የቦይንግ አውሮፕላን ማምረቻ ፋብሪካ

ከ 4 ሰአት በፊት

አዲሱ የቦይንግ ሥራ አስኪያጅ ኬሊ ኦርትበርግ የድርጅቱን ማገገም ስጋት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል በሚል የድርጅቱ ሠራተኞች አድማ እንዳይመቱ ተማፀኑ።

የሠራተኞች ማኅበር አድማ መምታትን በተመለከተ የድምፅ አሰጣጥ ለማድረግ ሰዓታት ሲቀሩት ነው ሥራ አስኪያጁ ተማፅኖ ያሰሙት።

የግዙፉ የአቪየሽን ኩባንያ ኃላፊዎች እና የሠራተኞች ማኅበር ተወካዮች በያዝነው ሳምንት በደረሱት ስምምነት መሠረት ቦይንግ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ለሠራተኞቹ 25 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ያደርጋል።

ነገር ግን ይህ ስምምነት በሠራተኞች ማኅበር አባላት አልፀደቀም።

ሠራተኞቹ ይህን ስምምነት ካልተቀበሉት ቀጣዩ እርምጃ የሚሆነው ከሚቀጥለው አርብ ጀምሮ አድማ መምታት ነው።

“ባለፈው ጊዜ በደረሰባችሁ በደል ምክንያት የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን እንዳትሰውት እጠይቃችኋለሁ” ሲሉ ኦርትበርግ ለሠራተኞቻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

“አብረን በመሥራት ወደቀደመ ስማችን እንደምንመለስ አምናለሁ፤ ነገር ግን አድማ ከመታችሁ እያገገመ ያለው ድርጅታችን ይጎዳል” ብለዋል።

ቃል ከተገባው የ25 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ባለፈ የተሻሻለ የጤና ሽፋን እና የጡረታ ጥቅማጥቅምም ከስምምነት ተደርሷል። ስምምነቱ ከፀደቀ ሠራተኞች የ12 ሳምንታት የወሊድ ፈቃድ ሊያገኙም ይችላሉ።

አልፎም ቦይንግ ቀጣዩ የመንገደኞችን አውሮፕላን በሲያትል ግዛት በሚገኘው ፋብሪካው ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን አሳውቋል።

የሠራተኞች ማኅበሩ መጀመሪያ ያቀረበው ዕቅድ ለሠራተኞች 40 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ይደረግ የሚል ነበር።

የቦይንግ ኃላፊዎች እና የማኅበሩ ተወካዮች የደረሱት ስምምነት ከ30 ሺህ በላይ ከሚሆኑት የቦይንግ ኩባንያ ሠራተኞች አዎንታዊ ምላሽ ያገኘ አይመስልም።

የማኅበሩ ኃላፊ እና ዋና ተደራዳሪ የሆኑት ጆን ሆልደን የሠራተኛ ማኅበሩ አባላት በስምምነቱ ደስተኛ ይሁኑ አይሁን ግልፅ አይደለም ብለዋል።

“በጣም ተበሳጭተዋል” ሲሉ ጆን ሆልደን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

አሁን ቦይንግ ኩባንያ እና ሠራተኞቹ የሚተዳደሩበት ማዕቀፍ የተደረሰው በአውሮፓውያኑ 2008 ሲሆን በወቅቱ የስምንት ሳምንታት አድማ ተመትቶ ነበር።

በ2014 ሁለቱ ወገኖች መተዳደሪያውን ለማስቀጠል የተስማሙ ሲሆን ይህ ስምምነት በአውሮፓውያኑ ሐሙስ መስከረም 12 እኩለ ለሊት የአገለግሎት ጊዜው ያበቃል።

ቦይንግ እና ትልቁ የሠራተኞች ማኅበር ስምምነት ላይ ካልደረሱ በተለያዩ ምክንያቶች ስሙ እየጠፋ ለሚገኘው ኩባንያ ትልቅ ኪሳራ ይሆናል።

በአንድ ወቅት ትልቅ የነበረው ስሙ እየጠፋ ያለው ቦይንግ በፋይናንስ ችግሮች ተተብትቦ የሚገኝ ሲሆን ሠራተኞቹ አድማ ከመቱ የአውሮፕላን ማምረቻው ፋብሪካ ሥራ ሊያቆም ይችላል።

ቦይንግ በተለይ ከአምስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በኢንዶኔዥያ አቻው ላይ በደረሱት አደጋዎች ምክንያት ነው ስሙ መጉደፍ የጀመረው።

የኤሮስፔስ ባለሙያ የሆኑት ኢንጂነሩ አዲሱ ሥራ አስኪያጅ ባለፈው ወር ነው የቦይንግ ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት።