ዜና
የሕወሓትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች በፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ እየተወዛገቡ ነው

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: September 11, 2024

‹‹የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንዲፈርም የተላከው ልዑክ ያልተወያየንበትን ስምምነት ፈጽሟል››

ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)

‹‹ተኩስ የማስቆም ኃላፊነታችንን ብቻ ነው የተወጣነው››

አቶ ጌታቸው ረዳ

‹‹ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተለያዩ መዋቅሮች ላይ የሚያደርገውን ምደባ ማቋም አለበት››

ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ

‹‹የሚደረጉ የመንግሥት የመዋቅር ለውጦች ተጠናክረው ይቀጥላሉ››

አቶ ጌታቸው ረዳ

በልዋም አታክልቲ

የሕወሓትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመሩትን ንትርካቸውን በመቀጠል፣ አሁን ደግሞ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ላይ መወዛገብ ጀመሩ፡፡ የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ፕሪቶሪያ የተላከው ልዑክ ያልተወያዩበትን መስማማቱን ሲገልጹ፣ ልዑኩን የመሩት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ልዑኩ ወደ ፕሪቶሪያ የሄደው ስለመንግሥትነት ጉዳዮች ለመወያየት ሳይሆን ተኩስ ለማስቆም መሆኑንና በዚያው መሠረት ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሕወሓት ስምምነቱን እንዲፈርሙ የመረጣቸው ልዑካን ስህተት መፈጸማቸው የተናገሩት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ በዚህም ምክንያት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት መጀመር የነበረበት ፖለቲካዊ ውይይት እስካሁን አለመጀመሩንና የክልሉም ሉዓላዊነት አለመረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በበኩላቸው ሰሞኑን ለርዕዮት ሚዲያ እንደገለጹት፣ በወቅቱ ስምምነቱን እንዲፈርም የተላከው ልዑክ በስምምነቱ ዙሪያ ሙሉ ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋለወ፡ ይህንንም ለአሜሪካ መንግሥት፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ለአፍሪካ ኅብረት በደብዳቤ መገለጹን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን፣ ‹‹ስምምነቱን ለመፈራረም ወደ ፕሪቶሪያ የሄድነው ስለመንግሥትነት ጉዳዮች ለመወያየት ሳይሆን፣ ተኩስ ለማስቆም ነበር፡፡  ይህንንም የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በደንብ ያውቃል፤›› ብለዋል፡፡

ወቅታዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ የመፍታት ጉዳይ ከጦርነቱ በኋላ ብቻ ሳይሆን ከጦርነቱ በፊትም የነበረ የድርጅቱ አቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

የሰላም ጉዳይ በዋነኝነት ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው እንደሆነ ገልጸው፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መቋጨቱን አስታውሰዋል። ይሁንና በወቅቱ ስምምነቱን እንዲፈርም የተላከው ልዑካን ቡድን ከስምምነት ሊደርስባቸው የማይገቡ ጉዳዮች ላይ በመስማማቱ ትልቅ ስህተት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ ልዑኩ ተኩስ እንዲቆም የመደራደር ኃላፊነት ቢሰጠውም የውሉን አቅጣጫ የመቀየር መብት አልተሰጠውም ሲሉ አስምረዋል፡፡

የውሉን አቅጣጫ ከቀየሩት ጉዳዮች መካከል ጊዜያዊ አስተዳደሩ በፌደራል መንግሥት ሥር እንዲተዳደር የወጣው ደንብ ነው ያሉት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህ በፍፁም ያልተስማማንበት ብቻ ሳይሆን ያልተወያየንበትም ጭምር ነው፤›› ብለዋል፡፡  

‹‹የፌደራል መንግሥት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበት አሠራር ቢኖርም፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚህ ደረጃ ለፌደራሉ መንግሥት ተጠሪ እንዲሆን የተስማሙበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፣ አፈጻጸም ላይም ችግር እየፈጠረ ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አፈጻጸሙ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ቅርርብ እንዲፈጠርና ከዚህ ቀደም የነበሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ በማለም የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴም ስምምነቱ ላይ የሌሉ ውሳኔዎችን እያሳለፈ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

በጦርነቱ ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ምርኮኛ ወታደሮችም በክልሉ የፀጥታ ኃይል ሥር ምርመራ ሲካሄድባቸው መቆየቱን የገለጹት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ሰፊ ምርመራ ከተካሄደ በኋላ 400 ገደማ የሚሆኑት በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተወንጅለው በፀጥታ ኃይሉ ሥር እንዲቆዩ ቢደረግም፣ ያለ ምንም ተጠያቂነት እንዲለቀቁ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ሒደቱ ስህተት መሆኑንና በምዕራብ ትግራይ ግፍ የፈጸሙ አካላትም በስምምነቱ መሠረት እስካሁን ተጠያቂ አለመደረጋቸውን ነው ያከሉት፡፡ ጉዳዩን በሚመለከት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል የተሰጠው ምላሽ የወታደሮቹ መዝገብ ወደ ፌዴራሉ መንግሥት ተልኮ በፌዴራል ደረጃ ይታያል የሚል እንደሆነ ጠቁመው፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተጠያቂነትን ጉዳይ ችላ እንዳለው ማሳያ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሕወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩን የማፍረስ ዓላማ እንዳለው በሌላኛው ቡድን በኩል በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ ‹‹አሥር ጊዜ የውሉን ጉዳይ የሚያነሱት ውጤት ማምጣት ስላቃታቸው እንደሆነ እንገነዘባለን፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ እየተደረገ ያለው እልህን ብቻ ማዕከል ያደረገ አካሄድ ተቋማዊ አሠራርን የሚያፈርስ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ከዚህም ባለፈ አቅማችን እንዲዳከም እያደረገን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከ14ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ውዝግብ አስታውሰው፣ ድርጅታዊ ጉባዔ ማካሄድ ከጦርነት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለና ነገር ግን ጦርነት ሊቀሰቀስ ነው በሚል ሐሰተኛ ዘመቻ ሕዝቡ እንዲሸበር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ 

‹‹እኛ የኤርትራ መንግሥትን ጨምሮ ከየትኛውም አካል ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የለንም፡፡ እልህን ብቻ ማዕከል ያደረገ አካሄድ ተቋማዊ አሠራርን ከማፍረስ ባለፈ አቅማችንንም እያዳከመ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ተነጋግረህ ካልተስማማህ በሌላ ጊዜ እንገናኝ ብለን ትለያያለህ፡፡ ይህ ደግሞ ከሌላ ዙር ውጊያ በኋላ የሚሆን ነው፡፡ ስለዚህ ተኩሱን የግድ ማስቆም ነበረብን፡፡ የፌዴራል መንግሥት ተወካዮች ብዙ ነገሮችን ሊጠይቁን ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ደግሞ በቋሚነት ነው ተኩስ ማስቆም ያለብን በማለት ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አልተወያየንም፤›› ሲሉ የነበረውን ሁነት አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል የፕሪቶሪያ ስምምነት በተፈረመበት ወቅት የፌዴራል መንግሥት በጦርነቱ የበላይነት እንዳለው ያምን በነበረበትና መቀሌን ከብቤያለሁ እያለ በነበረበት ወቅት፣ እንዲሁም ውጊያ ባልተቋረጠበት ሁኔታ ለድርድር መቀመጣቸው እጅግ በውስብስብ ሁኔታዎች የታጀበ እንደነበር የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የፌደራል መንግሥት ሕወሓት እጅ እንዲሰጥ ለማድረግ ለድርድር መቅረቡን አስታውሰዋል፡፡ ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ‹‹እጅ ስጡ፣ እጅ መስጠት የዓለም መጨረሻ አይደለም›› ያሉ ቢሆንም፣ ብዙ ውጣ ውረዶች መታለፍ እንደነበረባቸውና ነገር ግን ተኩስ ለማስቆም መደረግ ወይም መታለፍ ያለባቸው ነገሮች በሙሉ መደረጋቸውን አብራርተዋል፡፡ ሁኔታው ካለፈ በኋላ የሚብጠለጠለውን ያህል ቀላል እንዳልነበር ጠቅሰው፣ ለልዑኩ የተሰጠውን ተኩስ የማስቆም ኃላፊነት ብቻ መወጣቱን አክለዋል፡፡

‹‹ተኩስ ለማስቆም ትጥቅ አውርዱ ከተባልን እሺ ማለት እንጂ አይ ትጥቅ አላረግፍም ብለህ ተኩስ ልታስቆም አትችልም፡፡ እያንዳንዱ ነገር ሒደት አለው፣ የሠራዊታችንን አቅምም መዝነን የግድ ተኩስ ማስቆም ነበረብን፤›› ብለዋል፡፡ 

ክፍፍሉ ከወራት በፊት መሰማት የጀመረው ሕወሓት 14ኛውን ድርጅታዊ ጉባዔ ተከትሎ ለሁለት የመከፈሉ ጉዳይ አደባባይ ከወጣ ሰነባብቷል፡፡ ድርጅቱ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ከጉባዔው ራሳቸውን ያገለሉትን አባላቱን ሲያግድ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በበኩሉ ሹም ሽሮችን ማካሄዱን ቀጥሏል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የፀጥታ ዘርፍ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ የተለያዩ መዋቅሮች የሚያደርጋቸውን የምደባ ለውጦች ማቆም አለበት በማለት ከሁለት ቀናት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሳስበዋል። ምደባዎችንና ሽግሽጎችን ማቆም የሚያስፈልገው፣ በክልሉ ያለው ፖለቲካዊ ችግር እየተባባሰ በመሄዱ እንደሆነም ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ በክልሉ የተጀመሩ ከላይኛው እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር የሚደረጉ ለውጦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመናገር፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የፀጥታ ዘርፍ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ሌተና ጄነራል ታደሰ ወረደ ‹‹ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ የተለያዩ መዋቅሮች የሚያደርጋቸውን የምደባ ለውጦች ማቆም አለበት፤›› በማለት ለሰጡት ማሳሰቢያ ምላሽ ሰጥው፣ ይህ ማለት ግን ሁሉንም አመራር በአዲስ መተካት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ባለፉት ሳምንታት ሲካሄዱ የቆዩት ሕዝባዊ ስብሰባዎችም የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ መልኩ እንደሚቀጥሉ ጠቁመው በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ግን የፀጥታ ችግሮች እንደነበሩ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

ሌተና ጄኔራል ታደሰ አክለውም ፖለቲካዊ ችግሩ በዚህ ከቀጠለ በክልሉ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አካባቢ ካሉ የትግራይ ተወላጆች እጅ ወጥቶ ለሦስተኛ ወገን መጠቀሚያና መግቢያ ቀዳዳ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸውም ጠቁመዋል። በክልሉ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሠልፍ ማድረግ ጉዳት አለው ያሉት ሌተና ጀኔራል ታደሰ፣ ሠልፍ ማድረግ ታግዶ እንደሚቆይም ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ክልከላ ባለበት እንዲቆይ የተወሰነው አምባገነናዊ አካሄድን ለመከተል ሳይሆን፣ እየተባባሱ የመጡትን ችግሮች ለማርገብ እንደሆነም አክለዋል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በተለይም ከ14ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በኋላ ከሕወሓት ጋር የገባበትን ውዝግብ ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች ያሉ አመራሮችን ምደባ ለውጥ ማካሄዱ የሚታወስ ሲሆን ጄኔራሉ በበኩላቸው፣ ‹‹በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል የሚደረጉት ሹም ሽሮች ሕገ መንግሥቱን የሚጥሱና ያለውንም ክፍፍል የሚያባብሱ ናቸው፡፡ በሕዝቡ ላይ ሥጋት እየፈጠሩ ነው፤›› ብለዋል።

ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ በርካታ ስብሰባዎች እየተካሄዱ እንደሆነ የገለጹት የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊው፣ ማንኛውም ስብሰባ ወደ ፀጥታ ችግር የሚያመራ መሆን እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠረው ችግር ፖለቲካዊ እስከሆነ ድረስ ፖለቲካዊ መፍትሔ ብቻ ነው የሚሻው ብለው፣ ስም በማጥፋት ዘመቻም ሆነ በሌላ አላስፈላጊ መንገድ የሚፈታ እንዳልሆነ በመገንዘብ ከሕገወጥ አካሄዶች መቆጠብ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል፡፡  

‹ለሁለት የተከፈሉትን የሕወሓት አመራሮች በተቻለ መጠን ለማስማማት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸው፣ ጥረቱ ካልተሳካ ግን ልዩነታቸውን አክብረው በሕጉ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው አካሄድ ግን ቀይ መስመርን ማለፍ ስለሚሆን መገታት አለበት ሲሉም አስጠንቅቀዋል። ከዚህ ባሻገር በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ከወራት በፊት የተጀመረውን ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ተግባር በሚመለከት፣ ‹‹የትግራይና የአማራ ሕዝቦችን ዘላቂ ግንኙነት የሚጎዳ ማንኛውም እንቅስቃሴ መቆም አለበት፤›› በማለት ያስገነዘቡት ሌተና ጄኔራል ታደሰ፣ መሰል እንቅስቃሴ ትርጉም አልባ በመሆኑ ካለፈው መማር እንደሚገባ አሳስበዋል። ‹‹በጠመንጃ የሚወሰድ መሬትም ሆነ የሚቀየር ድንበር የለም፡፡ ስለሆነም በአማራ ክልል በኩል ያሉ ታጣቂዎች ከድርጊታቸው ይቆጠቡ፤›› ብለዋል፡፡

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሒደት ከወራት በፊት የተጀመረ ቢሆንም፣ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ እንዲያስጠብቅ ኃላፊነት የተሰጠው የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ተፈናቃዮች የደኅንነት ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን ሕወሓትና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በተደጋጋሚ ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል። የአማራ ክልል በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።