ዜና
እነ ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ክስ ተመሠረተባቸው

ታምሩ ጽጌ

ቀን: September 11, 2024

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የተላለፉ ውሳኔዎችና ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ያካሄደው የኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ምርጫ እንዲታገድ በቀረበው የፍትሐብሔር ክስ መሠረት በፍርድ ቤት ዕግድ ተሰጠ፡፡

በከሳሾች አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን በቀረበው የፍትሐብሔር ክስ አቤቱታ፣ ክስ የቀረባበቸው፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ (ዶ/ር) አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ ኤደን አሸናፊ (ዶ/ር)፣ አቶ ዳዊት አስፋውና አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ በዋናነት የቀረበባቸው ክስ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 154 እና 205 ድንጋጌዎችን በመተላለፍ፣ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ኮሚቴን ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፋቸውና ሕገወጥ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ምርጫ አካሄደዋል በሚል ነው፡፡

በመሆኑም ተከሳሾች ባደረጉት ሕገወጥ ጠቅላላ ጉባዔ የተላለፉ ውሳኔዎች፣ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ምርጫ እንዲታገድ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የክስ አቤቱታ ቀርቧል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሁሉም ንግድ ባንኮች ያለው ተቀማጭ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ዕግድ እንዲሰጥበትም ከሳሾች ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

የክስ አቤቱታውን የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍትሐብሔር ጊዜ ቀጠሮ ችሎት፣ በከሳሾች የተጠየቀውን ዕግድ ተቀብሎ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሁሉም ባንኮች ያለው ሒሳብ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ እንዳይንቀሳቀስና ግንቦት 6 እና ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቦርድ ምርጫ ጋር ተያይዞ የተላለፉ ውሳኔዎችም ታግደው እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ክሱ ፍርድ ቤቶች መደበኛ ሥራ ሲጀምሩ የሚንቀሳቀስ መሆኑም ታውቋል፡፡