ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች በጉባዔው ተገኝተዋል

ዓለም አፍሪካ ከቻይና አፍሪካ መድረክ ምን አገኘች?

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: September 11, 2024

ቻይና በዕዳ ውስጥ ለተዘፈቀችው አፍሪካ የምትሰጠውን ድጋፍ በሦስት ዓመታት ውስጥ 51 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ እንደምታደርሰው፣ በተጨማሪም የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ቢያንስ ለአንድ ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ቃል ገብታለች።

አፍሪካ ከቻይና አፍሪካ መድረክ ምን አገኘች? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የቻይና ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጉባዔውን ሲከፍቱ

እንደ ሮይተር ዘገባ ቻይና ከአፍሪካ ጋር በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በመሠረተ ልማት፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ትብብሯን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ፕሬዚዳንቷ ዢ ጂንፒንግ በቻይና- አፍሪካ የትብብር ፎረም ላይ ባለፈው ሳምንት በቤጂንግ ለተሰበሰቡ ከ50 በላይ የአፍሪካ አገሮች ለተውጣጡ ልዑካን ተናግረዋል።

‹‹ቻይናና አፍሪካ ከዓለም ሕዝብ አንድ ሦስተኛውን ይይዛሉ። ያለእኛ ዘመናዊነት ዓለም አቀፋዊ ዘመናዊነት አይኖርም፤›› ያሉት ዢ፣ በሀብት በበለጸገው አፍሪካ ሦስት እጥፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ቃል ገብተዋል።

የቻይናው መሪ ለሦስት ዓመታት 360 ቢሊዮን ዩዋን (50.70 ቢሊዮን ዶላር) የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገቡም፣ 210 ቢሊዮን ዩዋን ለብድር መሸፈኛና ቢያንስ 70 ቢሊዮኑ ለቻይና ኩባንያዎች አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንደሚከፈል ገልጸዋል። አነስተኛ መጠን ያለው ወታደራዊ ዕርዳታ እንደሚኖርም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

አፍሪካ ከቻይና አፍሪካ መድረክ ምን አገኘች? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የአፍሪካ መሪዎችን ለመቀበል ሲጠባበቁ

እ.ኤ.አ. በ2021 በዳካር በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ቻይና ቢያንስ 10 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ገብታ ነበር፡፡ በአሁን ጊዜ የገንዘብ ዕርዳታው በራስዋ ገንዘብ በዩዋን የሚሆነው የቻይናን ዩዋን የበለጠ ዓለም አቀፍ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ነው ይላል ዘገባው። አንድ ዶላር 7.0976 ዩዋን መሆኑንም አክሏል፡፡

ከመክፈቻው ሥነ ሥርዓት በኋላ ልዑካኑ የቤጂንግ መግለጫን ‹‹በአዲሱ ዘመን የጋራ የወደፊት ሁኔታ›› እና የ2025-2027 የቤጂንግ የድርጊት መርሐ ግብር ማፅደቃቸውን የቻይና መንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።

የቻይና-አፍሪካ የተቀናጀ የልማት ኔትወርክ እንዲፈጠር እንዲሁም የቻይና ተቋራጮች የፕሮጀክቶቻቸውን መስተጓጎል የፈጠረው የኮቪድ-19 እገዳዎች በመነሳታቸው ወደ አኅጉሪቱ እንዲመለሱ የአፍሪካ መሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።

በዲስኩራቸው ውስጥ ስለ ዕዳ ያላነሱት ፕሬዚዳንት ዢ፣ ምንም እንኳን ቤጂንግ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች የሁለትዮሽ አበዳሪ ብትሆንም የድርጊት መርሐ ግብሩ ክፍያን ለማዘግየት ቅድመ ሁኔታዎችን ያካተተ በመሆኑ የአፍሪካ ደረጃ አሰጣጥ ኤጀንሲ እንዲቋቋም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአፍሪካ አገሮች በቂ የብድር እፎይታ ለማግኘት አለመቻላቸውና የሃብት እጥረት ኅብረተሰቡ እንዳይረጋጋ አድርጎታል ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ናቸው፡፡

የቻይና አፍሪካ መድረክ ከታይዋን ጋር ግንኙነት ካላት ኢስዋቲኒ በስተቀር ለቻይናና ለሁሉም የአፍሪካ አገሮች የሦስት ዓመት መርሐ ግብር አስቀምጧል።

ከ30ዎቹ የመሠረተ ልማት ትስስር ፕሮጀክቶች በተጨማሪ፣ በአፍሪካ የንፁህ ኢነርጂ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ቻይ ናመዘጋጀቷን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ በኑክሌር ቴክኖሎጂ ላይ ትብብር መፍጠሩንና የኢንዱስትሪ ልማትን ሒደት ያዘገየውን የኢነርጂ እጥረትን በመቅረፍ ላይ መሆኗንም አስረድተዋል።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ፣ ቻይና እ.ኤ.አ. በ2021 በዳካር በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ 300 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የአፍሪካ ሸቀጦችን እንደምትገዛ ፕሬዚዳንቱ የገቡትን ቃል ባሁኑ መድረክ ባይደግሙትም፣ የገበያ መዳረሻን ለማስፋት ግን ቃል ገብተዋል።

ተንታኞች እንደሚሉት የቤጂንግ የዕፀዋት ጤና ቁጥጥር ሕጎች በጣም ጥብቅ በመሆናቸው ቻይና ቃልዋን መፈጸም አላስቻላትም። ይሁን እንጂ አፍሪካ በምትኩ ተጨማሪ  የገንዘብ ድጋፍ የምታገኝ ይመስላል። ዓምና ቻይና ለአፍሪካ 4.61 ቢሊዮን ዶላር ብድር መፍቀዷ ከ2016 ወዲህ የመጀመሪያው ዓመታዊ ጭማሪ ነው ተብሏል።