ትራምፕ እና ሃሪስ

ከ 3 ሰአት በፊት

ካማላ ሃሪስና ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ምሽት በፊላደልፊያ በተካሄደው የአሜሪካ ዕጩ ፕሬዝዳንቶች ክርክር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተዋል።

ሁለቱ ዕጩዎች ሲጨባበጡ የታዩ ቢሆንም ወዲያው ወደጦፈ ክርክር ገብተዋል።

90 ደቂቃ በቆየው ብርቱ ሙግት ሀሪስ በተደጋጋሚ ትራምፕ ላይ ዘለፋና ትችት እየወረወሩ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ሲያበሳጩ ታይተዋል። ክርክሩንም የጦፈ አድርገውታል።

የዲሞክራቶች ዕጩ ፕሬዛዳንት ካማላ ሃሪስ ትራምፕን ለመደገፍ በወጡ ሰዎች ብዛት እና ትራምፕ ከዓመታት በፊት በነበረው የካፒቶል ሁከት ላይ ስላሳዩት ተግባር አንስተዋል።

ጨምረውም ትራምፕ ፕሬዝዳንት በነበሩ ጊዜ ሹማምንት የነበሩ ሰዎች አሁን እንዴት በይፋ እንዴት እየተቿቸው እንዳሉ ሃሪስ የተናገሩ ሲሆን የፖለቲከኛዋ ነጥቦች የቀድሞው ፕሬዝደንት በክርክሩ ተሸናፊ መስለው እንዲታዩ አድርገዋል።

ይህ የሃሪስ የክርክር መንገድ የሪፐብሊካኑን ዕጩ ትራምፕ በራሳቸው ነጥቦች ላይ ከማተኮር ይልቅ ከዚህ በፊት የፈጸሙትን ተግባር እና የሰጡትን አስተያየት ላይ እንዲጠመዱ አድርጓቸዋል።

ሃሪስ መጀመሪያ ላይ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄዎች በመለሱበት ወቅት ትራምፕን ለመደገፍ ከወጡ ሰዎች ጋር በተያያዘ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዋ አሜሪካውያን ትራምፕን ለመደገፍ ወጥተው ተሰላችተው ሰልፉን ጥለው መሄዳቸውን በማንሳት ትራምፕን ወርፈዋል።

በዚህ ንግግር የቀድሞው ፕሬዝደንት ተበሳጭተው የታዩ ሲሆን ረዥሙን ጊዜያቸውን ስለራሳቸው ጥንካሬ በማውራት፣ ሊደግፏቸው የወጡ ሰዎችን ብዛት ላይ ለተሰጠው አስተያየት ምላሽ ለመስጠት በመሞከር እና ሃሪስን በመተቸት አሳልፈዋል።

ትራምፕ እና ሃሪስ

በመቀጠል ትራምፕ እውነታው ያልተረጋገጠ ሪፖርት ላይ ተመርኩዘው ረዥም ገለጻ ሲያደርጉ ተደምጠዋል። ሪፖርቱ በአሜሪካዋ ኦሃዮ ግዛት ስፕሪንግፊልድ በተባለች ከተማ ከሄይቲ የመጡ ስደተኞች የቤት እንስሳትን በመጥለፍ ወስደው ይበላሉ የሚል ነው።

የትላንት ምሽቱ ሙግት፣ ተቀናቃኞቹ ዕጩ ፕሬዝዳንቶች ነጥባቸውን ባቀረቡበት፣ ራሳቸውን በተካለከሉበት እንዲሁም የተፎካካሪዎቻቸውን ድክመት ባሳዩበት መስፈርት ቢላካ የወቅቱ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሀሪስ ትራምፕ ላይ የበላይነቱን እንደወሰዱ ያሳያል።

በትላንት ምሽቱ ክርክር የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተዳሰዋል።

በርካታ አሜሪካውያን ሃሪስ ቁልፍ አባል በሆኑበት የባይደን አስተዳደር የኑሮ ውድነት እና ኢኮኖሚውን በያዙበት መንገድ ደስተኛ እንዳልሆኑ የዳሰሳ ጥናት አመላክቷል።

ነገር ግን ሃሪስ የኢኮኖሚውን ጉዳይ ወደ ትራምፕ በማዞር ትችት ሰንዝረዋል። ሃሪስ የትራምፕን አዲስ የታክስ ዕቅድ በመተቸት “ታክስ የመሸጥ ዕቅድ” ሲሉ ከተቹ በኋላ የወግ አጥባቂዎቹን የ2025 አከራካሪ የኢኮኖሚ ዕቅድ አንስተዋል።

ቀድሞ የዚህ ዕቅድ አካል የነበሩት ትራምፕ “አሁን የለሁበትም” ብለው የራሳቸውን የታክስ ዕቅድ ተከላክለዋል። በዚህም በሳቸው የስልጣን ዘመን የነበረውን የታሪፍ አሰራር በሙሉ የባይደን አስተዳደር አንስቶታል ሲሉ ተችተዋል።