ሚሳኤል ሲተኮስ የሚኣሳይ ምስል

ከ 4 ሰአት በፊት

ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያካሄደች ላለችው ጦርነት እንዳትጠቀም በአሜሪካ ተጥሎባት የነበረው የረጅም ርቀት የጦር መሣሪያ ገደብ እንደሚነሳ ፕሬዚደንት ባይደን ፍንጭ ሰጡ።

ገደቡ የሚነሳ ከሆነ በአሜሪካ ድጋፍ በተደረጉላት የጦር መሣሪያዎች ላይ የተጣለባት ገደብ እንዲላላላት በተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀረበችው ዩክሬን ፍላጎት ይሞላል።

ቀደም ብሎ የዩክሬን ባለሥልጣናት የሩሲያን መጠነ ሰፊ ወረራ ‘በታሰረ እጃቸው’ እንዲጋፈጡ መደረጋቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

ሩሲያ እስካሁን በጉዳዩ ላይ ያለችው ነገር ባይኖርም ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ቀደም ብለው እንዲህ ዓይነት እርምጃ ወደ ከፋ መዘዝ ሊመራ እንደሚችል ተናግረዋል።

የባይደን አስተያየት የተሰማው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፤ ኢራን አጭር ርቀት የባሊስቲክ ሚሳኤል ለሩሲያ ሰጥታለች ሲሉ ከከሰሱ በኋላ ነው።

ማክሰኞ ዕለት አሜሪካ ዩክሬን ረጅም ርቀት መሣሪያ እንዳትጠቀም የተጣለባት ገደብ ይነሳ እንደሆነ በጋዜጠኞች የተጠየቁት ባይደን፣ አስተዳደራቸው በጉዳዩ ላይ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ሩሲያ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከከፈተች ጀምሮ አሜሪካ መሣሪያ ለማቅረብም ሆነ ወደ ሩሲያ ዘልቆ በመግባት ኢላማዎችን ለመምታት የሚያስችሉ የጦር መሳሪያዎች አጠቃቀምን በተመለከተ ግጭቱን ያባብሳል በሚል ስጋት ገደብ ለመጣል ስታመነታ ቆይታለች።

ሆኖም በሩሲያ ድንበር አካባቢ ያሉ ዒላማዎችን ለመምታት የሚያስችሉ በተወሰኑ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎች አጠቃቀም ላይ ጥላው የነበረውን ገደብ አላልታለች።

የኪዬቭ ሌሎች አጋሮችም ረጅም ርቀት መሣሪያዎችን በሩሲያ ውስጥ መጠቀም የኔቶ አባል አገራትን ወደ ጦርነት ሊያስገባ ወደሚችል የአፀፋ ጥቃት ሊያመራ ይችላል ወይም የኒዩክሌር ጦርነትን ሊቀሰቅስ ይችላል በሚል ስጋት እንዴት እና መቼ መጠቀም እንዳለባት ከሚገልጽ ገደብ ጋር ለዩክሬን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ መሣሪያ የሚቀርብላቸውን ፍጥነት የተቹ ሲሆን ከምዕራባውያኑ በቀረቡላቸው ሚሳኤሎች በሩሲያ ድንበር ውስጥ ዘልቀው በመግባት ኢላማዎችን ለመምታት እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

የሩሲያው መሪ ፑቲንም በአውሮፓውያኑ 2024 መጀመሪያ ላይ ዩክሬን ከምዕራባውያኑ ድጋፍ በተደረገላት ሚሳኤሎች ጥቃት ከፈፀመች ሰፊ ጦርነት ሊቀሰቅስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ፕሬዚደንት ፑቲን ጨምረውም በሩሲያ ግዛት ውስጥ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ምንም እንኳን የዩክሬን ኃይሎች ጥቃቱን ቢፈፅሙትም ኃላፊነቱን የሚወስዱት ግን ምዕራባውያን የጦር መሣሪያ አቅራቢዎች ናቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል ማክሰኞ ዕለት አሜሪካ ፣ ዩናይትድ ኪንግደም ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ እንዲውል ለሩሲያ የባልስቲክ ሚሳኤሎች በማቅረቧ በኢራን ላይ አዲስ ማዕቀብ ጥለዋል።

እርምጃው የኢራን ብሔራዊ አየር መንገድ ወደ ዩኬ እና አውሮፓ እንዳይበር እንዲሁም ለሩሲያ የጦር ድጋፍ እንዲደረግ ያስተባብራሉ የተባሉ በርካታ ኢራናውያን ሃብት እና ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ እንዲሁም የጉዞ እገዳን ያካትታል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብለንከን ለንደንን በጎበኙበት ወቅት ሩሲያውያን አጭር ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ለመጠቀም በኢራን ኃይሎች ሲሰለጥኑ ቆይተዋል ያሉ ሲሆን እነዚህ ወታደሮችም በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሊሰማሩ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

ሚሳኤሎቹ ከሩሲያ ድንበር አቅራቢያ ያሉ የዩክሬን ከተሞችን አሊያም በዩክሬን ግዛት ዘልቆ በመግባት ኢላማዎችን ለመምታት የሩሲያን አቅም ያጠናክራሉ ተብሏል።

ኢራን በበኩሏ ለሩሲያ እነዚህን የጦር መሣሪያዎች አቅርባለች መባሉን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።