ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሶፋ ላይ ቁጭ ብለው

ከ 5 ሰአት በፊት

በበርካቶች ዘንድ “የአፍሪካ አባት” በመባል የሚታወቁት አጼ ኃይለሥላሴ በወታደሮች መፈንቅለ መንግሥት ከተደረገባቸው እነሆ 50 ዓመት ሞላው።

መስከረም 2፤ 1967 ዓ.ም. ነበር የደርግ አባላት የሆኑት ወታደሮች፣ ኢትዮጵያን ለ44 ዓመታት የገዟትን ንጉሥ “. . . ለአገር እና ለሕዝብ ደህንነት ሲባል በዛሬው ዕለት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ከስልጣን ወርደዋል” በማለት የአገዛዛቸው ዘመን ማብቃቱን የነገሯቸው።

አጼ ኃይለሥላሴ በዓለም ዙሪያ በበርካቶች የፋሺስት ኃይሎችን በመጋፈጥ እንደ ጀግና ይቆጠራሉ።

ነገር ግን የአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ከአገሩ ወጥቶ ለአራት ዓመታት እኤአ ከ1936- 1940 ድረስ የጣልያኑን አምባገነን ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ በምዕራባዊቷ አገር ከተማ ባዝ ተቀምጦ ሲቃወም መቆየቱን የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው።

የጣልያን ጦር ኢትዮጵያን በተቆጣጠረበት ወቅት አጼ ኃይለ ሥላሴ እ.አ.አ. ከ1936 እስከ 1940 ድረስ ለአምስት ዓመት ያህል በስደት ኑሯቸውን በእንግሊዟ ባዝ አድርገው ነበር።

የዌስት ኦፍ ኢንግላንድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሾን ናፓታሊ ሶበርስ ለቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ አጼው በስደት እንግሊዝ ውስጥ የቆዩበትን ሁኔታ ተርከዋል።

ስደተኛው ንጉሥ ለንደን ፓዲንግተን ባቡር ጣብያ ሲደርሱ በርካቶች ነበር ወጥተው የተቀበሏቸው።

ይኹን አንጂ ኢትዮጵያን የወረረው ሙሶሊኒን በመቃወም ያሰሙት ጠንካራ ንግግር ለዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ምቾት የሚሰጥ አልሆነም።

ለዚያም ነው አጼ ኃይለሥላሴ ቤተሰቦቻቸውን እና አገልጋዮቻቸውን በመያዝ “ከከተማ ራቅ ብለው ወደሚገኝ አውራጃ እንዲሄዱ” እና ባዝ እንዲቀመጡ የተደረገው።

የስደተኛው ንጉሥ ከነቤተሰቦቻቸው እና ሠራተኞቻቸው ፌይርፊልድ እንዲሄዱ በመደረጉ የከተማው ነዋሪ መነጋገርያ ሆኑ።

ምንም እንኳ ለከተማው ባዳ በመሆናቸው “በቀላሉ የሚታወቁ” ቢሆኑም ንጉሡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ‘ቶሎ ተቀላቅለው” ነበር ይላሉ ፕሮፌሰር ሶበርስ።

“እውነቱን ለመናገር ሕዝብ የሚወዱ ሰው ነበሩ” ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ በአንድ ወቅት ‘ዌስቶን ሱፐር ማሬ ትሮፒካና ሪዞርት’ ለመጠቀም ሰልፍ ይዘው ሲታዩ እንዲቀድሙ ቢነገራቸውም አሻፈረኝ ብለው ሰልፋቸውን ይዘው መቆየታቸውን ይጠቅሳሉ።

ፕሮፌሰሩ፣ አምባገነኑ የጣልያን መንግሥት ኢትዮጵያን መውረሩን ተከትሎ ንጉሡ አገራቸውን ጥለው መሄድ አልፈለጉም ነበር ሲሉ የኃይለሥላሴ የቀድሞ መኖርያ ተንከባካቢዎች መናገራቸውን ይጠቅሳሉ።

“ነገር ግን ኢትዮጵያውያን በጦርና ጎራዴ ብቻ ያንን ወራሪ ኃይል መመከት እንደማይችሉ ተረዱ። ስለዚህም ወደ ምዕራቡ ዓለም መጥተው፣ ለነጻነታቸው መታገልን መረጡ” ይላሉ ፕሮፌሰር ሶበር።

አጼ ኃይለሥላሴ በስደት ባሉበት በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) አቤቱታ አቀረቡ።

“ዛሬ ተረኞቹ እኛ ከሆንን ነገ ደግሞ እናንተ ትሆናላችሁ የሚል በጣም መሳጭ ንግግር ነበር ያደረጉት” ይላሉ ፕሮፌሰር ሶበርስ።

አጼ ኃይለ ሥላሴ እኤአ በ1938 በለንደን አሌክሳንድራ ቤተ መንግሥትን ከልጃቸው ከልዕልት ተናኘወርቅ ጋር ሲጎበኙ

በዚህ ወቅት ዩናይትድ ኪንግደም “ሙሶሊኒን በእቅፏ ይዛ እሹሩሩ ትል ነበር” የሚሉት ምሁሩ ንጉሡ ወደ እንግሊዝ በመጡበት ወቅት በርካቶች ፓዲንግተን ባቡር ጣብያ ወጥተውእንደተቀበሏቸው ሲያስረዱ “በጣም ታዋቂ ነበሩ፤ ለብሪታንያ መንግሥት ደግሞ ይህ ምቾት የሚነሳ ነበር፤ ለዚያ ነው ድምጻቸውን አጥፍተው ራቅ ወዳለ አውራጃ እንዲሄዱ የተነገራቸው” ይላሉ።

ንጉሡ ለኑሮ ባዝን የመረጡበት ምክንያት በኢትዮጵያ በጦርነት ላይ ሳሉ በጣልያን የመርዝ ጋዝ፣ ኬሚካል፣ የተቃጠለውን እጃቸውን ለማከም በከተማዋ የሚገኘውን የመዋኛ ስፍራ ለመጠቀም በመፈለጋቸው ነው።

በባዝ ፌይርፊልድ ሐውስ ቤት ገዝተው ከእነ ልጆቻቸው፣ ሰራተኞቻቸው፣ ቀሳውስቶቻቸው እና ሚኒስትሮቻቸው ገቡ።

“በባዝ የኖሩት እጅግ ሰብሰብ ብለው ነበር፤ ስለዚህ በጣም ይለዩ እና ይታወቁ ነበር” ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

የንጉሡ ልጆች ከአካባቢው ማኅበረሰብ ልጆች ጋር መጫወት፤ እራት መገባበዝም ጀመሩ።

በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ንጉሡን ከሚያስታውሱባቸው ነገሮች አንዱ “ሰዓት አክባሪነታቸው” ነው።

“አንዳንድ ሰዎች ለሥራ እንዳረፈዱ የሚያውቁት ንጉሡ ምን ያህል በአውራ ጎዳናው ላይ ርቀው እንደተጓዙ በማየት ነበር” ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

አጼ ኃይለ ሥላሴ እኤአ በ1954 ከባዝ ከተማ ከንቲባ ዊሊያም ጋሎፕ ጋር

አጼ ኃይለሥላሴ ምንም እንኳ ባዝ በሚገኘው መኖርያ ቤታቸው ምድር ቤት ደቦል አንበሳ ነበራቸው የሚል የሐሰት ወሬ ቢነዛም፣ በባዝ ጎዳናዎች ላይ ግን ከውሻቸው ሉሉ ጋር ሲንሸራሸሩ ይታዩ ነበር።

የከተማዋ ጋዜጣም የየዕለቱን የንጉሡን ውሎ እቅድ ያትም የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም በእርሳቸው ላይ የሚነገሩ ሐሰተኛ ወሬዎችን “ጢማቸው ነጭ የሆነው ከብስጭት የተነሳ ነው” የሚለውን ጨምሮ አስተባብሎ አትሞ ያውቃል።

አጼ ኃይለሥላሴ በከተማዋ በሚገኙ መዝናኛ ስፍራዎች ይዝናኑ፣ የሕዝብ መዋኛ ገንዳዎች ውስጥ ይዋኙም ነበር።

የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ መዋኛ ገንዳ በሄዱበት ወቅት የነበረውን ሠልፍ ሳይጥሱ እንደማንኛውም ግለሰብ ሰልፋቸውን ጠብቀው በመስተናገዳቸው ያስታውሷቸዋል።

“አይሆንም፣ በጭራሽ እንደማንኛውም ሰው መሰለፍ እፈለጋለሁ ባይ ናቸው” ይላሉ ፕሮፌሰር ሶበርስ።

ንጉሡ በባዝ ቆይታቸው ወቅት በአገራቸው እየሆነ ያለውን አልረሱም።

በቤታቸው ሞግዚት የነበረችው ሩት ሀስኪንስ አንድ ቀን የሆነ ሰው በራዲዮ ግራሙ የኢትዮጵያን ጦርነት ዜና መክፈቱን ታስታውሳለች።

“የቦምብ የተኩስ ድምጽ ነበር፣ ሰዎች ይጮሁና ያለቅሱ ነበር። ወደ ንጉሡ ዞራ ስትመለከትም እንባ በፊታቸው ላይ ኮለል እያለ ሲወርድ ተመለከተች።”

ፕሮፌሰር ሶበርስ አክለውም ሞግዚቷ እንባቸው ከፊታቸው ወርዶ በኬሚካል አረር የተቃጠለው እጃቸው ላይ ሲነጥር መመልከቷን ታስታውሳለች።

“እርሷ እንደምትለው ይህ ትውስታዋ ሁልጊዜም አብሯት ይኖራል” ሲሉ አክለዋል።

እኤአ በ1939 ሙሶሊኒ ከሂትለር ጋር አጋር ሆነ።

አጼ ኃይለ ሥላሴ በባዝ ከተማ ፌይርፊልድ ሐውስ በስደት ኖረዋል

አጼ ኃይለ ሥላሴም በ1940 ብሪታንያ አምባገነኑን መንግሥት ለማስወገድ ካገዘቻቸው በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።

ንጉሡ በባዝ የነበራቸውን የስደት ቆይታ አልረሱም፤ ከቤተ መንግሥቶቻቸው አንዱን በብሪታንያ ከተማ በሚገኘው ፌይርፊልድ ሐውስ ሲሉ ሰየሙ።

በአሁኑ ወቅት በባዝ የሚገኘው ፌይርፊልድ ሐውስ በየጊዜው ጎብኝዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን በአስጎብኚ ታግዞ ቤቱን እና ቅርሳ ቅርሶችን መጎብኘትም ይቻላል።