ዜና በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ እስከ ሞት ተፈርዶባቸው የነበሩ የመከላከያ አባላት ይቅርታ ተደረገላቸው

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: September 11, 2024

በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም በሠራዊት አባላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ክስ ተመሥርቶባቸው፣ ክሳቸውም በጦር ፍርድ ቤት (Court-Martial) ታይቶ ከእስር እስከ ሞት ቅጣት ተወስኖባቸው ላለፉት ሦስት ዓመታት በእስር ላይ ለነበሩ 178 የመከላከያ ሠራዊት አባላት ይቅርታ ተደረገላቸው፡፡

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ አንዳንድ የሠራዊት አባላት የተሰጣቸውን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ ወደ ጎን በመተው፣ በሠራዊቱና በሕዝብ ጥቅሞች ላይ ወንጀል ፈጽመዋል ብሏል፡፡

ሚኒስቴሩ በመግለጫው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ አንዳንድ የሠራዊት አባላት የተሰጣቸውን ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ ወደ ጎን በመተው ሠራዊቱና በሕዝብ ጥቅሞች ላይ ወንጀል መፈጸማቸውን አስታውሷል፡፡ ጉዳያቸው በወታደራዊ ፍትሕ ሥርዓቱ አማካይነት ክስ ተመሥርቶባቸው በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው፣ በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች እስከ ሞት ቅጣት ተወስኖባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ 178 የሠራዊት አባላት፣ በፈጸሙት ወንጀል ተፀፅተው የይቅርታ ጥያቄአቸውን ለመንግሥትና ለመከላከያ ሚኒስቴር ማስገባታቸውንም ገልጿል።

በፍርድ ላይ የሚገኙት የሠራዊት አባላት መንግሥት ይቅርታ እንዲያደርግላቸውና ከእስር እንዲፈቱ ጥያቄውን ያቀረበው ‹‹ቅድሚያ ሰብዓዊ መብቶች ለኢትዮጵያ›› የተባለ አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሲሆን፣ ጥያቄውን ለፍትሕ ሚኒስቴርና ለይቅርታ ቦርድ አቅርቦ፣ ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር በግልባጭ አሳውቆ እንደነበር ሪፖርተር ማረጋገጥ ችሏል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቱ ጥያቄውን ያቀረበው በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ማረሚያ ቤቶች እንዲገቡ የተደረጉና ጉዳያቸው ፍርድ ያገኘ፣ እንዲሁም በክስ ሒደት ላይ ያሉ የትግራይ ተወላጆች አዲሱን ዓመት 2017 ዓ.ም. በማስመልከት በይቅርታ እንዲፈቱ ነበር።

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ጥያቄያቸው ለይቅርታ ቦርድ ቀርቦ በአዋጅ ቁጥር 840/2006 አንቀጽ (3) ድንጋጌ መሠረት፣ ይቅርታ ማድረግ የሚያሳካቸውን ዓላማዎች ግምት ውስጥ በማስገባትና የሠራዊት አባላቱ በፈጸሙት ወንጀል መፀፀታቸውም ተመልክቷል።

የመከላከያ ሚኒስቴር የይቅርታ ቦርዱን ውሳኔ መሠረት በማድረግ በመታረም ላይ የነበሩ 178 የሠራዊት አባላት፣ ከጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በይቅርታ ከእስር እንዲለቀቁ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

ሪፖርተር የተመለከተው ለተቋማቱ የተጻፈው ደብዳቤ መነሻ ጉዳዩ በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሥር እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ሲያገለግሉ በነበሩ የትግራይ ተወላጆች፣ አዲሱ ዓመትን በማስመልከት ይቅርታና ምሕረት እንዲሰጣቸውና ክስ እንዲቋረጥላቸው ለመጠየቅ ማመልከቱን ያስረዳል።

ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ በደብዳቤው መንግሥት የነበረውን ሰፊ ችግር ለመፍታት ትልቁን የሰላም ስምምነት ማድረጉን፣ የሰላምና ዕርቅ ሒደቱን ለማገዝ ሲባልም በእስር ላይ የነበሩ የሕወሓትና ለሌሎች የፖለቲካ አመራሮች ይቅርታ መስጠቱን አስታውሷል፡፡

የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ራሳቸው፣ ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ያሉበት ወቅታዊ ከባድ ሁኔታንና የታሰሩበትን ምክንያት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የተወሰነባቸው የሠራዊት አባላት በይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም አዋጅ ቁጥር 840/2006 እና በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 71 ንዑስ አንቀፅ 7፣ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሕግን መሠረት በማድረግ ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን ላይ በመመሥረት ይቅርታ ተደርጎላቸው እንዲለቀቁ ድርጅቱ ጠይቋል። በእስር ላይ ሆነው ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙና በክስ ሒደት ላይ ያሉ አባላት ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ (6ለ) መሠረት ክሱ እንዲነሳላቸውም ጠይቋል።

ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ለዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች፣ በአገሪቱ በሚገኙ 16 የተለያዩ እስር ቤቶች እንደሚገኙ ማረጋገጡንም ሪፖርተር የተመለከተው የአገር በቀል ድርጅቱ ደብዳቤ ያስረዳል።

የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በይቅርታ እንዲለቀቁ የተላለፈው ውሳኔን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቱ ዳይሬክተርና የሕግ ባለሙያ አቶ ተስፋለም በርኸ፣ ‹‹በትክክልም ይቅርታው የተሰጣቸው እኛ ማመልከቻ ያቀረብንላቸው የሠራዊቱ አባላት ናቸው፡፡ እኛ የምናውቀው 153ቱን ነበር፣ በወቅቱ ግን በደብዳቤው እንደጠቀስነው ብዛታቸው ከእዚህም እንደሚያልፍና መንግሥት አጣርቶ ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚችል አስታውሰን ነበር፣ በይቅርታው እጅግ ደስ ብሎናል፤›› ብለዋል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት በፌዴራል መንግሥትና በሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል ሁለት ዓመታት መቃረቡን የሚጠቅሰው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቱ በስምምነቱ ምክንያት ጦርነት ቆሞ ሰላም በመምጣቱ ድጋፉን ቢገልጽም፣ ነገር ግን አሁንም ስምምነቱን መሠረት በማድረግ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት፣ አዋጆችና ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች መሠረት፣ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጉ በርካታ ዜጎች ለተለያዩ የመብት ጥሰቶች ተጋልጠው ይገኛሉ ብሏል።