September 11, 2024 

ቅዱስ ዮሐንስ፡ ርእሰ ዐውደ ዓመት
መ/ር ጌታቸው በቀለ

ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የመሸጋገሪያው ዕለት በየዓመቱ “ቅዱስ ዮሐንስ” እየተባለ ይጠራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዘመን መለወጫ፣ ዕንቁጣጣሽ፣ ርእሰ ዐውደ ዓመት ይባላል፡፡ ርእሰ ዐውደ ዓመት የበዓላት ሁሉ የበላይ፣ ራስ ማለት ነው፡፡ ይህ በዓል የዓመት መጀመሪያ እንደመኾኑ መጠን በየዓመቱ ወሮች በመጀመሪያ ቀን ይከበራል፡

ቅዱስ ዮሐንስ ለምን ተባለ?
ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎ የተሰየመው በነቢዩ ዘካርያስ ልጅ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እንጂ በሐዋርያው (ወንጌላዊው) ቅዱስ ዮሐንስ አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን ሲጽፍ “የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ እነሆ መንገድህን የሚጠርግ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፡፡ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፡፡ ጥርጊያውን አቅኑ” እያለ “በምድረ በዳ የሚጮኸ ሰው ድምፅ” ተብሎ በኢሳይያስ እንደተነገረ የነቢዩ ዘካርያስ ልጅ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነስቶ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!” እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እየመሰከረ በምድረ በዳ የንስሐን ጥምቀት እያጠመቀ መጣ ብሎ ለዘመነ ወንጌል የመጀመሪያ ምዕራፍ ትምህርትና ተግሳጽ እንዳደረገው ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ ይነግረናል፡፡ /ማር. ፩1፥፲፬፤ ኢሳ. ፵፥፫-፬/፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻም በሄሮድስ ትዕዛዝ ራሱን የተቆረጠ ታላቅ ሰማዕት ነው፡፡

የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱን በመረዳት የቤተ ክርስቲያን አበው የበዓላትን ድንጋጌ በወሰኑበት አንቀጽ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በሚከበርበት መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ እንደወሰኑ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ ፩-፫/፡፡

ዘመን መለወጫ

በኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በመስከረም ወር የሆነበትን ምክንያት ሊቃውንቱ ሲያትቱ ብርሃናት ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ክዋክብት የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱ ከቀኑ ጋር እኩል ፲፪ ሰዓት ይሆናል፡፡ ዓመቱን ጠንቅቀው ሲቆጥሩ ፫፻፷፬ ቀናት ይሆናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ለዘመን መታወቂያው ይሆን ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትንም ፈጠረ” ይላልና /ሔኖክ. ፳፩፥፵፱/፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ በፍል ውኃ አጥለቅልቆ በኃጢአት ሕይወት ይኖሩ የነበሩት የኖኅ ዘመን ሰዎች ቀጥቶ ካጠፋ በኋላ ከንፍር ውኃ ምድር የተገለጠችበት ወር በመኾኑ ነው /ኩፋሌ. ፯፥፩/፡፡ “በመጀመሪያው ወር ምድር ታየች የንፍር ውኃም ከምድር ደረቀ” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መሠረት አድርገው የአቡሻኸር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስቀምጣሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖናዊ ሥርዐት ያጠኑ ሊቃውንት ደግሞ አዲስ ዓመት መስከረም አንድ ቀን መሆኑን አስመልክተው በክታባቸው እንዳስቀመጡት በአራቱ ወንጌላውያን ዘመኑን ይከፍሉታል፡፡ ምክንያቱም በዘመነ ዮሐንስ ተፀንሶ በዘመነ ማቴዎስ ተወልዶአል፡፡ በዘመነ ማርቆስ ተጠምቋል፡፡ በዘመነ ሉቃስ ተሰቅሎ ዓለምን ከፍዳና ከመርገም ነጻ አውጥቷል፤ እያሉ ታሪካዊ ሐረጋቸውን ጠብቆ አራቱ ወንጌላውያን ተከትለው ያለ እንቅፋት እንደሚጓዙ ያስረዳሉ፡፡
እንቁጣጣሽ
እንቁጣጣሽ የተባለበት ምክንያት አንደኛ “እንቁ – ዕፅ አመጣሽ” ብሎ የአበባውን መፈንዳት ያመለክታል፡፡ ሁለተኛ ኖኅ ለሦስቱ ልጆቹ አህጉራትን በዕጣ ሲያካፍላቸው አፍሪካ ለካም ደረሰችው፡፡ በአፍሪካ ምድርም ሲገባ በመጀመሪያ ያረፈው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሀገሪቱም በአደይ አበባ አሸብርቃ ነበር፡፡ ወሩ ወርኀ መስከረም በመኾኑ ደስ ብሎት “እንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ” በማለት ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል፡፡ ሦስተኛው /፩ ነገ.፲፥፩-፲/ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሣባ (አዜብ) ጋር የተያያዘ ትውፊት ነው፡፡ የንጉሡን ጥበብ ከመስማት ማየትን መርጣ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ከብዙ ሠራዊቶቿ ጋር የእጅ መንሻ በመያዝ ሄደች፡፡ ንጉሡም በደስታ ተቀብሎ እርሱም “እንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንሽ” በማለት ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ የጠቢቡ ሰሎሞንን ዝና ሰምታ ኢየሩሳሌም ተጉዛ ስትመለስ ንጉሥ ሰሎሞን “እንቁ ለጣትሽ (ለጣትሽ እንቁ) ጌጥ ይሁንሽ” በማለት አራት ዓይነት ቀለም የሚታይበት በቀንና በሌሊት የምታበራ ቀለበት ሰጥቷታል፡፡ ወሩም ወርኀ መስከረም ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት እንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜ ወጥቷል፡፡ ይህን ታሪክ መነሻ አድርገው “እንቁጣጣሽ” የሚለው ስያሜ ከዚያ እንደመጣ የታሪክ ድርሳናት ያስረዱናል፡፡ በኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ዕለት ምድሪቱ በክረምቱ ዝናብ ረስርሳ ድርቀቷ ተወግዶ በአርንጓዴ እጸዋት ተውባ ሜዳው፣ ሸለቆውና ተራራው በአደይ አበባ ተንቆጥቁጠው የሚታዩበት ወቅት በመሆኑ ዕለቱ “እንቁጣጣሽ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ ወቅት ሕፃናትና ልጃገረዶች ነጭ ባሕላዊ ልብስ በመልበስ፣ ለምለም ቄጤማና አደይ አበባ በመያዝ በአካባቢያቸው በመዞር አዲስ ዘመን መበሠሩን “እንኳን አደረሳችሁ” በማለት በቸርነቱ ዓመታትን የሚያፈራርቀውን እግዚአብሔርን በዝማሬ ያመሰግናሉ፡፡

የዘመን አቆጣጠራችን ከምዕራባውያን ለምን ተለየ?

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ባሕረ ሐሳብ በሚል መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከምዕራባውያን የተለየበትን ምክንያት ሲገልጹ “ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ዘመን መነሻ ያደርገው ይተቀማሉ፤ ታላቁ እስክንድርም የገነነበት ዘመን መቁጠሪያቸው ሆኖ ነበር” የእኛ ካህናትም ዘመነ እስክንድር በሚል ይጠቀሙበት እንደነበር መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ሶርያውያን የዘመን አቆጣጠራቸውን የሚለኩት በፀሐይ ቆጥረው ለዓመቱ ፫፻፷፭ ቀን ከስድስት አካፍለው ዕለትን መስጠትን ከሮማውያን በተዋሱት ጊዜ የዓመቱን መጀመሪያ አዲስ ዓመት ይሉታል፡፡ በኋላ የሰማዕታት መታሰቢያ እንዲሆን በ፬፻፷ ዓመተ እግዚእ ወደ መስከረም አንድ ቀን ለወጡት፡፡ የሀገራችን ሊቃውንትም አዲስ ዓመታችን መስከረም አንድ ቀን እንዲሆን የወሰኑት ይኸንን በመከተል ነው፡፡ የዓመቱን መጀመሪያ በመስከረም ማድረግን ከሶርያውያንም ሆነ ከግብጾች ብናገኘውም ጀማሪው በ፵፮ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ይገዛ የነበረው ዩልዮስ ቄሣር ስለነበር በዩልዮስ ባሕረ ሐሳብ ይባላል፡፡

ዩልዮስ ቄሣ በ፵፮ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ባወጣው የዘመን አቆጣጠር ሥርዐት መሠረት ዓመቱን ፫፻፷፭ ዕለት ከስድስት ሰዓት አድርጎ ለአራቱ ወራት ፴፣፴ ዕለት ለእንዱ ፳፰ ቀን በአራት ዓመት አንዴ ፳፱ ቀናት ለቀሩት ሰባት ወራት ፴፩፣፴፩ ቀናት መድቦላቸው በ፲፪ ቦታ ከፍሎታል፡፡ አውሮፓውያኑ የሚጠቀሙበትን ይህን አቆጣጠር መነሻ አድርገው ነው፡፡ የእኛ ዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን እንዴት እንደተለየ አሥራት ገብረ ማርያም የዘመን አቆጣጠር በሚለው መጽሐፋቸው ሲገልጹ “ዲዮናስዮስ የተባለው የሮም መነኩሴ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተወለደበት ዘመን በስሌት ለመድረስ የተከተለው መንገድ የታሪክ ክስተትን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ዘመን ለመሰወን የታሪክ ክስተትን አልተከተለችም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የተከተለችው ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን 5500 ዘመንን ነው” በማለት የልዩነቱን ምክንያት ይገልጻሉ፡፡
የዘመን አቆጣጠር ልዩነት መነሻው የዚህ ክስተት መሆኑን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲያረጋግጡ “ኢትዮጵያ ዘመነ ብሉይን እንዲህ አስከትላ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት ብላ ስትቆጥር ዘመነ ሐዲስ ልዩ ሆኖ ከማንም ቁጥር አይገጥምም፡፡ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከምስራቆቹም ከምዕራቦቹም ሁል ጊዜ በሰባት ዓመት ታጎድላለች፡፡ ምክንያቱም ባለ ታሪኮችን ትታ ወንጌል ተርጓሚዎችን መነሻዋ ስላደረገች ነው” ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያና የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ልዩነት ሊኖረው ቻለ፡፡
እንደመውጫ
እግዚአብሔር አምላካችን ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ የሚሰጠን መልካም ነገር እንድንሠራበት ነው፡፡ በየዓመቱ አዲስ ዓመት የሚሰጠን የትናንት ስሕተታችንን እንድናርምበት፣ የተጣላን እንድንታረቅ፣ የበደልን እንድንክስ፣ የታረዘን እንድናለብስ፣ የተጠማን እንድናጠጣ፣ የራበውን እንድናበላ እንጂ፤ በኃጢአት ሕይወት እንድንመላለስ አይደለም፡፡ የዘመኑ መቀየር ከቁጥር በዘለለ የእኛው አስተሳሰብ እንዲቀየር ነው፡፡ ለሥጋዊ ኑሮአችን መሳካት በእቅድ እንደምንመራው ሁሉ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እናስብ፤ ቃለ እግዚአብሔር ለመማር፣ ንስሐ ለመግባት፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል መንፈሳዊ እቅድ እናውጣ! ተግባራዊ ለማድረግም ጥረት እናድርግ፡፡ ከዘመን ወደ ዘመን የምንሸጋገረው ቅዱሳን መላእክት በሚለምኑልን የብደር ዕድሜ እንደሆነ እንረዳ፡፡ አምላካችን ከእኛ ሕይወት ፍሬ ለማግኘት በልጅነታችን፣ በወጣትነትና በሽምግልና ዕድሜያችን ሦስት ጊዜ መጣ፤ ፍሬ ሃይማኖትና ምግባር አጣብን አትክልተኞቹን ቅዱሳን መላእክትን “ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጎሳቁላለች?” ቢላቸው “ጌታ ሆይ ዙርያዋን እስክኮተኩትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት” እያሉ በለመኑት የብድር ዕድሜ ነው አዲስ ዓመቱን ለማየት የቻልነው /ሉቃ. ፲፫፥፮-፱/፡፡

በተሰጠን የንስሐ ዕድሜ መልካም ነገር ለመሥራት እንነሣ፤ በስንፍና ያሳለፍነው ጊዜ ይብቃን! ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት ጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” እንዲል /፩ኛ ጴጥ. ፬፥፫/፡፡ አዲሱን ዓመት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ፣ አቅመ ደካሞች የኾኑ ወገኖቻችን ጋር አብረናቸው በዓል እናክብር፤ ያን ጊዜ እኛ በሕይወት ተቀይረን አዲሱ ዓመት መቀበላችን እውነት ይኾናልና፡፡

መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዋቤ መጻሕፍት
✍️ መጽሕፍ ቅዱስ
✍️ ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
✍️ የቤተክርስቲያን ታሪክ በኢትዮጵያ
✍️ ባሕረ ሐሳብ (አቡሻኸር)
✍️ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ
✍️ መርሐ ዕውር
✍️ ሐመር መጽሔት መስከረም 2000 ዓ.ም