በጎንደር ከተማ ቀበሮ ሜዳ በሚገኘው የመጠለያ ጣቢያ

ማኅበራዊ  በጎንደር ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ መኖር ሰልችቶናል አሉ

አበበ ፍቅር

ቀን: September 11, 2024

ከተለያዩ ክልሎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ ቀበሮ ሜዳ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ በመጠለያ ጣቢያ መኖር እንደሰለቻቸውና በአዲሱ ዓመት መውጣት እንደሚፈልጉ ተናገሩ፡፡

ከኦሮሚያ፣ ከትግራይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ እንዲሁም ከሱዳን በተለያዩ ግጭቶች ተፈናቅለው በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ ቀበሮ ሜዳ በሚገኘው የመጠለያ ጣቢያ፣ ከአራት ዓመታት በላይ የቆዩ ተፈናቃዮች፣ በ2017 ዓ.ም. ወደ ቀዬአቸው ባይሆንም ሠርተው የሚኖሩበት ቦታ መሄድ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

አቶ አበበ ዳንዴ ከትግራይ ክልል ሽራሮ ከተማ 2013 ዓ.ም. በሰሜኑ ጦርነት ተፈናቅለው ወደ መጠለያ ጣቢያው እንደገቡ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹በመጠለያ ጣቢያ የመንግሥትን እጅ እየጠበቅን መኖር ሰልችቶናል፤›› ያሉት አቶ አበበ፣ መንግሥት ከቻለ ወደ መጡበት ካልሆነ ሠርተው መብላት ወደ ሚችሉበት ቦታ የትራንስፖርት ገንዘብ ሰጥቶ ከካምፕ እንዲያስወጣቸው ጠይቀዋል፡፡

‹‹ሲያበላንና ሲያጠጣን የነበረው የጎንደር ማኅበረሰብ በአሁኑ ወቅት ችግር ስላለበት፣ እንኳን እኛን ሊረዳ ለራሱም አቅም አጥቷል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ በዚህም ማኅበረሰቡ ተሰላችቷል ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ዘላቂ መፍትሔ ተፈልጎ ሠርተው ቤተሰባቸውን እንዲመሩ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡  

ተሽከርካሪን ጨምሮ ሙሉ ንብረታቸውን ጥለው ወደ መጠለያ ጣቢያ እንደገቡ የተናገሩት አቶ አበበ፣ በወር እስከ 30 ሺሕ ብር ለመንግሥት ግብር ይከፍሉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

‹‹መንግሥት የወደመብንን ንብረት ይተካልን አንልም፤›› ያሉት አቶ አበበ፣ ነገር ግን ከመጠለያ ወጥተው ሠርተው የሚተዳደሩበትን መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም. ከሽራሮ ከተማ ተፈናቅለው ወደ መጠለያ እንደገቡ የተናገሩት ወ/ሮ አማረች አለነ እንደተናገሩት፣ ችግሩ ከመቼውም በላይ ተባብሶባቸዋል፡፡

መንግሥት በሁለት ወራት 15 ኪሎ ግራም በቆሎ እያቀረበላቸው እንደነበር ተናግረው፣ ነገር ግን ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ለመኖር በጣም ከባድ እንደሆነባቸው አክለዋል፡፡

‹‹ልጆቼ ያለ ትምህርት በመጠለያ ጣቢያ መኖር ሰልችቷቸዋል፣ ከዚህ መውጣት ይፈልጋሉ፤›› ያሉት ወ/ሮ አማረች፣ በአዲሱ ዓመት የሰው እጅ ከማየት መላቀቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

የሚተኙበትና የሚለብሱት ስለሌላቸው መሬት ላይ በመተኛት እንደሚያሳልፉ የተናገሩት ተፈናቃዮቹ፣ በዚህም ምክንያት በተለይ በልጆቻቸው ላይ የቁስል በሽታ ተከስቶ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በሽታውን በማኅበራዊ ሚዲያ የተመለከቱ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የቁሳቁስና ዕርዳታ እንዳደረጉላቸው፣ ለዘመን መለወጫ በዓል መዋያም ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ገልጸዋል፡፡

ከ16 በላይ ሕፃናት ታመው ሲታከሙ መቆየታቸውን የተናገሩት ደግሞ፣ የተፈናቃዮች ካምፕ አስተባባሪ አቶ መላኩ ገብሬ ናቸው፡፡

በሽታው ከምግብ እጥረት የሚመጣ እንደሆነ ከባለሙያ መስማታቸውን የተናገሩት አቶ መላኩ፣ ከሕፃናቱ ገላ ትል መሰል ነፍሳት ሲወጡ ነበር ብለዋል፡፡

በመጠለያ ካምፕ ውስጥና ውጪ 9,300 ገደማ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የተናገሩት አስተባባሪው፣ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

ብዙዎቹ ተፈናቃዮች ከካምፕ መውጣትና የራሳቸውን ገቢ የሚያገኙበትን ሥራ መጀመር ይፈልጋሉ ያሉት አቶ መላኩ፣ መንግሥት ከተረጂነት የሚወጡበትን መንገድ ቢያመቻች የተሻለ ነው ብለዋል፡፡

በዓል በመጣ ቁጥር በተፈናቃዮች ፊት ላይ የሚታየው ድባብ በጣም የሚያሳዝን እንደሆነ የተናገሩት አቶ መላኩ፣ የዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባደረጉላቸው ድጋፍ እንደሚያሳልፉ አክለዋል፡፡

ግማሽ ሚሊዮን ብር፣ አምስት የዕርድ በሬዎች፣ አምስት ኩንታል ጤፍና ሌሎች የበዓል መዋያ ቁሳቁሶችን አሰባስበው እንደሰጧቸው አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ በ2015 ዓ.ም. ወደ ቀዬአቸው ካልተመለሱ ዕርዳታ አይሰጣችሁም ተብለው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው ወደ ነበሩበት ከመመለስ ይልቅ ወደ ምዕራብ አርማጭሆ መስፈር ይፈልጉ እንደነበር መናገራቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡