ልናገር የአዲስ ዓመት ምኞት ለለውጥ ፈላጊ አገር

ቀን: September 11, 2024

በተስፋዬ ወልደ ዮሐንስ ኃይሌ

ትንሽ ቦታ

ብንጣላ መታረቂያ

ብንታረቅ ለመጣያ

ብንታሰር ይቅር ማያ

ይቅር ብንል መታሰሪያ

ትንሽ እንተው ባዶ ቦታ።

ጥግ ድረስ የለም ሥራ፣ ጥግ ድረስ የለም ፋታ።

በልባችን ደግ በኩል፣ እንፈልግ ባዶ ቦታ

የጳጉሜ ዓይነት ትንሽ ቦታ

ለዘመን መለዋወጫ።                           

ነብይ መኮንን

የሚያልፍ አይመስልም ያልነውም፣ መስከረም ብለን የጀመርነውን ዓመት አገባደን በቁጥር አሻግረን ለሌላ አምላክ ቢፈቅድና ብንኖር ብለን ለምናስበው ሌላ መስከረም አሻግሮ ሊያስረክበን የቀናት ቆይታ ብቻ ቀርተውታል፡፡ በ2017 ዓ.ም. ከፊታችን እንኳን አደረሳችሁ መጣሁ መጣሁ እያለን ነው፡፡ አደይ አበባን በፀሐይ ብርሃን ታጅባ ልንመለከት ዓይኖቻችን መናፈቅ ላይ ቆመዋል፡፡ የጊዜ መንጎድ ድንቅ ነው፡፡ በብርሃን የተቀበልነውን አዲስ ዓመት በጨለማ እንሸኘው ዘንድ በብርሃን ደግሞ ሌላ አዲስ ዓመት እንቀበል ዘንድ ተፈጥሮ ግድ ትለናለች፡፡ ስንኖርበት የነበረውን ቁጥር ቀይረን አሮጌውን በአዲሱ ተክተን ቁጥር አክለን፣ በብርሃን፣ ደስታና በፀሐይ መናፈቅ ውስጥ አዲስነቱን በአደይ አበባ አጅበን እንቀበላለን፡፡ አንድ ብለን የምንጀምረው መስከረም ተጉዞ ከጳጉሜ ደጃፍ ያደርሰናል፡፡

የልጅነት የአዲስ ዓመት የትምህርት ቤት መከፈት ጉጉት፣ በጭጋግ ከተሞላው፣ በረዶና ዝናብ ከማያጣው ብርሃን ወደሚቀበለው ዓመት የነበረኝን ጉጉት የእንኳን አደረሳችሁ የባህል ጭፈራው፣ የየቤቱ የአዲስ ዓመት ዝግጅት፣ የግዥው ሩጫው፣ ትዝታ አሻግሮ ዛሬ ይህ ዓመት ካለፈው አዲስ ዓመት ምን የተለየ ነገር ይዞልን ይመጣ ወይም ይመጣብን ይሆን ወደሚል አንፃራዊ ጥያቄ እንድሻገር ዕድሜም ሳይሆን አይቀርም ይጎተጉተኛል፡፡

ያለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ከዕፎይታ ይልቅ ሥጋት፣ ከመልካም ነገር ይልቅ መጥፎ ጉዳዮች፣ ከመሻሻል ይልቅ ወደ ከፋ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎሽ እየቆጠርንና እየሰማን የመጣንባቸው ቀናት እየሆኑብን ሰላም፣ ደኅንነትና መፃይ ተስፋን መጠበቅ እርግጠኛና ተገማች አለመሆንን አስከትሎ በየቀኑ ወቸው ጉድ የሚያስብል ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡

በየቦታው የተከሰቱ ግጭቶች፣ የፖለቲካው መመሰቃቀል፣ ለመኖር ወጥቶ ለመግባት ደኅንነት ያለመሰማት ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት በርካታ ውስብስብ የሆኑ ችግሮች ለማጠናቀቅ ቀናት የቀሩትን 2016 ዓ.ም. የተፈታተኑ አንፃር ነጥቦች ነበሩ፡፡ በርካቶች በተፈጥሮ አደጋ ያጣንበት ያህል በቁጥሩ ከፍ ያሉትን  ደግሞ በሰው ሠራሽ ችግሮቻችን ከጎናችን ያጣንበት ዓመትም ነበር፡፡ ውጤቱም በርካቶችን በራቸውን ዘጋ፣ ለቤተሰቦቻቸው የእግር እሳት ሆኑ፣ ለአካባቢያቸው ደግሞ የሚቆጩ ሰዎች ሆነው አልፈውበታል፡፡

በእኔ ትውልድ ውስጥና ያለፉት ሃምሳ ዓመታት ተመሳሳይ የሆነ የፖለቲካ ችግር አዙሪት ሆኖባት፣ ሁሉም ነፃነት ፈላጊ ሁሉም ነፃ አውጪ ብሎም ተፈላጊው ነፃነት በውይይት ሳይሆን በጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ የሚገኝና የሚገኝ ብቻ የሆነ አስተሳሰብን መሆኑን መመልከት ግድ እየሆነባት፣ የዜጎችን ሕይወት በማስያዝ የሚገፋ የራስ እውነት ፍለጋ መድረክ ከሆነች ሰነባበተች፡፡ ክስተቱን ለሚመለከት መቋጫው ቅርብ ይሆናል ብሎ ለመገመት ያስቸግረናል፡፡

መንግሥት ሁሉን አካታች፣ ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ መደላድሎችን ከማመቻቸት ይልቅ የእኔ ብቻ አውቅልሃለው መርህ በመያዝ የእኔ ከሞትኩት ሰርዶ አይበቀል በሚል የፖለቲካ እሽክርክሪት ውስጥ ራሳቸውን ብቻ የሚመለከቱ የፖለቲካ ልሂቃንን ይዘው የሕዝብን እሮሮ ሲቃ፣ እንግልትና መከራ ከመጤፍ የማይቆጥሩ አመራሮችን ሰግስጎ ምርጫን ሕጋዊ መሣሪያ በማስመሰል የሥልጣን ማስቀጠያ መንገድ ብቻ ለማድረግ መንቀሳቀስን ትልቅ ጉዳይ ከተደረገ ሰነባበተ፡፡

ብሔር ለአዳዲስ አስተምህሮቶች፣ ለዴሞክራሲ ግንባታ፣ ለአብሮ መኖር ትስስሮሽ ከመጠቀም ይልቅ ለፖለቲካ ጥቅም መሸሸጊያ፣ የበዳይና ተበዳይ ትርክት መሥሪያ መሣሪያ ሆኖ መገልገልን የመረጥንበት፣ መርጠን ካልተፈጠርንበት ቡድን ጋር ማንነት፣ ጥላቻ፣ መወገሪያ፣ የማዕረግና ዕልቅና ማግኛ የመሆን ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡

ይህንን ፈተና ይዘን 2017 ዓ.ም. ለመቀበል ጉድጉድ ላይ ባለንበት ወቅት ራሴን ኢትዮጵያ ሆይ የሚመጣው ዓመት ምን ይግጠምሽ ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ለእኔና ለልጆቼ የምትሆነውን አገር በዓይነ ልቦናዬ እስላለሁ፡፡ እነዚህ ሦስት ቁልፍ ሐሳቦች ቢሳኩላት ምናልባትም የተሻለ አገር እንደምትኖረን ተስፋ በማድረግ ኢትዮጵያ ሆይ የአዲስ ዓመት  መልካም ምኞቴ ይህ ነው፡፡

የተደቀኑት አፈሙዞች ወደ መሬትሽ ይውረዱ፣ ያዘቅዝቁ

ግጭት እዚህም እዚያም መገለጫ በሆነበት፣ አፈሙዞች ወደፊት ሰድረው የሰውን ሕይወት በሚቀሙበት አገር ውስጥ የዛሬው ልጆች፣ መጪው ትውልድ ነገ በተስፋ አይተውም፡፡ የውይይትና ንግግር ትርጉም ይርቅበታል፡፡ ሁሉንም ነገር በጠመንጃ አፈሙዝ ውስጥ የማሰብ፣ ኃይል የሁሉም ነገር ምንጭነት የትውልዱ መገለጫ ይሆናል፡፡ በየቦታው ያሉ ግጭቶች ምንጫቸው ወደ ውይይት መጥተው ተኩስና የጥይት ድምፅ ርቀው መንደሮቹ ሰላም ወርዶባቸው ፀአዳ የለበሱ፣ በፈገግታ የታጀቡ የሚሰጡ እጆች የምናይበት፣ አፈሙዞች የሚተፉትን ድምፅ በደስታ ሲቃዎች የሚቀየሩበት ዓመት እንዲሆን፡፡      

ወጥቶ መግባት የማያሳስብበት፣ የዜጎች ደኅንነትና ሰላም ተጠብቆ መመልከት

መታሰር፣ መሰወር፣ መጥፋት፣ መታገትና መገደል በየዕለቱ በሚመስል ሁኔታ በመገናኛ ብዙኃን የምንመለከትበት፣ የማኅበራዊ ሚዲያው እዚህም ደረሰ እያልን የምንመለከትበት መድረክ ሆኗል፡፡ ዜጎችን ለማስለቀቅ ከግለሰቦች የመንገድ ልመና እስከ እምነት ቤቶች የዘለቀ ዕንባ፣ ዋይታና ሰቆቃ የበዛበት፣ ዜጎች ወጥተው ስለመመለሳቸው እርግጠኛ የማይሆኑበት፣ የቱ ጋ ምን እንደሚሆኑ ዜጎች ደኅንነታቸው ምን እንደሚሆን ጥያቄያቸው በርትቶ የንግድ እንቅስቃሴ የተገታበት፣ ለቅሶ ተገኝተው ከጎናቸው ያÚቸውን የሚወዳቸውን ቤተሰቦቻቸውን መቅበር አለመቻል የመሳሰሉ በርካታ ችግሮችን አስተናግደናል፡፡ ይህ ዓመት እዚህ ጋር ብሄድ ይህ ይገጥመኛል ብለው የማይጨነቁበት፣ በሰላም ካሰቡት ቦታ የሚደርሱበትና የሚመለሱበት ወጥቶ መግባት የማያሳቅቅበት ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ፡፡    

መነጋገር መደማመጥ መወያየት የሐሳብ ልዕልና ጠረጴዛ ላይ ማየት

ሁልጊዜም ከዘመን ጋር የሚቀያየር ፖለቲካዊ ትርክት፣ ፍላጎትና ተግባር እንደሚኖር በየትኛውም ዓለም የተለመደ ተግባር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ፖለቲካዊ ሥነ ምኅዳር ውስጥ መነጋገር፣ መደማመጥ፣ የሐሳብ ልዩነቶችን ለመስማት ብዝኃነትን ለመቀበል ልዩነቶች ላይ መሥራት እየራቀን፣ በተቃራኒው አለመደማመጥ ‘እኔን ብቻ ስሙ’ ‘እኔ ብቻ ልክ ነኝ’ የሚል መድረክን መፍጠርን ተያይዘነዋል፡፡ በተለይም ደግሞ በፖለቲካ ልኢቃኑ መካከል ዕውቀትና ሐሳብ ቦታ እያጣ፣ ስሜትና እኔ ብቻ እየገነነ መመልከት የዕለት ተዕለት ሥራችን ሆኗል፡፡ ያለመነጋገር፣ ያለመደማመጥ ለውጥን ማሰብ ሩቅ ስለሚሆንብን በሮቻችን ለሐሳብ ልዩነቶች ክፍት የሚሆኑበት ጠረጴዛችን ለውይይት መዳረሻዎቻችን ይሆኑ ዘንድ እመኛለው፡፡    

አድርባይነት ተወግዶ ለአገር የሚሠራ ትውልድ መገንባት

አንድ መንግሥታዊ ሥርዓት ይሄዳል፣ ሌላ መንግሥታዊ ሥርዓት ይመጣል፡፡ ሰዎች ይሄዳሉ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ አገር የብዙዎች መሰባሰቢያ ግለሰቦች ትውልድ ማፍሪያና ማስቀጠያ ገናናነትንና ታሪክ የማቆያ ምድር ናት፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አድርባይነት፣ በፊትለፊት መውደቅ “እኔ” እና “ዛሬ” ብቻ የሚል የጥቅመኝነት፣ ቡድንተኝነትና ምሁራዊ አድርባይነት መስፋፋት በሁሉም መስኮች ተስፋ እንድንቆርጥ እያደረገን ይገኛል፡፡ ሰው በችሎታው፣ በአቅሙና በዕውቀቱ የሚጠበቅበት ቦታ ሲገኝ ያስደስታል፡፡ ህሊናውን መሣሪያ አድርጎ የሚሠራው አንዳንዱ ተግባር ደግሞ ለነገ በትውልዱ ለመታወስ –ሚ ሐውልትን ለማቆም ዕድል ይሰጠዋል፣ ታሪክ ይዘክረዋል፡፡ እውነት አደባባይ እንድትቆም፣ ለሌሎች ማሰብን ለአገር መትረፍን፣ ለዕውቀት፣ ችሎታና አቅም ቦታ የምንሰጥበት እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡

እንደ መውጫ

ሁልጊዜም ቀናትን እንደ አዲስ መኖር መልመድ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ትላንት፣ ከትላንት በስቲያ፣ የዛሬ ሳምንት፣ ወር፣ ዓመት ነበር ሆነዋል፣ አልፈዋል፣ ላይመለሱ ጥለውን ሄደዋል፣ ነጉደዋል፡፡

መነሻችን እነሱ ነበሩ፡፡ መድረሻችን ግን ዛሬና ነገ ነገ ናቸው፡፡ የኋላው ሊጎትተን አይገባም፣ ሊያስተምረን ግን ፍፁም ትክክል ነው፡፡ ዛሬ አዲስ ቀናችን ነው ብሎ መጀመርን መለማመድ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡ አለበለዚያ ካለፉት  ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት፣ ዓመታት የተለየ አዲስ ነገርን እንጠብቅ፣ ተስፋን እናድርግ፡፡

መልካም አዲስ ዓመት ከምንወዳቸው ጋር!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ሲያትል ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው tesfayewoldeyohanes.h@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡