ማኅበራዊ
አዲሱ ዓመት ምን ይዞ ይዝለቅ?

የማነ ብርሃኑ

ቀን: September 11, 2024

ዓመተ 2016ን ጨርሰን ዛሬ 2017 ዓ.ም.ን ጀምረናል፡፡ አብዛኛው ሰው በአዲስ ዓመት፣ አዲስ ዕቅድ የሚያቅድበትና የሚተገብርበት ነው፡፡ ትዳር ያልመሠረተ ጎጆ የሚወጣበት፣ ያልወለደ አቅፎ የሚስምበት፣ የጤና ችግር ያለበት ከሕመሙ የሚፈወስበት፣ ወዘተ እንዲሆንለት የሚመኝበት ነው፡፡

ዓምና ለኢትዮጵያውያን እንዴት ዓይነት ዓመት ነበር? በምን ጎኑስ ያስታውሱታል? ሲል ሪፖርተር ሁለት ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡

‹‹ዓመቱ ለኢትዮጵያውያን የጭንቀት ዓመት ሆኖ ያለፈ ነው፡፡ ከወር እስከ ወር፣ ከዓመት እስከ ዓመት ሲተላለፍ የመጣ ግጭትና ብሔር ተኮር ጥቃት ያለበት ዓመት ነበር፤›› የሚሉት አንጋፋው ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላት ናቸው፡፡ ዘመኑ ዜጎችን ያስጨነቀና የፈተነ ከመሆኑ ባሻገር የኑሮ ውድነት ሌላው ራስ ምታት ሆኖ በአገሪቱ የከረመ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

እንደ ጸሐፌ ተውኔቱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጨለማ ውስጥ ብርሃን ይወለዳል የሚል ተስፋ አርግዞ በመኖር ላይ ያለ ነው፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አገሩን ይወዳል፡፡ ለሕዝቡም የሚቆረቆር ስሜት አለው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ክብሩን የሚወድ ነው የሚሉት አቶ አያልነህ የኑሮ ውድነቱና እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶት ወጥረው እየያዙት እንጂ አገሩን የሚጠላ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያ ልዩነቷ ሳይጎላና አንድነቷም ሳይጠብቅ በመሀል ላይ በመዋለል ዓመቱን የከረመች መሆኑን፣ ከዚህ በመነሳትም ዘመኑ ለኢትዮጵያ መልካም ዘመን ነበር ብሎ ለመግለጽ አያስደፍርም ሲሉየሚናገሩት ጸሐፌ ተውኔቱ፣ ለአዲሱ ዓመት ምኞታቸውን የገለጹት፡ ሕዝብ ከሥጋት ወጥተው በሰላም ሥራቸውን የሚከውኑበት ዓመት እንዲሆን፣ መንግሥትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ሆነው ሊመክሩበት ይገባል በማለት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት በአስቸጋሪ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀዋል የሚሉት አቶ አያልነህ፣ አዲሱ ዓመት ሕዝቡ ከገባበት የጭንቀትና የመከራ አረንቋ የሚወጣበት እንዲሆን ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹ረሃብ፣ ጦርነት፣ ግጭትና ስደት ለኢትዮጵያውያን መታወቂያ የሆኑበት ዘመን ምዕራፉ መዘጋት ይኖርበታል፤›› የሚሉት ጸሐፌ ተውኔቱ መንግሥት በመጪው አዲስ ዓመት ስለሕዝቡ ግድ ሊለውና የተበላሹ ነገሮችን በማስተካከል ይህችን አገርና ሕዝብ ወደቀደመ ክብርና ከፍታቸው ሊመልሳቸው የሚገባ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በማኅበራዊ ሕይወት፣ በጋብቻና በወጣቶች ዙሪያ የተለያዩ መጻሕፍት ያዘጋጁት  መጋቢ አመሉ ጌታ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ 2016 ዓ.ም. እንደ አገር  ደግም ክፉም የታየበት ነበር፡፡ መልካም የልማት ሥራዎች የተሠሩበት፣ የከተሞች ውበት በኮሪደር ልማት አማካይነት የታየበትና ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ዕውን የሆኑበት ዓመት ነው፡፡ እኚህ ሥራዎችም የሚያስመሰግኑ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

በተቃራኒው ከሰላም ዕጦትና ካለመረጋጋት ጋር ተያይዞ አገርና ሕዝብ ዋጋ የከፈለበት ዓመት መሆኑን የሚገልጹት መጋቢ አመሉ፣ ዕገታዎች ግድያዎችና መፈናቀሎች የታዩበት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡ ይህም መልካም የነበረውን የሕዝቡን ማኅበራዊ እሴት ሊሸረሽር የቻለ ነው፡፡

እንደ መጋቢ አመሉ የመከባበር፣ የመተሳሰብና ወንድማዊ ፍቅር የቀዘቀዘበት፣ የመጣላላትና የመገፋፋት ስሜት  የገዘፈበት ዓመት ሆኖም  ከርሟል፡፡

በመሆኑም መጪው አዲስ ዓመት ከራሳችን ጋር የምንታረቅበት፣ እንደ አገር አንድ ሆነን የምንቆምበት፣ በእግዚአብሔር ቃል የምንታነፅበትና በሰላምና በፍቅር የምንኖርበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ያክላሉ፡፡

በአገሪቱና በምድሪቱ እነኚህ እውን እንዲሆኑ መንግሥት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላትና በአጠቃላይ ሕዝቡ አንድ በመሆንና በመቀናጀት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡