ማኅበራዊ
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሚያቀርበውን የምግብ ዕርዳታ አርባ በመቶ ለመቀነስ መገደዱን አስታወቀ

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: September 11, 2024

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በስደተኛ ጣቢያዎች ለተጠለሉ የተለያዩ አገሮች ስደተኞች መቅረብ ከሚገባው የምግብ ዕርዳታ 60 በመቶውን ብቻ ለመስጠት መገደዱን አስታወቀ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዘላታን ሚሊስክ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተቋሙ በቀጣይ ስድስት ወራት ከሚያስፈልገው አጠቃላይ በጀት 341 ሚሊዮን ዶላር እጥረት ስላጋጠመው በአሁን ወቅት ማሰባሰብ እንደሚቻል የታመነበት 90 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

‹‹በዚህን ያህል መጠን የገንዘብ እጥረት ያጋጠመበትን ምክንያት ለይተን ለማቅረብ እየሞከርን ነው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ምክንያቱ ግን ዓለም አቀፋዊ ክስተት ነው ብለዋል።

‹‹እኛ በምግብና በሎጂስቲክስ አቅርቦት ላይ እንደሚሠራ ተቋም፣ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳስቦናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጠ ሰዎች ብዛት 13 ሚሊዮን እንደሆነ ገልጸው፣ ከእዚህ ውስጥ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከስድስት እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ታሳቢ አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

‹‹እነዚህን ታሳቢ ያደረግናቸውን ሰዎች በቋሚነት ማዳረስ አልቻልንም፡፡ ከሦስት እስከ አራት ሚሊዮን ለሚሆኑት ብቻ ነው በየወሩ የምግብ ድጋፍ እያቀረብን ያለነው፤›› ብለዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም እያገኘው ያለው ድጋፍ በመቀነሱ በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች፣ ከዚህ ቀደም ሲያቀርብ ከነበረው መጠን 60 በመቶ የሚሆነውን ያህል ብቻ ለመስጠት መገደዱንም አክለዋል።

‹‹ድጋፉን ለማሻሻል አጋር ተቋማትንና ወዳጆቻችንን እያነጋገርን ነው፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ግን አሳሳቢ ነው፤›› ያሉት ሚሊስክ፣ ባለፈው ሳምንት በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች የሚሠራጭ፣ 13,000 ሜትሪክ ቶን ሩዝ ከኮሪያ መንግሥት ለተቋማቸው የተደረገውን ድጋፍ መረከባቸውን ገልጸዋል፡፡