የህወሓት ሊቀ-መንበር

11 መስከረም 2024, 13:19 EAT

የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጳጉሜ 5/2016 በሰጡት መግለጫ የትግራይ ክልል እና የኤርትራ ባለሥልጣናት ግንኙነት እያደረጉ እንደነበር ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለረዥም ዓመታት ጉልህ ሚና የነበረው ህወሓት በሁለት ጎራ ተከፍሎ ከፍተኛ ውጥረት በገባበት ወቅት ነው ደብረፅዮን ይህንን ያሉት።

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር እና በህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ኃይል በየፊናቸው መግለጫ በማውጣት ላይ ይገኛሉ።

ሊቀመንበሩ በመግለጫቸው ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ማዕከላዊው መንግሥት ብቻ ሳይሆን ከኤርትራ እና ከፋኖ ኃይሎች ጋር ሰላም መፍጠር አለብን በሚል አቋም፤ በጌታቸው ረዳ የሚመራ ልዑክ ከኤርትራ ጋር ድርድር ያደርግ እንደነበር ጠቁመዋል።

ነገር ግን ይህ ይሆን የነበረው በህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና በማዕከላዊው መንግሥት እውቅና እንደሆነ ገልፀዋል።

“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ራሳቸው ‘ሻዕቢያ ከናንተ ጋር ከባድ ቅሬታ አለው፤ ራሳችሁ ተግባቡ’ ይሉን ነበር” ብለዋል ሊቀመንበር ደብረፅዮን።

ደብረፅዮን፤ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ የኤርትራ ባለሥልጣናት እና የትግራይ ክልል አስተዳዳሪዎች በምን ጉዳይ ላይ እንደመከሩ በዝርዝር ከመግለፅ ተቆጥበዋል።

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ልዑክ ከኤርትራ ባለሥልጣናት ጋር በተደጋጋሚ ውይይት ያደርግ እንደነበር የጠቀሱት ደብረፅዮን፣ አሁን ይህን ግንኙነት [ከኤርትራ ጋር] ሌላ መልክ ለማስያዝ ሆነ ተብሎ “በነባር አመራሮች” የተካሄደ አስመስሎ ማቅረብ ትክክል አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል።

የህወሓት መሪዎች ከትግራይ ጦርነት በኋላ ከኤርትራ ባለሥልጣናት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ሲናገሩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሊቀመንበሩ በንግግራቸው በሁሉም ወገኖች እውቅና የተደረገው ውይይት አሁን እንደ አዲስ መነሳቱ ትክክል አይደለም ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ የሰጡትን አስተያየት ተችተዋል።

አቶ ጌታቸው ባለፈው ወር ህወሓት ያካሄደውን ጉባዔ ተቀባይነት የሌለው እና ሕጋዊ ያልሆነ ሲሉ መተቸታቸው አይዘነጋም። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አክለው ይህ የህወሓት እንቅስቃሴ ከተጠያቂነት አምልጦ ድጋሚ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚያደርገው ጥረት ነው ብለዋል።

አቶ ጌታቸው በጉባዔው እንደማይሳተፉ ባሳወቁበት ወቅት የህወሓት “ከፍተኛ አመራሮች” ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር እየሠሩ ነው ሲሉም ወቅሰው ነበር።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ለክልሉ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አራት የህወሓት አመራሮች “ደጀን ይሆነናል ያሉትን የውጭ ኃይል ተማምነው የሚያደርጉት ድርጊት ወዳልተፈለገ ችግር ሊያስገባን ይችላል” ሲሉም ተሰምተዋል።

አቶ ጌታቸው አራት ያሏቸውን አመራሮችንም ይሁን የውጭ ኃይሎች ያሏቸውን አካላት በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

የኤርትራ ባለሥልጣናት እና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት እያደረጉ ነው የተባለውን ውይይት በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ደብረፅዮን፣ “ጥረታችን ውይይቱን በሰላማዊ መንገድ ማስቀጠል ነው” ብለዋል።

የህወሓት ሊቀ መንበር፤ በትግራይ እና ኤርትራ ድንበር አካባቢዎች የነበረው የፀጥታ ጉዳይ በውይይቱ የተፈታ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎች አብይ የሚባሉ ጉዳዮች ግን በፌዴራል መንግሥቱ መሪነት እንደሚፈቱ ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአውሮፓውያኑ 2018 ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ መንግሥት ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማለሳለስ በርካታ እርምጃዎች መውሰዳቸው ይታወሳል።

ነገር ግን ለሁለት ዓመታት ከዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በኋላ በኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መካከል ያለው ግንኙነት መልሶ የሻከረ ይመስላል።