ዜና የቤቶች ኮርፖሬሸን ቢሮ አሰጣጥ ፍትሐዊነት የጎደለው ነው ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ አቀረቡ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: September 11, 2024

‹‹እጥረት የፈጠረው ቅሬታ ነው››

ፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕውቅና አግኘተው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል፣ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በዝቅተኛ የኪራይ ተመንና በነፃ እያቀረበ ያለው የቢሮ አሰጣጥ ግልጽ ያልሆነ፣ ፍትሐዊነት የጎደለውና መፍትሔ የሚሻ ነው ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ እናት ፓርቲ፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ አረና ትግራይ ለዴሞክራሲ ፓርቲና ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያላቸው ፓርቲዎች በተለያዩ መንገዶች እየተስተናገዱ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ ግልጽ ያልሆነና መሥፈርቱ የማይታወቅ አሠራር ባሉት መንገድ፣ ፓርቲ እየተመረጠ እንደሚሰጥ፣  ምርጫ ቦርድ በዝቅተኛ ዋጋ ቢሮ እንዲያገኙ የድጋፍ ደብዳቤ ቢጽፍም የአንዳድ ፓርቲዎች ጥያቄ ለዓመታት መልስ እንዳላገኘ ተናግረዋል፡፡

የአረና ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አሥራት በሰጡት አስተያየት፣ ፓርቲያቸው ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ ቢሮ በዝቅተኛ ኪራይ ለማግኘት ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም፣ እስካሁን ምላሽ አላገኘም ብለዋል፡፡ አረና ለመንግሥትና ለብልፅግና ፓርቲ ጉዳዩን በደብዳቤ ቢያሳውቅም ቤቶች ኮርፖሬሽን መልሰ ሊሰጥ አልቻለም ሲሉም አስረድተዋል፡፡

አረና በታኅሳስ 2015 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ፣ በውጭ አገር በስደት ከነበሩበት ወደ አገር ቤት ለመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር በአገር አቀፍ ደረጃ የፋይናንስ፣ የጽሕፈት ቤትና የተሽከርካሪ ድጋፍ ሲደረግላቸው፣ አረና ምንም ዓይነት ድጋፍ አለማግኘቱ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሶ በተደጋጋሚ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጠው ማሳወቁን ከተላከው ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የፓርቲው የሥራ ኃላፊዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በገዥው መንግሥት የድጋፍ ደብዳቤ አማካይነት ቢሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡  አክለውም መንግሥት ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር፣ ሁሉም ፓርቲዎች እኩል እንዲስተናገዱና የቢሮ ይሰጠን ጥያቄያቸውን ምላሽ እንዲያገኝ ጠይቀዋል፡፡

የነፃናት እኩልነት ፓርቲ የአቅም ግንባታና አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ሙባረክ ረሻድ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ፓርቲው ከተመሠረበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ማመልክቻና አቤቱታ ቢያስገባም ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

በየሳምንቱ ረቡዕ ወደ ቤቶች ኮርፖሬሽን ጉዳዩን ለማስፈጸም ይሄዱ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ሙባረክ፣ ሁልጊዜም ወረፋ ጠብቁ ቢባልም በጊዜ ሒደት ግን አዲስ የሚመሠረቱ ፓርቲዎች ቢሮ ሲያገኙ፣ ፓርቲያቸው ግን ምላሽ ማጣቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹ምልጃ በሚመስል ሁኔታ በተቋምም በግልም ቢሮ እንዲሰጠን ለመጠየቅ ብንሞክርም፣ አንዳንዶች በግልጽ በምን መሥፈርት እየተሰጣቸው እንዲሆን ባናውቅም፣ የእኛ ፓርቲ መልስ የሚሰጠው ጠፍቷል፤›› ብለዋል፡፡

ፓርቲው ቢሮ ባለማግኘቱ የተነሳ የሚያቅዳቸውን ሥራዎች በልኩ ለማከናወን መቸገሩን፣ ቢሮ ከግለሰቦች ለመከራየት በሚፈልግበት ወቅት ደግሞ ለፓርቲ አናከራይም የሚል ሥጋት መኖሩን አስረድተዋል፡፡

አቶ ሙባረክ መንግሥት የዴሞክራሲ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ከፈለገ፣ ወደ ጫካ የገቡ ፓርቲዎች ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለሱ አመቺ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይገባል ብለዋል፡፡ በተቃራኒው በፖለቲካ ሜዳው ጋባዥ ምኅዳር ከሌለ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሒደትን አዳጋች ያደርገዋል ሲሉ አክለዋል፡፡

በፋይናንስ ችግር የተነሳ ፓርቲያቸው በአዲስ አበባ የነበረውን የዋና መሥሪያ ቤትና የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ቢሮን ወደ አንድ በማጠፍ፣ በአንድ ማዕከል ብቻ እንዲወሰን መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የእናት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ በበኩላቸው፣ የቤቶች ኮርፖሬሽንን ከሦስት ዓመታት በላይ ‹‹ደጅ ጠንተናል›› ይላሉ፡፡ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ከተማፅኖ ውጪ ምላሹ አጥጋቢ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ በተለያየ መንገድ በተደረገ ጥረትና ቤቶች ኮርፖሬሽን ውስጥ ከሚገኙት አቶ ጌቱ ዘውዴ የተባሉ የሥራ ኃላፊ ጋር በተደረገ ንግግር፣ ለቢሮ የማይሆን ነገር ግን ለዕቃ ማስቀመጫ ሊያገለግል የሚችል ሃያ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቤት ጦር ኃይሎች አካባቢ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የተገኘው ቤት ለምንም ዓይነት የቢሮ አገልግሎት፣ ለመሰብሰቢያ ወይም ለመሥራት የማይሆንና ጠባብ፣ ለትራንስፖርት አመቺ ያልሆነ ቦታ ላይ መሆኑን አቶ ጌትነት አስረድተዋል፡፡ ‹‹በሕይወቴ እንዲህ ዓይነት አድካሚ ጉዳይ አስፈጽሜ አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም የቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚን በቢሮቸው ከማግኘት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማግኘት ይቀላል ይላሉ፡፡

የቤቶች ኮርፖሬሽን ቤት አለመስጠቱ ብቻ ሳይሆን ለቢሮ ኪራይ ሕንፃና ክፍሎችን የሚያከራዩ ባለንብረቶች ለፖለቲካ ፓርቲ ለማከራየት ፍላጎት እንደሌላቸው፣ ሲያከራዩም በሦስትና አራት እጥፍ ማሳደጋቸው ችግሩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ ሰዎች ቤቶቻቸውን ቢያከራዩ በመንግሥት ዕርምጃ ይወሰድብናል ብለው ስለሚፈሩ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ለማከራየት እምብዛም ፍላጎት አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

ይህ አጠቃላይ የሥርዓት ችግር ነው የሚሉት አቶ ጌትነት፣ የሚሰጠው ቤት ለመዝናኛ ሳይሆን እንደ ብልፅግና ፓርቲ ሁሉ መንግሥት ለመሆን የሚያበቁ ሥራዎችን ለማከናወን በመሆኑ መልስ ሊያገኝ እንደሚገባና የፍትሐዊነት ጥያቄ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ክልላዊ ፓርቲ የሆነው ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በሚንቀሳቀስበት ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ ምንም ዓይነት ድጋፍ አለማግኘቱን የገለጹት የፓርቲው ሊቀመንበር መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ፓርቲያቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ምንም ዓይነት ምላሽ አለመኖሩንና በክልሉ የተፎካካሪ ፓርቲን ጥያቄ መስማት የማይፈልጉ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢሕአፓ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት በበኩላቸው፣ እንደ ማንኛውም ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘ ፓርቲ ሊደረግላቸው የሚገባውን ድጋፍ ለማግኘት ወደ ቤቶች ኮርፖሬሽን ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት አድካሚ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ይህ ምላሽ የማጣት ችግር ከሥርዓት ጋር የተያያዘ ነው የሚሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ የመንግሥት ለውጥ በተደረገበት ወቅት ወደ አገር ቤት ግቡ ተብለው ከተጠሩት ፓርቲዎች መካከል ግንቦት 7፣ ኦነግና ሌሎችም ፓርቲዎች ቢሮ ቢያገኙም  ኢሕአፓ ግን አለመስተናገዱን ተናግረዋል፡፡

ኢሕአፓ እንደ ማንኛውም ፓርቲ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ቢሮ ተከራይቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን፣ ለዚህ ችግር በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ መጥፋቱን አስረድተዋል፡፡

ከ50 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የዘለቀው ኢሕአፓ ቢሮ ሳይሰጠው፣ ትናንት የተመሠረቱ ፓርቲዎች ቢሮ ማግኝታቸው ግርምት የሚያጭር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሚዲያ ተቋማት ቢሮ ለመከራየት በጣም አዳጋች መሆኑን፣ የሚያከራዩ አካላትንም የመንግሥት ሰዎች እንደሚያስፈራሯቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ብልፅግናና ኢሕአፓ የሚለያዩት የመንግሥትን ሥልጣን በመያዝና ባለመያዝ እንጂ በምርጫ ቦርድ ሕግ መሠረት ሁሉም እኩል ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ገዥው ፓርቲ ባለው ጡንቻ አጎብዳጅ ለሆኑ ፓርቲዎች የሚያደርገውን ድጋፍ ኢሕአፓ የሕዝብ ፓርቲ በመሆኑ በዚያ መልኩ አጎብድዶ ሊቀበል አይችልም፤›› ብለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩና በአዲስ አበባ ከንቲባ አማካይነት ቢሮ የሚያገኙ ፓርቲዎች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፣ ‹‹የፍትሐዊነት ጥያቄው ይመለስ፣ የአገር ሀብት እኩል በሆነ መንገድ ክፍፍል ይደረግ፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የቤቶች ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊ፣ ተቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን አገራዊ ሚና የአባላት ብዛትና የፓርቲ ቁመና ግምት ውስጥ በማስገባት ይሰጣል እንጂ፣ አገር ውስጥ ላሉት ከመቶ በላይ ፓርቲዎች ለቢሮ የሚሆን ቤት በአንድ ጊዜ ለማቅረብ ኮርፖሬሽኑ የሀብት ውስንነት አለበት ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም እያገኙና  ጥያቄያቸው እየተመለሰላቸው መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ አንዳንድ ፓርቲዎች እንደተመሠረቱ ወዲያውኑ ቢሮ ማግኘት ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡

እስካሁን ቢሮ አላገኘሁም የሚል ቅሬታ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አለመምጣቱን ገልጸው፣ ኮርፖሬሽኑ ማኅበራዊና አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፓርቲዎችና የተራድኦ ድርጅቶች ያለ ምንም አድልኦ ቤት እንደሚያቀርብ፣ አሁን ሊነሳ የሚችለው ቅሬታ እጥረት የፈጠረው መሆኑን አክለዋል፡፡ በሁሉም ጥያቄ በአንድ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት ባይቻልም በሒደት ግን ጥያቄያቸው ይመለሳል ሲሉ አስረድተዋል፡፡