አቶ ሰለሞን ንጉሴ የኢትዮጰያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳሬክተር

ማኅበራዊ የመድኃኒት ዕዳቸውን የማይከፍሉ የጤና ተቋማት ከባንክ ሒሳባቸው የሚከፍሉበት ሥርዓት መዘርጋቱ ተገለጸ

ሔለን ተስፋዬ

ቀን: September 11, 2024

መድኃኒት በዱቤ ወስደው የማይከፍሉ የጤና ተቋማት ከባንክ ሒሳባቸው እንዲቆረጥባቸው የሚያስገድድ ሥርዓት መዘርጋቱን፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በድጋፍ የሚመጡ መድኃኒቶች በነፃ፣ መደበኛ የሚባሉ መድኃኒቶችን ደግሞ በብድር ለጤና ተቋማት እንደሚያቀርብ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሤ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የጤና ተቋማቱ በዱቤ የሚወስዱትን መድኃኒት ክፍያ በተገቢው ጊዜ ስለማይከፍሉ፣ የሌሎች ተቋማትን አሠራርና ተሞክሮ ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

የጤና ተቋማቱ በተለያዩ ምክንያቶች ዕዳቸውን መክፈል አለመቻላቸውን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ክፍያውን እንዲፈጽሙ ለማድረግ በግዴታ ከባንክ ሒሳባቸው የመቀነስ አሠራር እየተዘረጋ ነው ብለዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን ግብርና ቀረጥ በጊዜ የማይከፍሉ ተቋማትን ከባንክ ሒሳባቸው የመቁረጥ አሠራር እንዳላቸው ገልጸው፣ ይህንን ተሞክሮ መድኃኒት በዱቤ ወስደው በማይከፍሉ የጤና ተቋማት ላይ ለመተግበር መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ኅብረተሰቡ በወቅቱ መድኃኒት እንዲያገኝ ለማድረግ  መሆኑን ገልጸው፣ በሁለት ወራት እንዲከፍሉ ዕድል ተሰጥቷቸው ባልከፈሉት ላይ ከባንክ ሒሳባቸው እንዲቆርጥባቸው የሚደረግበት አሠራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህንን አሠራር ተግባራዊ በማድረግ ኅብረተሰቡ ተገቢውን የመድኃኒት አቅርቦት እንዲያገኝ ለማድረግ እንደ ሁለተኛ አማራጭ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

የብድር ሥርዓቱ የጤና ተቋማቱ ዕዳቸውን ባለመክፈላቸው በ2016 በጀት ዓመት ብቻ 1.9 ቢሊዮን ብርና ያልተከፈለ ዕዳ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡  

ዕዳቸውን ካልከፈሉ የጤና ተቋማት አብዛኛዎቹ ትላልቅ ሆስፒታሎች መሆናቸውንና ጥቁር አንበሳ፣ ዘውዲቱ፣ ጳውሎስ፣ ፈለገ ሕይወትን ጨምሮ 20 ሆስፒታሎችና ሌሎችም የጤና ተቋማት እንዳሉበት ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ ዕዳቸውን ያልከፈሉ የጤና ተቋማትን በሕግ መጠየቅ ሌላኛው መፍትሔ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በዘላቂነት የመድኃኒት ክፍያ ዕዳ እንዳይኖር ለማድረግ ውል የተገባለት የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን፣  የጤና ተቋማትም የመድኃኒት በጀታቸውን በቀጥታ ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉ ይረዳል ብለዋል፡፡

አሠራርን ተግባራዊ ለማድረግ 32 ሆስፒታሎች ተመርጠው ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጸው፣ አሁንም ዕዳ ያለባቸውም ተቋማት በዚህ ሥርዓት መካተታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፣ የጤና ተቋማት ያለባቸው 1.9 ቢሊዮን ብር ዕዳ ስለሆነ፣ መድኃኒት የወሰዱት ደግሞ ከውጭ ምንዛሪ ተመን በፊት በመሆኑ ዕዳቸውን  ቢከፍሉ እንኳ በማሻሻያው ምክንያት ግማሽ ያህል ነው የሚሆነው፡፡