ልናገር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቅርቃር ከዓለም የኢኮኖሚ ታሪክ አንፃር ሲታ

ቀን: September 11, 2024

በጌታቸው አስፋው

ብዙ ሰዎች ስለዓለም ኢኮኖሚ ሲነጋገሩ የሚያወሩት ከአዳም ስሚዝ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ጀምሮ ያለውን ነው፡፡ ሆኖም የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ታሪክ ገና ከክርስቶስ ልደት በፊት በእነ አሪስቶትልና በእነ ፐሌቶ የፍልስፍና ማዕከል ሆኖ በተለይም ስለየራስና የሰው ሀቅ፣ ስለልግስና እና ስለግብረ ገብ ይነጋገሩ የነበረ ሲሆን፣ በመካከለኛው ዘመንም የእምነት ተከታይ የኢኮኖሚ ፈላስፎች የእነ አርስቶትልን ግብረ ገባዊ ፍልስፍና ከሃይማኖታዊ ትምህርቶች ጋር አዛምደው ይመለከቱ ነበር፡፡

ከአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን እስከ አሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን በነበሩት ዓመታት የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ለሁለት ጎራ ተከፍሎ ክርክር ይካሄድበት ነበር፡፡ በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ ተጀምሮ በመላው አውሮፓ የተስፋፋው ንግድ ሀብትን እንደሚያመነጭ የሚያምኑ የኢኮኖሚስቶች ስብስብ የሚታመን (Mercantalism) አመለካከት አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛው የዚህ ተቃራኒ የሆነው በፈረንሣይ ተጀምሮ ወደ አውሮፓ የተስፋፋው የሀብት ምንጭ የግብርና ምርት ብቻ እንደሆነ በሚያምኑ የኢኮኖሚስቶች ስብስብ የተቀነቀነው (Physiocracy) አመለካከት ነው፡፡ የሁለቱን ቡድኖች አመለካከት ኢትዮጵያ ዛሬ ከገባችበት የኢኮኖሚ ቅርቃር አንፃር እንመልከት፡፡

ሀብት ከንግድ ይመነጫል (Mercantalism) አመለካከት አገሮች በፍጥነት ሊያድጉ የሚችሉት ከሌሎች አገሮች ጋር በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ኢምፖርት ከሚያደርጉት በላይ፣ ኤክስፖርት አድርገው ወርቅና የውጭ ምንዛሪዎችን በመሰብሰብሰብ እንደሆነ ያመኑ ናቸው፡፡ እነዚህ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግሥት እጅ ጠንካራ ሆኖ ብሔራዊ ኢኮኖሚው በመንግሥት ቅኝት እንዲተዳደር አደረጉ፡፡ በሃያኛው ክፍለ ዘመን በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ተስፋፍቶ አፍሪካንና ኢትዮጵያንም ጭምር ነካክቶ ብልጭ ድርግም ያለው የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ የመነጨውና አምሳያ የሆነው ከዚህ የንግድ ኢኮኖሚ አመለካከት ጋር ነው፡፡    

ሁለተኛውና ሀብት ከግብርና ምርት ይመነጫል (physiocracy) አመለካከት አገሮች በፍጥነት ሊያድጉ የሚችሉት፣ በአገር ውስጥ ትርፍ ምርት አምርቶ ለመሸጥ ግለሰቦች በገበያ ሲወዳደሩ እንደሆነ በማመን ኋላ በአዳም ስሚዝ ለተነደፈው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት መሠረት ሆኗል፡፡  

ዓለም አቀፍ ንግድ ሁሌም የነበረ ቢሆንም እንደዚህ በዓለም አቀፍ ተቋማት በአስገዳጅነት መከናወን የጀመረው ግሎባላይዜሽን የሚባለው ፍልስፍና ከመጣ በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የበለፀጉት አገሮች እርስ በርሳቸው ይነጋገዱ የነበረ ቢሆንም፣ ለታዳጊ አገሮች ግን በአቅማቸውና በፈቀዱት ልክ ወደ የዓለም ንግድ ሥርዓት ከመግባት በቀር፣ ለዕድገታቸው ግን የልማት ኢኮኖሚ ፍልስፍናን ነድፈው በኢኮኖሚያቸው ውስጥ የተንሰራፋውን መዋቅራዊ ችግር እንዲቀርፉ ፈቅደውላቸውም ደግፈዋቸውም ነበር፡፡

ከግሎባላይዜሽኑ በኋላ ግን ዓለምን አንድ የገበያ መንደር ለማድረግ በጠነሰሱት ሥርዓት መሠረት ታዳጊ አገሮች ከልማት ኢኮኖሚ መንገድ ተላቀው የዓለም አቀፍ ንግድ ሥርዓትን እንዲቀላቀሉ አስገደዷቸው፡፡ የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም የሚባል የአተገባበር ዘዴ ነድፈው አቀረቡላቸው፡፡

በዓለም አቀፍ ተቋማት ለታዳጊ አገሮች የተነደፈው የኢኮኖሚ አስተዳደር መድኃኒት በተቃርኖ የተሞላ ነው፡፡ ከላይ ካየናቸው የበለፀጉት አገሮች የተጓዙባቸው የኢኮኖሚ አመለካከቶች አንፃር ሲገመገሙ የሚከተለውን ይመስላሉ፡፡

በንግድ ኢኮኖሚ (Mercantalism) ፍልስፍና አምሳያ በመንግሥት ጠንካራ እጅ ተሳትፎ አገርን በጋራ ለማበልፀግ የታለመው ዓይነት ነው እንዳይባል የመንግሥት እጅ ከኢኮኖሚው ውስጥ ይውጣ በሚል ቀጭን ትዕዛዝ የታጠረ ነው፡፡ በግብርና ምርት ኢኮኖሚ (Physiocracy) ፍልስፍና አምሳያ በውስጣዊ የነፃ ገበያ ውድድር ኢኮኖሚ ሥትርዓት ላይ የተመሠረተ ነው እንዳይባል የብራችሁን ዋጋ አርክሳችሁ ወደ ዓለም አቀፍ ንግድ ግቡ በሚል ትዕዛዝ የታጠረ ነው፡፡ ይህ አጉል ምክር አይሉት ትዕዛዝ ታዳጊ አገሮችን ከሁለት ያጣ ጎመን አድርጓቸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት የብርን ዋጋ ሸቀጥን በዓለም ገበያ በመግዛት አቅሙ አዳክሙ ወይም አንሳፍፉ ሲሉ የሠራተኛን ደመወዝ ከዓለም የክፍያ ስኬል ጋር አስተካክሉ አላሉንም፡፡ ሠራተኛው በዝቅተኛ ደመወዝ ቢራብ ቢጠማ ምን ገዷቸው፡፡ እኛ ተመካሪዎቹም ይህንን ጥያቄ አናነሳላቸውም ምን ገዶን፡፡

ዛሬ የበለፀጉት ተብለው የሚጠሩ አገሮች ከላይ የተጠቀሱትን ሁለቱንም የኢኮኖሚ ፍልስፍናዎች አፈራርቀው ተጠቅመዋል፡፡ በንግድ ኢኮኖሚ የመንግሥት ጠንካራ እጅ ሥርዓት እርስ በርስ ከመነጋገድም አልፈው ተርፈው ታዳጊ አገሮችን በቅኝ ግዛትነት ይዘው የጥሬ ዕቃ ምንጭና የሸቀጥ ማራገፊያ አድርገዋቸው ቆይተዋል፡፡ በውስጥ ኢኮኖሚ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርት ዕድገት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍናም ከአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ራሳቸውን አደልበዋል፡፡ በሃያኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ ወደ ግሎባላይዜሽኑ የገቡትና ሸማች ፍለጋ ዓለም አቀፍ ቅኝት ያደረጉትም በውስጥ ከደለቡና የተትረፈረፈ ምርት ማምረት ከቻሉ በኋላ ነው፡፡ 

በዚህ ቅጥ ያጣ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት ቅርቃር ኢትዮጵያንም ጨምሮ የታዳጊ አገሮች መጨረሻ ምን እንደሚሆን እንመልከት፡፡

በተደረገባቸው ግፊት መሠረት ኢትዮጵያና ታዳጊ አገሮች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርትን ከማስፋፋት ይልቅ የመንግሥት አጋርነት በሌለበት ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ እንዲያተኩሩ ተደርገዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በቴክኖሎጂ መራቀቅ ምክንያት ንግዱ ከቁሳዊ ምርቶች ንግድ ይልቅ የፌስቡክና የቲክቶክ የአገልግሎት ምርቶች ንግድ ላይ አተኩሯል፡፡ የወደፊት አዝማሚያ ዝንባሌውም እጅግ በጣም አስፈሪ ደረጃ ላይ ነው፡፡

መጨረሻው ምንድነው? የአገልግሎት ንግድ በተለይም በሶሻል ሚድያ አገልግሎት ንግድ አማካይነት ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው ከመጠን በላይ ገንዘብ፣ በሕዝብ ቁጥር ዕድገት ምክንያት ምርታማነቱ ሊያድግ ከማይችለው የግብርና ምርት ጋር ተነፀሮ ሲታይ የኑሮ ደረጃ ነቀርሳ የሆነው የዋጋ ንረት ተባብሶ የሚቀጥል እንጂ፣ የሚረግብ ወይም ወደ ኋላ የሚመለስ አይሆንም፡፡ ጤፍ በድንገት ከወጣበት በኩንታል አሥራ አምስት ሺሕ ብር የመቀነስ አዝማሚያ እንዳላሳየ አይተናል፡፡

ሁኔታው ለምን ያህል ጊዜ ይቀጥላል፡፡ መልሱ ትናንት ዛሬና ነገ በአገራችን እያየን ያለነው ወደፊትም ለረዥም ጊዜ የምናየው በ18ኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዛዊ ኢኮኖሚስት ቶማስ ማልተስ የተነደፈው የሕዝብ ቁጥር ጽንሰ ሐሳብ ነው (Population Theory)፡፡ እንደ ቶማስ ማልተስ ጽንሰ ሐሳብ ተፈጥሮ ሁልጊዜም ሚዛን ትጠብቃለች፡፡ በፍጥነት የሚያድገው የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና ፍጥነቱን ጠብቆ የማያድገው የምግብ ምርት ተፈጥሯዊ ሚዛን የሚጠበቀው፣ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች የሕዝብ ቁጥር ቀንሶ ራስን በሕይወት ለማቆየት የሚያስችል ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ልክ የምግብ አቅርቦቱ ከሕዝቡ ቁጥር ጋር ሲመጣጠን ነው፡፡

ይህ ጽንሰ ሐሳብ በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት በምርታማነት ዕድገት ውድቅ የተደረገ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የምርት ቴክኖሎጂ ባልተስፋፋባቸው አገሮች እስከ ዛሬም የፀና ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለረዥም ጊዜ የሚሽከረከረው በዚህ ራስን በሕይወት ለማቆየት በሚደረግ ጥረት የኑሮ ደረጃ ልክ ነው፡፡ ይህም የውጪውን ኑሮ ዓይነትና ደረጃ በድምፅና በምሥል አይቶ ለሚጓጓው ለአዲሱ ትውልድ ከስደት በቀር መፍትሔ እንደሌለው መልዕክት የሚሰጥ ነው፡፡

ይህን አስከፊ ሁኔታ መቀልበስ ይቻላልን፡፡ የማይቻል ነገር የለም በአገር ውስጥም ይመረት ከውጭም ኢምፖርት ተደርጎ ይግባ የሚያስፈልገን የግብርናና የኢንዱስትሪ ቁሳዊ ምርትን የሚያሳድግ ቴክኖሎጂ እንጂ፣ አሰሱም ገሰሱም የሚወራበት የወሬ ማማ ላይ ተቀምጦ የሚያንተከትክ ጥቅም አልባ የሚዲያ ቴክኖሎጂ አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነት ሕዝባዊ ጥቅም የሌለው አገልግሎት ዘርፍ መስፋፋት በገበያ ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን ከልክ በላይ አሳብጦ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን ይፈጥራል፡፡  

ኢትዮጵያውያን ለኢኮኖሚስቶች ምክር ጆሮአቸውን መስጠት የፈለጉ አይመስሉም፡፡ ምን ቢባል ምን ቢደረግ እንደሚያሳምናቸው መገመት ያስቸግራል፡፡ የባለሙያ ምክር ገፍተው ዓይናቸው እያየ ገደል እየገቡ ነው፡፡ ‹ምከረው እንቢ ካለ መከራ ይምከረው› እንደሚባለው መከራም አልመከራቸውም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡