የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዩ አጽቀ ሥላሴ (አምባሳደር)

ዜና በግብፅ የሚሰነዘርባትን ተደጋጋሚ ዛቻ የፀጥታው ምክርቤት ሊመለከት ይገባል ስትል ኢትዮጵያ አሳሰበች

ዮሐንስ አንበርብር

ቀን: September 11, 2024

የግብፅ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የኃይል ዕርምጃ ለመውሰድ በተደጋጋሚ የሚሰነዝረውን ዛቻ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሊመለከተው ይገባል ስትል ኢትዮጵያ አሳሰበች። 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዩ አጽቀ ሥላሴ (አምባሳደር) ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ጷጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በላኩት ደብዳቤ፣ ግብፅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር በመጣስ በኢትዮጵያ ላይ የኃይል ዕርምጃ የመውሰድ ተደጋጋሚ ዛቻ እየሰዘረች ነው ብለዋል። የግብፅ መንግሥት ከሳምንት በፊት ለፀጥታው ምክር ቤት በላከው ደብዳቤ ላይ ተመሳሳይ ዛቻ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደምም የግብፅ ባለሥልጣናት ተመሳሳይ ዛቻ ያዘሉ መልዕክቶችን በመገናኛ ብዙኃን ሳይቀር እንዳስተላለፉ ሚኒስትሩ ለፀጥታው ምክር ቤት በላኩት ደብዳቤ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ግብፅ የተመድን ቻርተር በመጣስ በተደጋጋሚ የምታስተላልፈውን ዛቻ የፀጥታው ምክር ቤት ሊያስተውለው እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ታዬ አጽቀ ሥላሴ (አምባሳደር) በላኩት ደብዳቤ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር መሠረት አገራዊ የልማት ፕሮጀክቶቿን በመጠበቅ የአገሪቱን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ በፅናት እንደምትሠራ አስታወቀዋል።

የግብፅ መንግሥት ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ባስገባው ደብዳቤ፣ በኢትዮጵያ ላይ ያቀረባቸውን ክሶች የተለመዱና መሠረት የሌላቸው እንደሆኑ በመግለጽ ያጣጣሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ ግብፅ የተለያዩ ጥሰቶችን መፈጸሟን ብትቀጥልም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ በሦስቱ አገሮች የተደረሰውን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረጓን አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውኃ ፍሰትን የሚያረጋግጡ ተጨማሪ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ጥሩ ጉርብትና ማሳየቷንም ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹ግብፅ ጠበኛ አካሄዷንና ምክንያታዊ ያልሆኑ ጥያቄዎቿን በመተው፣ ተቀባይነት ያለው ዓለም አቀፍ የሕግ መርሆዎችን መተግበር አለባት፤›› ያሉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚነሱ ልዩነቶችን በእውነተኛ ድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆኗንም አስገንዝበዋል።

የዓባይ ወንዝ ተጋሪ አገሮች እ.ኤ.አ. በ2010 በኡጋንዳ ኢንቴቤ ተስማምተው የፈረሙት የዓባይ ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ፣ ከወንዙ ተጋሪ አገሮች መካከል ስድስቱ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶቻቸው አፅድቀው፣ ለአፍሪካ ኅብረት ሲያስገቡ ተፈጻሚ መሆን የሚጀምር መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ታዬ አጽቀ ሥላሴ (አምባሳደር)፣ ባለፈው ሰኔ ወር ስድስት አገሮች ማዕቀፉን አፅደቀው በአፍሪካ ኅብረት ያስቀመጡ በመሆኑ፣ የትብብር ማዕቀፉን ወደ ትግበራ እንደሚገባና የዓባይ (ናይል) ተፋሰስ ኮሚሽን እንደሚቋቋም አስታውቀዋል። በመሆኑም ግብፅ ይህንን የትብብር ማዕቀፍ እንድታፀድቅ ጠይቀዋል። 

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚነሱ ልዩነቶችን በእውነተኛ ድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን የጠቀሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ልዩነት በአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና አልያም በሚቋቋመው የዓባይ ተፋሰስ ኮሚሽን አማካይነት መደራደር እንደምትችል አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የማልማት መብት እንዳላት የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ግብፅ በዚህ ጉዳይ ላይ ያላትን ልዩነት ወደ ተመድ የፀጥታ ምክር ቤት መውሰዷ ተገቢ እንዳልሆነም ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የወሩ ፕሬዚዳንት የሆኑት የስሎቬኒያው ሳሙኤል ዛቦጋር (አምባሳደር)፣ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ ግብፅ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ለፀጥታው ምክር ቤት ስላስገባችው ደብዳቤና በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የሚታየውን የፖለቲካ ውጥረት አስመልክቶ፣ የፀጥታው ምክር ቤት ይወያይበት እንደሆነ ተጠይቀው ነበር።

የግብፅ ደብዳቤ እንደደረሳቸው የገለጹት የፀጥታ ምክር ቤቱ የዚህ ወር ፕሬዚዳንት የሆኑት ሳሙኤል ዛቦጋር (አምባሳደር)  በሰጡት ምላሽም፣ የግብፅ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ጠቁመው፣ ነገር ግን ጉዳዩ በአኅጉር ደረጃ እየታየ በመሆኑ፣ የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት እንደማይገባበት ገልጸዋል።