አሜሪካዊቷ ድምፃዊት ቴይለር ስዊፍት

ከ 3 ሰአት በፊት

አሜሪካዊቷ ድምፃዊት ቴይለር ስዊፍት በሚቀጥለው ምርጫ ድምጿን የምትሰጠው ለካማላ ሀሪስ እንደሆነ አስታወቀች።

ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሀሪስ ከቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ያደረጉት የምርጫ ክርክር ከተጠናቀቀ በኋላ ነው ድምፃዊቷ ይህን ያለችው።

የፖፕ ሙዚቃ ዘውግ ኮከቧ ስዊፍት ማክሰኞ ምሽት በኢንስታግራም ገጿ ባጋራችው መልዕክት “ጥናቴን ሠርቼ ጨርሻለሁ” ብላለች።

“በ2024 ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ድምፄን የምሰጠው ለካማላ ሀሪስ እና ቲም ዋልዝ [ዕጩ ምክትል ፕሬዝደንት] ነው። ምክንያቱም እኔ ለማምንበት ጉዳይ የምትታገል ናት” ስትል ፅፋለች።

ስዊፍት ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሀሪስን “ተሰጥዖ ያላት ጠንካራ መሪ” ስትል ገልፃቸዋለች።

ድምጻዊቷ አክላ “በእኔ እምነት በወከባ ሳይሆን በመረጋጋት የምንመራ ከሆነ በሀገራችን ብዙ ነገሮችን ማሳካት እንችላለን” ብላለች።

ስዊፍት በኢንስታግራም ገጿ መልዕክቷን የፃፈችው ከድመቷ ጋር የተነሳችውን ፎቶ አብራ ሲሆን ይህ ደግሞ የትራምፕ ዕጩ ምክትል የሆኑት ጄዲ ቫንስ የሰጡትን አስተያየት ለመተቸት እንደሆነ ተገምቷል።

የኦሃዮ ግዛት ሴናተር የሆኑት ዕጩ ምክትል ፕሬዝደንት ጄዲ ቫንስ በአውሮፓውያኑ 2021 ካማላ ሀሪስን ጨምሮ በርካታ ዲሞክራቶችን “ሕይወታቸው የላሸቀ፤ ልጅ አልባ ድመት አሳዳጊ ሴቶች” ሲል ዘለፋ ማሰማታቸውን ተከትሎ ብዙ ትችት ገጥሟቸው ነበር።

ቴይለር ስዊፍት አክላ ካማላ ሀሪስ ለምክትልነት ያጯቸውን የሚኒሶታው ሀገረ-ገዥ ቲም ዋልዝ “ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን እና ለሴቶች ገላ መብት የቆሙ ናቸው” ስትል አድንቃቸዋለች።

ስዊፍት ድምጿን ለማን እንደምትሰጥ ለማጋራት የተነሳሳችው በሰው ሰራሽ ልኅቀት [ኤአይ] የተሠራ እና ስዊፍት ለትራምፕ ድጋፏን ስትገልፅ የሚያሳይ ምስል በዶናልድ ትራምፕ ድረ-ገፅ ላይ ከተለጠፈ በኋላ ነው።

ሙዚቀኞቹ ጆን ሌጀንድ እና ኦሊቪያ ሮድሪጎ እንዲሁም ተዋናዩ ጆርጅ ክሉኒ እና ዳይሬክተሩ ስፓይክ ሊ ለካማላ ሀሪስ ድምፃቸውን እንደሚሰጡ ይፋ ያደረጉ ታዋቂ ሰዎች ናቸው።

የነፃ ትግል ተፋላሚው ሆልክ ሆገን፣ የቴሌቪዥን ኮከቧ አምበር ሮዝ እንደ ቢሊየነሩ ኢላን መስክ ደግሞ ለዶናልድ ትራምፕ ድጋፋቸውን ገልፀዋል።

ስዊፍት ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለባይደን እና ሃሪስ ድጋፏን ገልፃ ነበር።

የቴይለር ስዊፍት አብዛኛዎቹ አድናቂዎች ታዳጊዎችና ሴቶች በመሆናቸው ለካማላ ድጋፏን ማሳየቷ ምን ያህል ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚለው አጠያያቂ ሆኗል።

ዘፋኟ በኢንስታግራም 283 ሚሊዮን ተከታዮች ያሏት ሲሆን ለካማላ ድምጿን እንደምትሰጥ ያሳወቀችበት መልዕክት ከ5 ሚሊዮን በላይ ‘ላይክ’ አግኝቷል።