September 11, 2024 

በሀገሪቱ ተመዝግበው የሚገኙ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖችና የታዋቂ አትሌቶች ሕጋዊ ወኪል ጠበቆች በቀን 6/12/16 እና በ15/12/16 ዓ.ም ለኢ.ፊ.ድ.ሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የቅሬታ አቤቱታ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የብሄራዊ ፌዴሬሽኖችና የታዋቂ አትሌቶች ሕጋዊ ወኪል ጠበቆች ከላይ በተገለፀው መሠረት ከሕግና ስርዓት ውጪ በሆነ መንገድ በተፈፀሙ ተግባራት ላይ ተገቢው አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሥ/አ ቦርድ አባላትና በፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አሸብር ላይ እንዲወሠድ በማለት ከአንድም ሁለት ጊዜ የሕግ ሂደቱን በጠበቀ መልኩ የቅሬታ አቤቱታ በማቅረብና የአምስት ቀናት ቀነ-ገደብ ቢያስቀምጡም ጥያቄ የቀረበለት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ምላሽ ሳይሠጥ ቆይታል።

በሦስት የሕግ ባለሙያተኞች የሕግ ትንታኔ ይሰጣል።

 አያሌው ቢታኔ መንዛ

በማናቸውም የፌዴራል ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ

 አቶ ጳውሎስ ተሠማ ኢላላ፣

የሕግ አማካሪና በማናቸውም ፍ/ቤት ጠበቃ

 አቶ ኃይሉ ሞላ ደምሴ

በማናቸውም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃና የሕግ አማካሪ ናቸው።

የኦሎምፒክ ተሳታፊ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖችና በታዋቂ ግለሠቦች የተወከሉ የህግ ባለሙያዎች(ህጋዊ ጠበቆች)

ትናንት(ሐሙስ) በኢ.ፊ.ድ.ሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣በዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እና በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሥ/አ ቦርድ አባላት ላይ ክስ መመስረታቸው መግለፃችን ይታወሳል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ ከላይ በተጠቀሱት አካላት ላይ የቀረበውን የክስ አቤቱታ የመረመረውና የተመለከተው ፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ላይ የዕግድ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገንዘብ ያንቀሳቅስባቸዋል ተብለው የተለዩ በሀገሪቱ የሚገኙ 11 ባንኮች ላይ ያለውን ገንዘብ (አካውንት) ከዛሬ ጳጉሜን 5/13/2016 ዓ.ም ጀምሮ ሌላ ውሳኔ እስኪተላለፍ ድረስ እንዳያንቀሳቅስ የዕግድ ትዕዛዝ ተላልፎበታል።

ፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በቀን 4/13/16 በቁጥር 320687 ባስተላለፈው የዕግድ ትዕዛዝ መሠረት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ

👉 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣

👉 በወጋገን ባንክ፣

👉 በአዋሽ ባንክ፣

👉 በአቢሲኒያ ባንክ፣

👉 በዳሽን ባንከ፣

👉 በሕብረት ባንክ፣

👉 በንብ ባንክ፣

👉 በአባይ ባንክ፣

👉 በግሎባል ባንክ፣

👉 በኦሮሚያ ኅብረት ስራ ባንክ እና

👉 በዘመን ባንክ ያለው የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች (አካውንቶች)በከሳሽና በተከሳሾች መካከል ባለው ክርክር ላይ ፍ/ቤቱ ውሳኔ እስኪሠጥ ድረስ ሳይንቀሳቀሱ ታግደው እንዲቆዩ ትዕዛዝ ከመሠጠቱም ሌላ ውሳኔው ለሁሉም ባንኮች ዋና መ/ቤቶች ተልኮ እንዲያስፈፅሙ አዟል።

***

የጋዜጣዊ መግለጫ ጥሪ ሙሉ ቃል እንዲህ ይነበባል

ከኦሎምፒክ ተሳታፊ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና ከታዋቂ ግለሰቦች የተወከልን እንዲሁም የዜግነት ኃላፊነት የሚሰማን ጠበቆች

📌 የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ስላካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ፣

📌 ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ስለተከናወነው የኦሎምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት ምርጫ፤

📌 ከዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፣

📌 ከANOCA፣

📌 ከአዲዳስ ካምፓኒ፣

📌 ከኢትዮጵያ መንግሥት እና

📌 የመንግሥት የልማት ድርጅቶች

📌 ለቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ስለተገኘው ገንዘብ የኦዲት ምርመራ አለመደረግና

📌 በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ስለአጋጠሙ ያልተገቡ ተግባራት

በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት እና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስተዳደር ችሎት በተከሳሾች እነ ኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስን አካቶ 5ት ሰዎች እንዲሁም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ስለተከሰሱበት የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት ክስ ከዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ቻርተር፣ ከኦሎምፒክ ኮሚቴው መተዳደሪያ ደንብ ፣ ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት መመሪያ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ሕግ አንጻር የተመሠረተባቸውን ዝርዝር የክስ አቤቱታና በተከሳሾች ላይ እንዳይፈጽሟቸው በፍርድ ቤቱ ስለተላለፈው የእግድ ትእዛዝ የሚገልጽ የሕግ ትንታኔ በመስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም በኃይሌ ግራንድ ሆቴል ከጠዋቱ በ4፡00 ሰዓት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የምንሰጥ ስለሆነ በዚሁ እለት ተገኝታችሁ እንድትዘግቡ እንጠይቃለን፡፡