንዝ የምታገኘውን የውሃ ጥምቅ ለማስከበር እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ግብጽ ለተባበሩት መንግሥታት በጻፈችው ደብዳቤ የገለጸች ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ይህንን በመቀዋም ለድርጅቱ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ደብዳቤ ጽፋለች።

ግብጽ ወደ ሶማሊያ ሠራዊቷን ለማሰማራት የፈለገችው በሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን አልሻባብንን በመዋጋት ላይ ያለውን የሶማሊያን ጦር ለመደገፍ ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖን ለማሳደር እንደሆነ በአንዳንድ ወገኖች ሲገለጽ ቆይቷል።