የሶማሊላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሳ ካይድ
የምስሉ መግለጫ,የሶማሊላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሳ ካይድ

11 መስከረም 2024, 14:11 EAT

የሶማሊላንድ መንግሥት በፀጥታ ስጋት ምክንያት ሐርጌሳ የሚገኘውን “የግብፅ የባሕል ቤተመጽሐፍ” በዘላቂነት መዝጋቱን አስታወቀ።

የሶማሊላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ ገፁ በለጠፈው መግለጫ ነው መንግሥት ሐርጌሳ የሚገኘውን ቤተመጽሐፍ መዝጋቱን ያስታወቀው።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው በካባድ የፀጥታ ስጋቶች ምክንያት ቤተመጽሐፉ እንዲዘጋ ከመወሰኑም በላይ ሠራተኞቹ በ72 ሰዓታት ራስ ገዟን ሀገር ለቀው እንዲወጡ አዟል።

ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነችው ሶማሊላንድ ከሳምንት በፊት የግብጽ ጦር በሶማሊያ ተሰማርቶ የቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ ሲወድቅ በዝምታ አልመለከትም ማለቷ ይታወሳል።

ይህ የሐርጌሳ ውሳኔ ግን ከዚህ መግለጫ ጋር ስለመያያዙ ምንም የተባለ ነገር የለም።

የሶማሊላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሳ ካይድ በሰጡት መግለጫ “ሁኔታውን በጥንቃቄ ካጤንን በኋላ ባለው ከባድ የፀጥታ ችግር ምክንያት የግብፅ የባሕል ቤተመጽሐፍን እስከ መጨረሻው ለመዝጋት ወስነናል” ብለዋል።

ሚኒስትሩ፤ የሶማሊላንድ መንግሥት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ባጣሩት መሠረት ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩን አረጋግጠዋል ሲሉ ተናግረዋል።

“ሁኔታዎችን በጥንቃቄ ካጤንን በኋላ የግብፅ የባሕል ቤተመጻሕፍን ለመዝጋት ወስነናል” ያሉት ሚኒስትሩ ውሳኔው ቀላል እንዳልሆነ አሳውቀዋል።

የቤተ መጽሐፉ ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ በሚቀጥሉት 72 ሰዓታት ውስጥ ሶማሊላንድን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸውም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

አክለው የሶማሊላንድ መንግሥት ከግብፅ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሚቀጥል አስታውቀው፣ ነገር ግን “የሕዝባችን ሰላም እና ፀጥታ ከምንም በላይ ነው፤ ውሳኔውም የሀገራችንን ጥቅም መሠረት ያደረገ ነው” ብለዋል።

ከሳምንታት በፊት የግብጽ ጦር አውሮፕላኖች በሞቃዲሾ መታየታቸውን ተከትሎ የሶማሊላንድ መንግሥት የግብጽ ጦር በሶማሊያ ተሰማርቶ የቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ ሲወድቅ በዝምታ አልመለከትም ማለቱ ይታወሳል።

የግብጽ ጦር በሶማሊያ መስፈርን በመቃወም የሶማሊላንድ መንግሥት ባወጣው መግለጫ የካይሮ ጦር በአፍሪካ ቀንድ መገኘትን አጥብቆ ተቃውሞ ነበር።

ይህ የአሁኑ የሶማሊላንድ መንግሥት እርምጃ ከዚህ ጋር የተያያዘ ይሁን አይሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ “በየትኛውም ምክንያት የውጪ ኃይልን በጎረቤት አገር ሶማሊያ ማሰማራት፤ ቀጠናው መረጋጋት እንዳይኖረው ሊያደርግ ይችላል፣ የሰላም ማስከበር ጥረቱን ይጎዳል እንዲሁም ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ውጥረት ይፈጥራል” ብሎ ነበር።

የሶማሊላንድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በወቅቱ ባወጣው መግለጫ “በአፍሪካ ቀንድ እንደምትገኝ ሉዓላዊት እና ዴሞክራሲያዊት አገር ልክ እንደ ሌሎች ጎረቤት አገራት የሕዝባችንን እና የቀጠናውን መረጋጋት እና ደኅንነት የሚያውክ የውጪ ኃይል መሰማራትን ሙሉ በሙሉ አንቀበልም” ይላል መግለጫው።

የባሕር በር አልባዋ ኢትዮጵያ የንግድ መተላለፊያ ወደብ ለማግኘት እና የባሕር ኃይሏን ለማጠናከር ካላት ፍላጎት የተነሳ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መፈረሟ ከሞቃዲሾ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ ከትቷት ቆይቷል።

ሞቃዲሾ የአዲስ አበባ እና ሐርጌሳ ስምምነት ሉዓላዊነቴን እና የግዛት አንድነቴን የሚጥስ ነው ስትል ጠንከር ያለ ተቃውሞ ስታሰማ ቆይታለች።

ሶማሊያ ከግብጽ ጋር ወታደራዊ ትብብር ስምምነት ከመፈራረሟ በተጨማሪ ካይሮ ሠራዊቷን ለሰላም ማስከበር የኢትዮጵያ ጎረቤት ወደ ሆነችው ሶማሊያ ለመላክ ጥያቄዋን በይፋ አቅርባለች።

ይህ ግን በኢትዮጵያም ሆነ በሶማሊላንድ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።