እንቅስቃሴዋ የተስተጓጎለ መንገደኛ

11 መስከረም 2024, 13:08 EAT

የኬንያ ዋና አየር ማረፊያ በሕንድ ኩባንያ እንዲተዳደር የተያዘውን እቅድ ተከትሎ ሠራተኞች በመቱት አድማ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ጉዞ ተስተጓጎለ።

የአቪየሽን ሰራተኞች ማኅበር በመዲናዋ ናይሮቢ የሚገኘውን ጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ለ30 ዓመት በኪራይ እንዲያስተዳደር አዳኒ ግሩፕ ለተሰኘ የሕንድ ኩባንያ ለመስጠት የቀረበውን እቅድ በጥብቅ ተቃውሞታል።

ማኅበሩ ስምምነቱ በርካታ ሠራተኞችን ሥራ አጥ ያደርጋል ብሏል።

በዚህ ምክንያት ዛሬ ረቡዕ ጠዋት ላይ የማኅበሩ አባላት ሥራቸውን በማቆማቸው በረራዎች እንዲሰረዙ እና እንዲዘገዩ ሆኗል።

መንግሥት በበኩሉ “አየር ማረፊያው ከአቅሙ በላይ ነው እየሰራ ያለው በመሆኑም ይህን ለማሻሻል የግል ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል” ሲል እቅዱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።

ረቡዕ ጠዋት ላይ ከአየር ማረፊያው ውጭ መንገደኞች በሻንጣዎቻቸው ላይ ተቀምጠው የሚሆነውን ሲጠባበቁ ታይተዋል።

የጆሞ ኬንያታ አየር ማረፊያ በሰጠው መግለጫ “ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ የተወሰኑ ሥራዎች ተጀምረዋል፤ ወደ መደበኛ ሥራው ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው” ሲል ለተፈጠረው ችግር ደንበኞቹን ይቅርታ ጠይቋል።

የአቪየሽን ሠራተኞች ማኅበሩ ቀደም ብሎ መንግሥት ከውጪ ኩባንያው ጋር የገባውን ስምምነት ዝርዝር ይፋ ባለማድረጉ ላልተወሰነ ጊዜ አድማ እንደሚያደረግ አስጠንቅቆ ነበር።

የኬንያ የሕግ ማኅበረሰብ እና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአገሪቷን ወሳኝ ሃብት ለግል ድርጅት አሳልፎ መስጠት ምክንያታዊ አይደለም ሲሉ እቅዱን ተችተዋል።

ሁለቱ ተቋማት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት የመቃወሚያ ክስ ያቀረቡ ሲሆን ዳኞች ስምምነቱን ለመገምገም የሚያስችላቸውን ጊዜ ለመስጠት ስምምነቱን አስቁሞታል።

ሆኖም ፍርድ ቤቱ የመጨረሻውን ውሳኔ መቼ እንደሚሰጥ የተቀመጠ ጊዜ የለም።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጆሞ ኬንያታ አየር ማረፊያ ባለው ተቃውሞ ምክንያት ከኬንያ እና ወደ ኬንያ የሚደረጉ በረራዎች መስተጓጎላቸውን አስታውቋል።

አየር መንገዱ በማኅበራዊ ሚድያ ገፆች በለቀቀው መግለጫ በአድማው ምክንያት ለተከሰተው መስተጓጎል ይቅርታ ጠይቆ ሁኔታውን እየተከታተለ እንደሆነ ጠቁሟል።