ከግራ ወደ ቀኝ፡ ኩኩ፣ ዮሀና፣ ፍቅርአዲስ፣ እግቱ እና ቤቲ ጂ

ከ 5 ሰአት በፊት

ቢቢሲ አዲሱን ዓመት በማስመልከት ስድስት ድምጻውያንን ጋብዞ አምስት ከአውደ ዓመት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አቅርቧል።

ድምጻውያኑ የበዓል ዕለት ምን መመገብን ይወዳሉ? የትኞቹ መጻሕፍትስ እንዲነበቡ ይመክራሉ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎችን ሰንዝረናል።

ኩኩ ሰብስቤ

ኩኩ ሰብስቤ
የምስሉ መግለጫ,ኩኩ ሰብስቤ

ቢቢሲ፡ የ2016 ዓ. ም. ልዩ ትውስታዬ የምትይው ምንድን ነው?

ኩኩ፡ በ2016 ዓ. ም. አሜሪካ ለስድስት ወር ቆይቻለሁ። ለ16 ዓመት የኖርኩበት አገር ነውና እዛ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼን፣ ጓደኞቼን አዝናንቻለሁ። ሳን ፍራንሲስኮ፣ ሲያትል፣ ዲሲ እንዲሁም ካናዳ። በዛው ዓመታዊ የጤና ምርመራ አድርጌ፣ ከወዳጆቼ ጋር ገበያ አድርጌም ነበር። ሌላው፣ በየጊዜው ስሄድ እንደማደርገው ከኢትዮጵያ ቁልፍ መያዣዎች ይዤ ሄጄ ነበር። ሰዎች በ20 ዶላርም፣ በ100 ዶላርም ገዝተውኛል። ያንን ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ አምጥቼ ለችግረኞች መርጃ እንዲውል ሰጥቻለሁ። አዲስ አልበም በቅርቡ ስለማወጣ እዛ ሆኜ ብዙ ነገር አዘጋጅቻለሁ።

በበዓል ወቅት በጣም የምትወጂው ምግብ ምንድን ነው?

ኩኩ፡ክትፎና ዶሮ ወጥ እወዳለሁ። ዋና እነሱ ናቸው። የበግ ወጥም እወዳለሁ።

የምንጊዜም ምርጥ የምትያቸው 3 ዘፈኖች ወይም አልበሞች የትኞቹ ናቸው?

ኩኩ፡የውልሽ. . .ሙዚቃ እንደ ቀለም ነው። ቀለሞች ሁሉ ስናያቸው እንደምንወዳቸው፣ ብዙ የተለያዩ ዘፋኞችን እኔ በጣም ነው የምወዳቸው። ያለ ምክንያት በአንድ ወቅት ዝነኛ አልሆኑም እና ልክ እንደ ቀለም ለመምረጥ ያስቸግረኛል። ሙሉቀን መለሰ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ቴዲ አፍሮ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ አስቴር አወቀ፣ ጂጂ፣ ሐመልማል፣ ነጻነት. . . ስንቱን እዘረዝራለሁ? ቴዲ አፍሮ የሕዝብ ልጅ፣ መልዕክተኛ ስለሆነ እጅግ በጣም አደንቀዋለሁ። ከእኔ ዘፈኖች ምረጭ ብትይኝ፣ ‘ከልጆቻችሁ የቱን አብልጣችሁ ትወዳላችሁ?’ እንደማለት ነው። ቢሆንም ያነሳኝ ዘፈንና መታወቂያዬ ስለሆነ ‘ፍቅርህ በረታብኝ’ ን በጣም ነው የምወደው። ትዝታ አልበሞቼ ላይ ያሉ የትዝታ ቅኝቶቼንም እወዳለሁ።

መነበብ አለባቸው የምትያቸው 5 መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው?

ኩኩ፡‘ፍቅር እስከ መቃብር’፣ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው የጻፉት ‘አርሙኝ’- ድሮ ያነበብኩት አስተማሪና ደስ የሚል ታሪክ ያለው መጽሐፍ ነው፣ ሌላው የአቤ ጉበኛ ‘አልወለድም’ እና ከአሁኖች ደግሞ ‘እመጓ’ መነበብ ያለባቸው መጻሕፍት ናቸው እላለሁ።

የቀጣይ ዓመት ዕቅድሽ ምንድ ነው?

ኩኩ፡ በ2017 ዓ. ም. አልበሜ ይወጣል። እንደእኔ ሐሳብና ፍላጎት፣ በመስከረም መጨረሻ ወይም በጥቅምት እንደሚያልቅ ተስፋ አለኝ። 90 በመቶው አልቋል። ትንሽ የሚስተካከል ነገር ነው የቀረው።

አቢ ላቀው

አቢ ላቀው
የምስሉ መግለጫ,አቢ ላቀው

ቢቢሲ፡ የ2016 ዓ. ም. ልዩ ትውስታዬ የምትይው ምንድን ነው?

አቢ፡ እውነቱን ለመናገር አገር ቤት ባለው ሁኔታ የተነሳ በ2016 ዓ. ም. ጥሩ ትውስታ የለኝም። 2017 ዓ. ም. አገራችን በጣም የምትፈልገው ሰላም የሚመጣበት፣ ሰዎች ሰላምና ደኅንነታቸው የሚጠበቅበት እንዲሆን እፀልያለሁ።

በበዓል ወቅት በጣም የምትወጂው ምግብ ምንድን ነው?

አቢ፡ በበዓል የምንበላቸውን ባህላዊ ምግቦችን ሁሉ እወዳቸዋለሁ። ግን በዋናነት ዶሮ ወጥ። በአዲስ ዓመት አከባበር ከምንም በላይ ደስ የሚለኝ ግን የቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓትና ቤተሰብ ሲሰባሰብ ነው። ያው በዓሉ አብሮ ተሰባስቦ የመመገብ ስለሆነ።

የምንጊዜም ምርጥ የምትያቸው 3 ዘፈኖች ወይም አልበሞች የትኞቹ ናቸው?

አቢ፡ የአስቴር አወቀ፣ የጂጂ እና የሚካያ በሃይሉ

መነበብ አለባቸው የምትያቸው 5 መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው?

አቢ፡ ሦስት ልንገርሽ። አንደኛ መድሐፍ ቅዱስ፣ ከየትኛው በላይ ነው። ሁለተኛ የPaulo Coelho- ‘The Alchemist’፣ ልባችንን ማዳመጥን እና ሌላ ቦታ የምንፈልገው ነገር ደጃፋችን እንዳለ ያስተምረናል። ሦስተኛ የRobert Kiyosaki- ‘Rich Dad poor Dad’፣ ስለ ፋይናንስ አያያዝ ስለሚያስተምር ማንኛውም ንግድ መክፈት የፈለገ ነው ቢያነበው እላለሁ።

የቀጣይ ዓመት ዕቅድሽ ምንድ ነው?

አቢ፡ ከዓመት በፊት አንድ ፕሮጀክት ጀምሬያለሁ። የቀጣይ ዓመት ዕቅዴ ይሄን ፕሮጀክት ማጠናቀቅ ነው። አንደኛው የሙዚቃ ፕሮጀክቴ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ የራሴን ቢዝነስ መጀመሬ ነው።

ቤቲ ጂ

ቤቲ ጂ
የምስሉ መግለጫ,ቤቲ ጂ

ቢቢሲ፡ የ2016 ዓ. ም. ልዩ ትውስታዬ የምትይው ምንድን ነው?

ቤቲ ጂ፡ ዋናው ከፍታዬ ልጄን ማሳደግ ነበር። አልበሜንም እየሠራሁ ነው። ሁለተኛ ልጅም እየጠበቅኩ ነው። እነዚህ ናቸው ትልልቆቹ የምላቸው።

በበዓል ወቅት በጣም የምትወጂው ምግብ ምንድን ነው?

ቤቲ ጂ፡በበዓል ወቅት በጣም የምወደው ምግብ የእናቴ ዱለት ነው። ጉበት ተመርምሮ በግ አይታረድምና ብዙ ጊዜ በግ ከታረደ በኋላ የምጠይቀው ‘ጉበቱ ደኅና ነው ወይ?’ ብዬ ነው። ምክንያቱም የዱለት ወዳጅ ስለሆንኩና የእናቴ ዱለት በጣም ስለሚጣፍጠኝ።

የምንጊዜም ምርጥ ሙዚቃ የምትያቸው 3 ዘፈኖች ወይም አልበሞች የትኞቹ ናቸው?

ቤቲ ጂ፡በዓል ስለሆነ የጋሽ ጥላሁን ‘ክረምት አልፎ በጋ’. . . ልጅ ሆነን ጀምሮ የምንሰማውና በልጅነቴ በዓል ያሳለፍኩበትን የሚያስታውሰኝ ነው። በጣም የማይክል አድናቂ ነኝና ‘Man in the Mirror’ የሚለው ትልቅ ትርጉም ይሰጠኛል።በሕይወታችን ውስጥ ምንም ነገር ስንጠይቅ፣ ለውጥ ማምጣት ስናስብ ራሳችንን ማሰብ አለብን የሚል መልዕክት አለው። ሦስተኛው የብዙነሽ በቀለ ‘የሚያስለቅስ ፍቅር’ ነው። ልጅነቴን ያስታውሰኛል። እናቴ የምትወዳትም ዘፋኝ ስለሆነች የሷን ዘፈን እሞክር ነበር። ሦስት ብቻ ለመምረጥ ግን ከባድ ነው. . . እንደምንም ተጠብቤ ነው የነገርኩሽ።

መነበብ አለባቸው የምትያቸው 5 መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው?

ቤቲ ጂ፡የመጀመሪያው የM. M. Kay- ‘The Far Pavilions’ በሕንዳዊና በፈረንጅ መካከል ያለ የፍቅር ታሪክ ነው። በጣም ረዥም ነው። ግን በጣም ከምወዳቸው መጻሕፍት አንዱና ታሪኩን ውስጡ ገብቼ ያነበብኩት ነው። ሁለተኛ ‘ፍቅር አስከ መቃብር’፣ ስለ ኢትዮጵያ ምንነትና ማንነት፤ ስለእኛ ባህልና ሥነ ሥርዓት ማወቅ ከፈለግን. . . ብዙ ምስጢር ያለው መጽሐፍ ነው። ሌላው ‘Romeo and Juliet’ ነው። የፍቅር ታሪክ ነው፣ ግን መቸኮል ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል ያሳያል። ሌላኛው ‘Animal Farm’ ነው። አሁን ስለምንኖርበት ዓለምና ስለ ሰዎች አኗኗር ብዙ ትምህርት ይሰጠናል።

የቀጣይ ዓመት ዕቅድሽ ምንድ ነው?

ቤቲ ጂ፡ሁለተኛ ልጄን በሰላም ተገላግዬ፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሦስተኛ አልበሜ ይወጣል። ከዛ በፊት አንድ ነጠላ ዜማ እለቃለሁ ብዬ አስባለሁ። ወደ ፊልም ሙያ ውስጥም ለመግባት እየሞከርኩ ነው። ዘንድሮ በእኛ የክረምት ወቅት በአሜሪካ በነበረኝ ቆይታ የትወና ትምህርት ወስጄ ነበር። ከእኔ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ሆኖ ስላገኘሁት ወደ ፊልም ትወና የምገባበት ዓመት ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

እግቱ

እግቱ
የምስሉ መግለጫ,እግቱ

ቢቢሲ፡ የ2016 ዓ. ም. ልዩ ትውስታዬ የምትይው ምንድን ነው?

እግቱ፡ በዋልታ ቴሌቭዥን ጣቢያ ‘ደሞ አዲስ’ የተሰኘ የሙዚቃ አይዶል ውድድር አለ። እዛ ላይ በአሠልጣኝነት እና በዳኝነት ሠርቼ ነበር። በእኔ ሥር ከተመደበው ተወዳዳሪ ማቲያስ ደርብ ጋር ውድድሩን ማሸነፋችን ልዩ ትውስታዬ ነበር።

በበዓል ወቅት በጣም የምትወጂው ምግብ ምንድን ነው?

እግቱ፡በበዓል ወቅት ዶሮ ወጥ ምንጊዜም የምወደው የምግብ ምርጫዬ ነው።

የምንጊዜም ምርጥ ሙዚቃ የምትያቸው 3 ዘፈኖች ወይም አልበሞች የትኞቹ ናቸው?

እግቱ፡ይሄ ጥያቄ በጣም ከባድ መሆኑን ሳልገልጽ አላልፍም። ግን. . . የአስቴር አወቀ ‘Aster’s Ballads’ (2008)፣ የJohn Legend ‘Once Again’ (2006) እና የቴዎድሮስ ታደሰ ‘ዝምታ’ (1997)።

መነበብ አለባቸው የምትያቸው 5 መጻሕፍት/መታየት አለባቸው የምትያቸው ፊልሞች የትኞቹ ናቸው?

እግቱ፡መታየት አለባቸው የምላቸውን ፊልሞች ልንገርሽ፣ ‘Titanic’፣ ‘The Note Book’፣ ‘Meet Joe Black’፣ ‘It’s Complicated’፣ እና ‘The English Patient’

የቀጣይ ዓመት ዕቅድሽ ምንድ ነው?

እግቱ፡የቀጣይ አመት ዕቅዴ፣ ከፈጣሪ ጋር፣ እኔን በተወሰነ መንገድ ይገልጻል ወይም ከሕዝብ ጋር ያገናኘኛል የምለውን አልበም ማቅረብ ነው።

ዮሃና ሳህለ

ዮሃና ሳህለ
የምስሉ መግለጫ,ዮሃና ሳህለ

ቢቢሲ፡ የ2016 ዓ. ም. ልዩ ትውስታዬ የምትይው ምንድን ነው?

ዮሃና፡ አልበሜ የተለቀቀ ቀን ይመስለኛል። በጣም ረዥም ጊዜ የወሰደ ነበርና የተለቀቀ ቀን ትልቅ ሸክም እንደማራገፍ. . . እንደ መውለድም ነው የተሰማኝ። አልበሜ የተለቀቀ ቀን፣ ለኔ በጣም ደስ የሚል ቀን ነበር።

በበዓል ወቅት በጣም የምትወጂው ምግብ ምንድን ነው?

ዮሃና፡የእናቴን ዶሮ ወጥ። እኔ አትክልት ተመጋቢ (Vegetarian) ነኝ፣ ሥጋ አልበላም፣ ግን እንቁላሉንና የወጡን ቁሌት መብላት እወዳለሁ። እንደ እናቴ ዶሮ ወጥ የሚሠራ ያለ አይመስለኝም።

የምንጊዜም ምርጥ ሙዚቃ የምትያቸው 3 ዘፈኖች ወይም አልበሞች የትኞቹ ናቸው?

ዮሃና፡ብዙ የምወዳቸው አልበሞች ስላሉ በጣም የሚከብድ ጥያቄ ነው። አንደኛ የ Lauryn Hill- ‘The Miseducation of Lauryn Hill’፣ ሁለተኛ የMiles Davis- ‘Kind of Blue’ እና የጀጂ- ‘Illuminated Audio’ እና ‘Gold & Wax’

መነበብ አለባቸው የምትያቸው 5 መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው?

ዮሃና፡ይሄም ከባድ ነው፣ ግን አብረውኝ የቀሩ የምላቸውና መነበብ ያለባቸው የMaya Angelou- ‘I Know Why the Caged Bird Sings’፣ የToni Morrison- ‘The Bluest Eye’፣ የCharles Baudelaire- ‘Les Fleurs du mal’- ይሄን የግጥም ስብስብ በጣም ልጅ እያለሁ ነው ያነበብኩት. . . አምስተኛው የሕይወት ተፈራ- ‘Tower in the Sky’ ነው።

የቀጣይ ዓመት ዕቅድሽ ምንድ ነው?

ዮሃና፡እውነቱን ለመናገር፣ ማቀድን ገና እየተማርኩ ነው። ግን ለኔ ትልቁ ነገር ብዙ መፍጠር ነው። ለተወሰነ ጊዜ ሳልፈጥር ስለቆየሁ በቀጣዩ ዓመት ብዙ ፈጠራ መሥራት እፈልጋለሁ።

ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ

ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ
የምስሉ መግለጫ,ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ

ቢቢሲ፡የ2016 ዓ. ም. ልዩ ትውስታዬ የምትይው ምንድን ነው?

ፍቅርአዲስ፡ በ2016 ዓ. ም. እንዲህ የምለው ነገር የለኝም። አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ትዝታ የለኝም። እውነቱን ልንገርሽ፣ ጭንቀት ነው የማስታውሰው። የጎንደር ልጅ ነኝ። ስደውል ቤተሰብ ውስጥ ያለው ሰላም ማጣት ያስጨንቃል። እየተረበሽ ገንዘብ ብትሠሪም፣ ሥራ ላይ ብትሆኚም ደስታ የለውም።

በበዓል ወቅት በጣም የምትወጂው ምግብ ምንድን ነው?

ፍቅርአዲስ፡ዶሮ ወጥ እና ጥብስ ነው በጣም ደስ የሚለኝ።

የምንጊዜም ምርጥ የምትያቸው 3 ዘፈኖች ወይም አልበሞች የትኞቹ ናቸው?

ፍቅርአዲስ፡የአስቴር አወቀን ነዋ. . . ከሷ ምንም የምጠላው ዘፈን የለኝም። የአዲስ ዓመቱን ‘እዮሃ አበባዬ’ ብትጋብዢልኝ ደስ ይለኛል። አስቴርን በጣም ነው የምወዳት። ሁሌም ከሷ እማራለሁ። ቀና ናት። በዚሁ እንኳን አደረሰሽ በይልኝ። ከራሴ ሙዚቃዎች ልንገርሽ. . . ‘ልዑል አስወደደኝ’፣ ‘ምስክር’ እና ‘ዞማ’ን እወዳቸዋለሁ።

መነበብ አለባቸው የምትያቸው 5 መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው?

ፍቅርአዲስ፡ከማንበብ ይልቅ ሲነበብ ስሰማ ነው ደስ የሚለኝ። ቢነበቡ የምላቸው ‘አንድ ለእናቱ’ እና የፍቅረማርቆስ ደስታ መጻሕፍት ናቸው። አቤ ቁጭ ስንል አንብቦልኛል። አቤ ግጥሙን የጻፈው ‘ያሙ ያሙ’ የሚለው ዘፈኔ ‘አቻሜ’ ከሚለው መጽሐፍ ነው የተወሰደው። በትረካ ሰምቼ ከወደድኳቸው መካከል ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ ዋናው ነው።

የቀጣይ ዓመት ዕቅድሽ ምንድ ነው?

ፍቅርአዲስ፡ሁሉም ነገር ሰላም ሆኖ፣ በቀጣይ ዓመት የሠራሁትን ሲዲ ለማውጣት ዝግጀት ላይ ነኝ።