ከፍተኛ ውጤት ያመጡት የቀላሚኖዎቹ ዮናስ እና ሄለን

ከ 5 ሰአት በፊት

ጳጉሜ 4/2016 ለ12ኛ ተማሪዎች ልዩ ቀን ነበረች። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ውጤታቸውን ለማየት እስከ እኩለ ለሊት ስልክ እና ኮምፒውተራቸው ላይ ተጥደው ነው ያመሹት።

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ዶ/ር) የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የፈተና ውጤት እንደሚለቀቅ ይፋ አደረጉ ።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ፈተና ለመቀመጥ ከተመዘገቡ 701 ሺህ 749 ተማሪዎች ከ684 ሺህ በላይ የሚሆኑት እንደተፈተኑ አሳወቁ።

አክለው በዘንድሮው ፈተና ከፍተኛው ውጤት 675 መሆኑን ተናግረው ይህ ተማሪ መቀለ የሚገኘው የቀላሚኖ ትምህርት ቤት ተማሪ መሆኑን ገለፁ።

ዮናስ ንጉሰ እና ሄለን በርኸ የመቀለው ቀላሚኖ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው።

የዮናስ ውጤት 675፤ የሄለን ደግሞ 662 ነው።

ዮናስ ንጉሰ

ዮናስ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ አንደኛ ነበር የሚወጣው። ዘጠነኛ ክፍል ግን ሁለተኛ ወጣ።

“በጣም የምወዳቸው የትምህርት ዓይነቶች ሒሳብ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ናቸው” ይላል። እንግሊዝኛ ቋንቋ 95፤ ሒሳብ ደግሞ 100 ነው ያመጣው። ከመቶ ማለት ነው።

ለዓመታት [በጦርነቱ ምክንያት] ከትምህርት ርቆ መቆየት በጣም ከባድ እንደነበር አይክድም።

“በጦርነቱ ወቅት ትምህርት አልነበረም። መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች አልነበሩም። ጊዜው በጣም ከባድ ነበር” ይላል።

በወቅቱ ያዘወትር የነበረው ልብ-ወለድ መፃሕፍትን ማንበብ ነው። ለምን? “ካለው መጥፎ ሁኔታ ለመራቅ እና ለአእምሮዬ ሰላም ለመስጠት ነበር” ሲል ምክንያቱን ይገልፃል።

ከባዱን ጊዜ በፅናት ለማለፍ የቤተሰቦቹ አስተዋፅዖ ቀላል እንዳልነበረ አይዘነጋም። ቀላሚኖ ትምህርት ቤት ግቢው ደስ የሚል እንደሆነ፤ ለጥናት እንደሚመች ይናገራል።

ውጤቱን ‘ኦንላይን’ ያየው ጳጉሜ 4/2016 እኩለ ለሊት ገደማ ነው። መብራት አልነበረም። ስልኩ ግን ‘ባትሪ’ ነበራት። ውጤቱን ተመለከተ። መግለፅ የሚከብድ ደስታ።

“ልክ ውጤቱን እንዳየሁት በጣም ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ። ለመግለፅ የሚከብድ ደስታ ነው የተሰማኝ። ውጤቱን ሳይ እናቴም አባቴም አብረውኝ ነበሩ። እነሱም በጣም ነው ደስ ያላቸው።”

የትምህርት ሚኒስትሩ የፈተናው ውጤት ይፋ እንደሚሆን ባሳወቁበት መግለጫቸው ከፍተኛው ውጤት ያመጣው ተማሪ የቀላሚኖ እንደሆነ ጠቁመዋል። ቢሆንም ዮናስ ውስጥ ቅንጣት ጥርጣሬ ነበረች።

“ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛው ውጤት 675 ነው ሲል ‘ይሄ ውጤት የኔ ሊሆን ይችላል’ የሚል ጥርጣሬ ነበረኝ” ይላል በፈገግታ። “የኔን ውጤት ሳየው 675 ነው፤ ይሄኔ ነው ከአገሪቱ ከፍተኛው እንደሆነ የገባኝ።”

ፈተናው ቀሎት እንደሁ ቢቢሲ ጠየቀው።

“የፈተናው ክብደት እንደ ትምህርት ዓይነቱ ይለያያል። አንዳንድ ‘ሰብጀክቶች’ በጣም ቀላል ነበሩ። አንዳንዶቹ ‘ሰብጀክቶች’ ደግሞ ከበድ ይሉ ነበር።”

ዮናስ የጉብዝናው ምስጢር ጥረት እንደሆነ ደጋግሞ ያወሳል። ነገር ግን ጥረት ብቻውን ዋጋ የለውም ይላል።

“ሰዎች ከጣሩ ከፍተኛ ውጤት ያመጣሉ ብዬ አምናለሁ። ጥረት ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም ሊኖራቸው ይገባል። ሁለቱን ማጣመር ከቻሉ በእርግጠኝነት ውጤት ያመጣሉ።”

እስካሁን ከትምህርት ሚኒስቴር ስለሽልማት የሰማው ነገር የለም። “የሚድል ኢንካም [መካከለኛ ገቢ ያላቸው] ቤተሰብ ልጅ ነኝ” የሚለው ዮናስ ነጋዴ አባቱ እና የቤት እመቤት እናቱ ሊሸልሙት ቃል እንደገቡለት ነገሮናል።

በርካቶች ደውለው እንኳን አደረሰህ ሊሉት ሲደውሉ ነበር። የቀድሞው ትምህርት ቤቱ እንዲሁም የቀላሚኖ ርዕሰ-መምህራን፤ ጓደኞቹ፤ ዘመድ አዝማድ እና ጎረቤት. . . እንዲሁም ቢቢሲ ስልኩን እረፍት ነስተዋት ነው የዋሉት።

“ሁሉም አስተማሪዎቼ የራሳቸው የሆነ አስተዋፅዖ አድርገውልኛል። መርጬ ማመስገን ይከብደኛል።”

ወደፊት የኮምፒውተር ሳይንስ መማር ይፈልጋል። ማኅበረሰብ የሚበለፅገው በቴክኖሎጂ ነው ብሎ ያምናል። ከአገር ቤት መቀለ፣ አሊያም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምርጫዎቹ ናቸው።

“ወደ ውጭ ሄዶ የመማር ዕድሉ ከተገኘም እሞክራለሁ” ይላል።

ሄለን በርኸ

የጉብዝናዋ ምስጢር ምንድነው? “[እኔ እንጃ] ተሰጥዖ መሰለኝ” ትላለች ሄለን። ነገር ግን ሌላም ምስጢር አላት።

“ተማሪ ከሆንኩ አይቀር ለምን ጎበዝ አልሆንም ብዬ አቅሜን ስለምፈትን ነው። እኔ እንደማስበው አንድ ነገር ላይ ያለህን መቶ በመቶ አቅም ተጠቅመህ ውጤቱ ጥሩ ካልሆነ ጥሩ አይደለህም ማለት ነው። ብዙዎች ሙሉ አቅማቸውን አይፈትሹትም [መሰለኝ]።”

ከአንደኛ ክፍል ጀምራ ተሸላሚ ተማሪ ናት። “ከልቤ ነው የምማረው። አጥንቼ ሲገባኝ ደስ ይለኛል” ትላለች።

ፊዚክስ ትወዳለች። ብዙ ጊዜዋን ለፊዚክስ ትምህርት ጥናት እንደምታውል ትናገራለች።

‘ክላስ’ ውስጥ በሚሰጡት ፈተናዎች ላይ የምታመጣው ውጤት አያረካትም።

“ቀላል አይደለም። ማትሪክ ፈተና ላይ እንዳይከብደኝ ብዬ ብዙ ጊዜየን የማጠፋው ፊዚክስ በማጥናት ነበር። በስተመጨረሻ ውጤቱ መልካም ሆነ።”

አንደኛ ስትወጣ ቤተሰቦቿ ይሸልሟታል። ብዙውን ጊዜ ሽልማቷ መጽሐፍ ነው። በተለይ ደግሞ ለሚመጣው ‘ግሬድ’ [ክፍል] የሚሆን መጽሐፍ ይገዛላታል።

“በሽልማት መልክ ‘አሳይመንት’ እየሰጡኝ ይሆናል። ግን እኔ እወደው ነበር። ምክንያቱም አንብቤ ስገባ ‘ክላስ’ ውስጥ ብዙ የሚከብደኝ ነገር አይኖርም። መጽሐፍ ብቻ አይደለም፤ ልብስምኮ’ ይጨመርልኛል።”

ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ጎበዝ እየተባለች፤ እየተሸለመች ማደጓ ለዚህ ውጤት እንዳበቃት ታስባለች። ነገር ግን በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንደተፈተነች አትክድም።

“ከጦርነቱ መትረፌ ለምክንያት ነው ብዬ አስባለሁ። በሕይወት ከተረፍኩ አይቀር ይሄን ዕድል መጠቀም አለብኝ ብዬ በደንብ ሳጠና ነበር። ፈተናው ምናልባት በሰላሙ ጊዜ ቢመጣ ኖሮ ይሄን ውጤት ባላመጣሁ ነበር። ያለፈው መከራ አበርትቶኛል ብዬ አምናለሁ።”

ሄለን በጦርነት ወቅት ታዘወትር የነበረው ልብ-ወለድ መጻሐፍትን ነው። “ማንበብን እንዳልረሳው” አድርገውኛል ትላለች።

“ትምህርት ነክ መጻሕፍትን እንዴት አድርጌ አነባለሁ? ምክንያቱም ሁኔታዎች አስጨናቂ ነበሩ። ከሕዝቡ ጋር አብረህ ነው የምትጨነቀው።”

ሄለን 662 አመጣለሁ ብላ ባታስብም ውጤቷ ከ650 በላይ ሊሆን እንደሚችል ትገምት ነበር።

በአሸንዳ ዋዜማ ውጤት ይነገራል ተብላ ቁጭ ብላ አደረች። ውጤቱ የውሀ ሽታ ሆነ። ውጤቱ ጳጉሜ 4 እንደሚነገር ሰማች። ይህን ለቤተቦቿ አልተናገረችም።

“ጠብቄ ውጤቱን አየሁት። እናት እና አባቴን እየሳቅኹኝ ስቀሰቅሳቸው ‘ምን ሆና ነው?’ ብለው ደንግጠው ነበር። ውጤቱን ሳሳያቸው በጣም ደስ አላቸው። በደስታ ብዛት ሳንተኛ ነው ያደርነው፤

“. . .ፈጣሪዬን፣ ተስፋ እንዳልቆርጥ አድርገው ያስተማሩኝን ወላጆቼን እንዲሁም ትምህርት ቤቶቼን ማመስገን እፈልጋለሁ።”

ዩኒቨርሲቲ ስትገባ ሜዲሲን ማጥናት ነው ፍላጎቷ። በተለይ ደግሞ ኒውሮሎጂ (የነርቭ ሥርዓት ጥናት) የማጥናት ዕቅድ አላት። ይህ ፍላጎቷ የመነጨው ገና ልጅ ሳለች ነው።

“ሕፃን እያለሁም ፍላጎት ነበረኝ። አንድ ‘ኒውሮሎጂስት’ ዘመድ አለን። ስለኒውሮሎጂ ብዙ ይነግረኝ ነበር። ሕክምናው በአቅራቢያችን አይገኝም፤ ብዙ ዶክተሮችም የሉንም። በዚህ የተቸገሩ ሰዎችን ስለማይ ይህንን ክፍተት መሙላት እፈልጋለሁ።”