የሉዓላዊነት ቀን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ‹‹ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት›› ቀን ሲዘከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቅሉ ይታያሉ (ፎቶ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት)

ፖለቲካ

ዮናስ አማረ

September 11, 2024

‹‹የሉዓላዊነት ቀን›› በሚል መሪ ቃል በተዘከረበት ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ብዙ ዓይነት መርሐ ግብሮች በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መሪነት ሲካሄዱ ውለዋል፡፡ መንግሥት ስለአገር ሉዓላዊነት ምንነት ያለው አቋም ምን እንደሚመስል በእነዚህ መርሐ ግብሮች ተንፀባርቀዋል፡፡ በሌላ በኩል አሁን ኢትዮጵያ ገጥሟታል ተብለው በሚታሰቡ የሉዓላዊነት ፈተናዎች ላይ መንግሥት አቋሙን ሲያንፀባርቅ የታየበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ከሉዓላዊነት ቀን ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ ቀደም ብሎ በተከበረው የምሥራቅ ዕዝ ምሥረታ 47ኛ ዓመት በተከበረበት ወቅትና በየአጋጣሚው በሚካሄዱ ወታደራዊ ክንዋኔዎች በቅርብ ጊዜያት ጠንከር ያሉ መልዕክቶች የሚተላለፉባቸው ወታደራዊ ሠልፎች፣ ትርኢቶች፣ ልምምዶችና የከፍተኛ አመራሮች ንግግሮች በርከት ብለው ሲስተዋሉ ቆይተዋል፡፡

የሉዓላዊነት ጉዳይ ከየት ወዴት? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሉዓላዊነት ቀን ሲዘከር ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ
ማርሻል ብርሃኑ ጁላና ከአገር መከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ ጋር (ፎቶ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት)

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም የፖለቲካ ለውጥ ከመጣ ጀምሮ ያስተናገደቻቸው ውስጣዊና ውጫዊ ቀውሶች የሚታወቁ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት የሉዓላዊነት ሥጋት አለባት ወይ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ ውኃ እንደማያነሳ ይታመናል፡፡ በአገር ውስጥ በሰላምና ፀጥታ መደፍረስ ስትፈተን የቆየችው ኢትዮጵያ ከባባድ ጦርነቶችንም እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች ጀምሮ ከሶማሊያ ጋር የገባችበት የዲፕሎማሲ ፍጥጫ አሁንም ድረስ አልበረደም፡፡ በሱዳን ድንበር በኩል ሲያገረሽ የቆየው የአልፋሽቃ እርሻ መሬት ይገባኛል ውዝግብ በእንጥልጥል ላይ ይገኛል፡፡ በደቡብ ሱዳን በኩል ታጣቂዎች ድንበር አልፈው በርካታ ኪሎ ሜትር ዘልቀው ገብተው የወርቅ ማዕድን ማውጫዎችንና ከተሞችን ጭምር መቆጣጠራቸው የሚወራበት አጋጣሚ ተደጋግሞ ተከስቷል፡፡ በሶማሊያ ድንበር በኩል ደግሞ የአልሸባብ ሽብር ቡድን ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት ተደጋግሞ የተከሰተበት አጋጣሚ ከመፈጠሩ በተጨማሪ፣ በአገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የሽብር ክንፎች ጋር የተሳሰረ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው መባሉ ከባድ ሥጋት አጭሮ ነው የቆየው፡፡

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ የኤርትራ ሠራዊት በጦርነቱ የመሳተፉ ጉዳይ ደግሞ ስለአገር ሉዓላዊነት ምንነት ብቻ ሳይሆን፣ ስለሉዓላዊነት ጥሰትና መከበር አጀንዳ ጠንካራ ክርክሮች እንዲካሄድ በር የከፈተ ጉዳይ ነበር፡፡ የአገር ሉዓላዊነት የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ከውጭ መንግሥት ጋር አብሮ የራሱን ሕዝብ አስወጋ የሚለው ውንጀላ ቢሰማም፣ በዚያው ልክ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገር ሮኬት በመተኮስ ጭምር ጦርነቱን ቀጣናዊ ለማድረግ ተፋላሚ ኃይሉ ሕወሓት ስለመሞከሩ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ከውጭ መንግሥታት ጋር በተደረጉ ውሎች፣ በተፈጠሩ አጋርነቶች፣ ግንኙነቶችና አለመግባባቶች ላይ ተመርኩዞ በሉዓላዊነት ጉዳዮች ላይ ብዙ ጥያቄዎች እንደተነሱ ነው የታለፈው፡፡ ከሰሞኑ በተከበረው የሉዓላዊነት ቀን ላይ በተካሄዱ መድረኮች በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ የተነሱ ሉዓላዊነትን የተመለከቱ ሐሳቦችም እንዲሁ ትኩረት የሚስቡ ነበሩ፡፡ ጉዳዩ ባለፉት ዓመታት ከሳበው ትኩረትና የመከራከሪያ አጀንዳ ከሆነበት አጋጣሚ በላይ በአዲሱ 2017 ዓመትም ልዩ ቦታ የሚሰጠው የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ እንደሚቀጥል ብዙ ጠቋሚ ምልክቶች ታይተዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) በሉዓላዊነት ቀን በተካሄደ የፓናል ውይይት ላይ ስለሉዓላዊነት ምንነት ብቻ ሳይሆን፣ ሉዓላዊነትን ማስጠበቂያ ነው ስላሉት ስለሶፍትና ሀርድ ፓወር ጉዳይ ሰፊ ትንተና አቅርበው ነበር፡፡ ሶፍት ፓወር በሚለው ምድብ በፊልም፣ በሙዚቃ፣ በባህልና በሌሎችም የገጽታ ግንባታ ሥራዎች የሚደረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራዊ ተፅዕኖና ቅቡልነትን የማሳደጊያ መንገድ እንደሆነ አውስተዋል፡፡ ሀርድ ፓወር በሚለው ወገን ደግሞ ወታደራዊ ጡንቻን ስለማፈርጠም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ኢትዮጵያ ልትከተለው ስለሚገባ የተፅዕኖ አድማስ ማስፊያ መንገድ ምክረ ሐሳብ የሰጡት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ሁለቱንም ሶፍቱንም ሀርድ ፓወሩንም ደባልቆ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እሳቸው ስማርት ፓወር ሲሉ ያስቀመጡትን ሁለቱንም የቀየጠ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ተፅዕኖ መፍጠሪያ መንገድን ስለመጠቀም ያሳሰቡት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ‹‹ለሁሉም ማግጠጥም ልክ አይደለም በሁሉም ማፍጠጥም ልክ አይደለም፡፡ አንዳንዴ ለስለስ፣ እንደነገሩ ደግሞ አንዳንዴ ኮምጨጭ ማለት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ በሶፍት ፓወር የፈለገውን ያህል አቅም አንድ አገር ቢፈጥር በሀርድ ፓወር በኩል ተመሳሳይ ጠንካራ አቅም ካልገነባ የተሻለ ግንኙነትና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደማይችል በመጠቆም፣ ሁለቱንም በሚዛን አጣጥሞ ስለመጠቀም ሰፊ ትንተና አድርገዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተሩ በዚሁ የፓናል ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የምትወዛገብበትንና ሱዳን በኃይል ወራዋለች የሚባለውን የአልፋሽቃ መሬት በተመለከተ አስገራሚ ጉዳይ አንስተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት የሱዳን ኃይሎችን በማስታረቅና ለሱዳን ሰላም የተጫወቱትን ሚና በመጠቆም፣ በሱዳናዊያን ዘንድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝታ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወገናችን፣ ኢትዮጵያ ወዳጃችን በሚል በግብፅ የሚደረገውን ግፊት ሁሉ አልፎ ካርቱም ከተማን በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አስውቦ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሱዳን ሕዝብ ያደረገው የሞቀ አቀባበልን በቪዲዮ አስደግፈው አብራርተዋል፡፡  

በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ከ20 ዓመታት በፊት በድንበር ይገባኛል ውጊያ መደረጉንና ኢትዮጵያ መሬቱን መያዟን አስታውሰው፣ ነገር ግን ገፍተናቸዋል በሚል ኢትዮጵያዊያን በሒደት በሰላም ችግሩን በሰላም ወደ መፍታት እንደገቡ አስረድተዋል፡፡ ይህ ከሆነ ከጊዜ በኋላ ያን መሬት በቅርቡ ሱዳኖች እንደወረሩት፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ መሬቱን ለማስመለስ ኃይል ወደመጠቀም አለመግባቷን የታሰበበትና ታቅዶ የተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ሱዳኖች ወዲያው ወደ ጦርነት መግባታቸውን ያከሉት አምባሳደሩ በዚህ ጊዜ መሬቱን ይዞ ለመቆየት የተዳከሙ አቅም ያላቸው መሆኑን በማየት ኢትዮጵያ በጉልበት ወደ መውሰድ አለመግባቷን ተናግረዋል፡፡ በቀላሉ ኢትዮጵያ መሬቱን ልታስመልስ ብትችልም ሱዳኖቹ ሲረጋጉ በሰላም ተነጋግሮ ችግሩን መፍታት ይበጃል በሚል፣ ጉርብትናን ባስቀደመ መንፈስ ኢትዮጵያ በትዕግሥት እየተጠባበቀች መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

ይህን ጉዳይ ከዚህ ቀደምም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲናገሩት መደመጡ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ በሱዳን ጦር መጣሱና ድንበሯ መወረሩ የትግራይ ጦርነት ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ሲነገር የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጦርነት መነሳቱን ጠብቀው ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና ዳር ድንበሯን ለመጠበቅ የምትችልበት ሁኔታ መዳከሙን አይተው፣ ሱዳኖች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበትን የኢትዮጵያ መሬትን መውረራቸው ሲነገር የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ሱዳኖች ኢትዮጵያን ከጀርባ መውጋታቸውና ክህደት መፈጸማቸው በሰፊው ሲነገር የቆየ ጉዳይ ቢሆንም፣ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መሬቱን ለማስመለስ ሱዳኖቹ እስኪረጋጉ እየጠበቅን ነው የሚል መልስ ሲሰጡ እየተደመጠ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ እያከራከረ ያለ ጉዳይ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጠው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ነው ወይስ ለሱዳን መረጋጋትና የመደራደር አቅም መፈጠር የሚል መልስ ያጣ ክርክር መነሻ ሆኗል፡፡         

በኢትዮጵያ የአገር ዳር ድንበርና ሉዓላዊነትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ይህን መሰል ጥያቄ የተፈጠረው አንዴ ብቻ አለመሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በአንድ ወቅት የመተማ ከተማ ከንቲባ እንደመሰከሩትም ከሱዳን የተነሱ ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን አፈናቅለው መሬቱን ሲያርሱና የተዘራውን ሲሰበስቡ፣ ቦታው ድረስ የሄዱ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን አትንኳቸው የሚል ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረው ነበር፡፡ በቀድሞ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ዓባይ ፀሐዬ የሚመራ የባለሥልጣን ቡድን በኢትዮጵና በሱዳን አወዛጋቢ ድንበር ተገኝቶ ቦታው የሱዳኖች ስለሆነ ይውሰዱት አትንኳቸው የሚል ትዕዛዝ መሰጠቱን፣ በጊዜው የነበሩ የአካባቢው ባለሥልጣናት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የባድመ ወረራ በተፈጸመበት ወቅት የመጀመሪያዎቹን ድንበር ተሻጋሪ ትንኮሳዎች ሲመክቱ የነበሩ የአካባቢው ሚሊሻዎች የኤርትራ ሠራዊት በታንክ ታጅቦ ወረራ መፈጸሙን ጠቅሰው፣ ለትግራይ ክልል የዞንና የክልል አመራሮች በማሳወቅ ዕርዳታ መጠየቃቸው በጊዜው በነበሩ የፕሬስ ውጤቶች ተጽፏል፡፡ ይሁን እንጂ የጠየቁት ዕርዳታ ሳይላክ እነሱም አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን የአካባቢው ሚሊሻዎች ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ የሻዕቢያን ወረራ በስተኋላ ለመቀልበስ ብዙ ሺሕ ሠራዊት ሲመለመል፣ መሣሪያ ሲገዛ፣ ሥልጠና ሲሰጥም ከረመ፡፡ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ ነበር የሻዕቢያ ወረራ የተቀለበሰው፡፡

ይህ ሁሉ መስዋዕትነት ተከፍሎ ኢትዮጵያ ከወረራ ነፃ ብትወጣም፣ ነገር ግን በአልጀርስ የሰላም ስምምነት ስም ይግባኝ በሌለው የሄግ ፍርድ ቤት ዳኝነት እጅ ላይ ሉዓላዊነቷን የማረጋገጡ ዕጣ ፈንታ ተተወ፡፡ በጊዜው የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች አገሪቱ ልክ እንደ ዓድዋው ሁሉ ሉዓላዊነቷን የልጆቿን አጥንትና ደም ከስክሳ አስከበረች ብለው ሕዝቡን ማስጨረሳቸው ሲነገር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በሄጉ ፍርድ ቤትና በአልጀርሱ የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ በጦርነቱ ያገኘችውን ድል እንደተቀማች ነው ዛሬም ድረስ ክርክር ሲደረግ የቆየው፡፡ ኢትዮጵያ በጦር ሜዳ ከሻዕቢያ ወረራ ነፃ ብትወጣም፣ በሰላማዊ ሜዳ ግን ያን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለችበትን መሬት አሳልፋ መስጠቷ ታላቅ አገራዊ ፀፀት ፈጥሮ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬም ድረስ ለሚያገረሽ የድንበር ግጭት አገሪቱ እንድትጋለጥ ማድረጉ በሰፊው ይተቻል፡፡

የሉዓላዊነትና የዳር ድንበር ማስከበር ጉዳይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑ በሰፊው ተጽፎበታል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ጉዳይ እስከ መጨረሻው ዳር በማድረስ ረገድ ኢትዮጵያውያን ሁሌም ቢሆን ስብራትና ፀፀት ሲገጥማቸው መኖሩ ይተቻል፡፡ በአንፀባራቂ ጀግንነቱ የሚጠቀሰው የዓድዋው ትውልድ ከመረብ ምላሽ ብሎ የተወው ጉዳይ ዛሬም ድረስ አገሪቱን የሚከተል ችግር ሲፈጥር መቆየቱ ይወሳል፡፡ ኢትዮጵያን ከቅኝ ገዥዎች ሲታደግ የኖረው የቀደመው ትውልድ ከጎረቤት አገሮች ጋር አገሪቱ ዙሪያዋን የምትዋሰንባቸውን የድንበር አካባቢዎች በተመለከተ በሕግ የተደረገ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው መንገድ የድንበር ማካለል ሥራ ሳይሠራ በማለፉ፣ አገሪቱ በየጊዜው ከተለያዩ ጎረቤቶቿ ጋር ስትናቆር እንድትኖር የሚያደርግ ችግር ለትውልድ ማውረሱ ይነገራል፡፡

ከእነዚህ በይደርና በእንጥልጥል ተትተው በየጊዜው የሚያመረቅዝ ችግር ከፈጠሩ የሉዓላዊነት ጥያቄን ከሚያስነሱ የታሪክ አጋጣሚዎች፣ የአሁኑ ትውልድ በቂ ትምህርትና ተሞክሮ ቀስሟል ወይ የሚለው ጉዳይ ያጠያይቃል፡፡ ከሱዳን ጋር በተያያዘ የተፈጠረው የድንበር ይገባኛል ሽኩቻ በመንግሥት በኩል የተያዘበት መንገድ የቀደመው ትውልድ ከተከተለው መንገድ ጋር በተነፃፃሪነት እየቀረበ ነው፡፡  

የውጭ ግንኙነት ባለሙያው በለጠ በላቸው (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ያልተቋጨው የቤት ሥራ በሚለው የ2014 መጽሐፋቸው ላይ ኢትዮጵያዊያን ስለሉዓላዊነትና ዳር ድንበራቸው ቀናኢ የሆኑ ሕዝቦች መሆናቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ በዘመናቱ ለሉዓላዊነትና ለዳር ድንበር መከበር በርካታ ኢትዮጵያዊያን መስዋዕት ሲከፍሉ መኖራቸውንና ይህም እንደሚቀጥል ይገልጻሉ፡፡

‹‹ነገር ግን የኢትዮጵያን የግዛት ዳርቻ በተመለከተ ያለው ግንዛቤ የተሟላ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ጉዳዩ ይበልጥ የሚመለከታቸው የመንግሥት አስተዳደር አካላትንም ይመለከታል፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ሲነሳ በደምሳሳው ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለው የወዳጅነት ወይም የሽኩቻ አግባብ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ በወሰን አካባቢ የሚነሱ ግጭቶችም በሚሰጣቸው ፖለቲካዊ አንድምታ ይመዘናሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወሰንን በተመለከተ ያለው ነባራዊ ሀቅ ግን ገና ያላተጠናቀቀ የቤት ሥራ መኖሩን ያመለክታል፡፡ እስካለንበት ጊዜ ድረስ በመሬት ላይ በሕግ የተካለለው የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ከ15 በመቶ ያልበለጠ ነው፤›› ሲሉ የሚጠቅሱት በለጠ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በቅጡ ድንበር ያልተካለለች አገር መሆኗ ለብዙ ዘመናት ለሉዓላዊነት አደጋ ሲያጋልጣት መኖሩን አብራርተዋል፡፡

አገር፣ ሉዓላዊነት፣ ማንነትና ብሔራዊ ኩራት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ዳር ድንበር መሆኑን አስምረው የሚያነሱት በኢትዮጵያ ውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ታሪክ ላይ ሰፊ ጥናት ያቀረቡት በለጠ በላቸው (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ መሪዎች ለዘመናት አገሪቱ ላይ ችግር ሲጎትትባት በቆዩ የዳር ድንበር ችግሮች ላይ አተኩረው ከመሥራት ይልቅ የሉዓላዊነት ጥሰት አጋጠመ በተባለ ጊዜ አገር ለመቀስቀስና ከጎናቸው ለማሠለፍ ብዙ ሲተጉ እንደሚታዩ አመልክተዋል፡፡

ከሰሞኑ የተከበረው የሉዓላዊነት ቀን ላይ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ሲቀርቡ የተደመጡ ንግግሮች የኢትዮጵያ አሁናዊ የሉዓላዊነት ሁኔታ አደጋ ላይ መውደቁን አመላካች ተደርገው ነበር የታዩት፡፡ አገሪቱ የሉዓላዊነት ቀን ብላ ማክበሯ በወቅቱ ከሶማሊያ ጋር ከገባችበት ውዝግብ፣ እንዲሁም በዙሪያዋ ካሉ አገሮች ጋር ከተፈጠረው የግንኙነት መሻከር ጋር ሲያያዝ ሰንብቷል፡፡ የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ጥያቄን ተከትሎ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ሴራ ለመጎንጎን ማበራቸው በሰፊው ሲነሳ የሰነበተ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን አጋጣሚ ተገን አድርገው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሆኑት ግብፆች በሶማሊያ ሰላም በማስከበር ስም ጦር ለማስፈር እንቅስቃሴ መጀመራቸው ደግሞ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከልም ከፍተኛ ፍጥጫ ፈጥሮ ሰንብቷል፡፡ በህዳሴ ግድብ ግንባታና የአምስተኛ ዙር ውኃ ሙሌት የተነሳ ግብፆቹ በኢትዮጵያ ላይ ከፈጠሩት ክስና ውንጀላ በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአስመራ በረራ እንዲቋረጥ የኤርትራ ባለሥልጣናት ፈጥረውታል የተባለው እንቅፋት ሁሉ በኢትዮጵያ ዙሪያ የእርስ በእርሱ የተሳሰረ የዲፕሎማሲ ጫና ሴራ እተካሄደ ነው የሚል ድምዳሜ ያሰጠ ጉዳይ ሆኗል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ ጫናና ውጥረቱ በበዛበት በዚህ ወቅት በተከበረው የሉዓላዊነት ቀን ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይህንኑ ጉዳይ በቀጥታ የተመለከቱ መልዕክቶች ሲያስተላልፉ ነው የታየው፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ‹‹ሉዓላዊነት በደምም በላብም የሚጠበቅ እሴት ነው፡፡ የአገር ነፃነት፣ የአገር ዳር ድንበርና የወገንን ክብር መጠበቅ የሚቻለው በደም መስዋዕትነት ነው፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡ ከፖሊሲ ጀምሮ፣ የበጀት፣ የዕውቀት፣ የኢኮኖሚ፣ ወዘተ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለኢትዮጵያ እንደ አገር ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተመስገን፣ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት አገሪቱ እንደሚያስፈልጋት ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ስለአገር ስለመሰዋት በሰፊው አብራርተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊያን አንድም አገር ወረው አያውቁም፡፡ ኢትዮጵያውያን የሰውን በመንካት አንታወቅም፡፡ ከቅርብም ከሩቅም ሊነኩን የመጡ ኃይሎችን ግን በጋራ ድል አድርጎ አሳፍሮ መመለስ ባህላችንና ማንነታችን ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢትዮጵያ ከአንዳንድ አገሮች ጋር ወደ ግጭት እንደምትገባ ይነገራል፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከሶማሊያ ጋር በተደጋጋሚ ተዋግታለች፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት በአንድም ጎረቤት ላይ አንድም ጥይት ተኩሰን አናውቅም፡፡ ምክንያቱም ጎረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ እኛ ሰላም እንደምንሆን እንረዳለን፡፡ ከማንም ጋር የመጋጨት ፍላጎት የለንም፡፡ ነገር ግን በቅርብም በሩቅም ያሉ ሊነኩን የሚፈልጉ ኃይሎችን እንደልማዳችን አሳፍረን ለመመለስ ዝግጁ ነን›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የግጭት ፍላጎት እንደሌላት ደጋግመው ያነሱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ መንግሥታቸው የአገሪቱን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን በሰፊው አብራርተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከቅርብ ሰሞን ወዲህ ስለሉዓላዊነትና ስለአገር መስዋዕትነት ስለመክፈል ደጋግመው እያነሱ የሚገኘው፣ አገሪቱ በቅርብ ጊዜያት ከገጠሟት የሉዓላዋነት ሥጋቶች ጋር በተያያዘ መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል፡፡ ይህ ጉዳይ ደግሞ በአዲሱ ዓመትም ቢሆን ከሁሉ ገዝፎ አገራዊ አጀንዳ እንደሚሆን ብዙዎች ይገምታሉ፡፡