የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቲ ፕሬዝዳንት [ዶ/ር] አሸብር ወልደጊዮርጊስ
የምስሉ መግለጫ,ፕሬዝደንቱ በቅርቡ “ከኃላፊነታቸው የመልቀቅ” ሐሳብ እንደሌላቸው መናገራቸው ይታወሳል

ከ 2 ሰአት በፊት

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቲ ፕሬዝዳንት [ዶ/ር] አሸብር ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ አራት አመራሮች በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎች ተያያዝ ጉዳዮች ክስ ተመሰረተባቸው።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቲም ከተከሳሾቹ መካከል ነው።

ክሱን የመሰረቱት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ናቸው።

በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በተከፈተው የክስ መዝገብ አራት ግለሰቦች እና አንድ ተቋም በተከሳሽነት ስማቸው ተጠቅሷል።

እነዚህ ተከሳሾች የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቲ፣ፕሬዝዳንቱ አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ ዐቃቤ ነዋይዋ [ዶ/ር] ኤደን አሸናፊ፣ ዋና ፀሐፊው አቶ ዳዊት አስፋው እና ምክትል ፀሐፊው አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ናቸው።

በከሳሾቹ ጠበቆች በኩል ክሱ የቀረበለት የፌደራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት አራድ ምድብ ችሎት ኮሚቴው፤ ግንቦት 5 እና ሰኔ 4፤ 2016 ዓ.ም. ያካሄዳቸው ጠቅላላ ጉባኤዎች እና ውሳኔዎች እንዲታገዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ አያሌው ቢታኔ “ከፓሪስ ኦሊምፒክ ጋር በተያያዘ [ተከሳሾቹ] ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሰማርተዋል ብለን እንጠረጥራለን። የወንጀል ተጠያቂነቱ እንዳለ ሆኖ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም ኦሊምፒክ ኮሚቴውን [በዝብዘዋል]” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቃው አክለው “ደብዳቤ ስለተጻፈ ብቻ የማይመለከተው ሰው [ወደ ፓሪስ] ይሄድ ነበር” ብለዋል።

“ተቋሙ እስካሁን ድረስ ኦዲት አልተደረገም” የሚሉት ጠበቃ አያሌው፤ “የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ደብዳቤዎች ምላሽ አልሰጡም፤ ፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትም ኦዲት እንዲደረግ ከአንድም ሁለት ጊዜ ደብዳቤ ጽፎ ኦሊምፒክ ኮሚቲው ፈቃደኛ አልሆነም” ሲሉ አስረድተዋል።

“ስለዚህ በገለልተኛ ተቋም ኦዲት ተደረጎ በሚገኘው ግኝት መሰረት ኃላፊነት ይረጋገጥ ነው” ሲሉ የሚጠይቁትን ዳኝነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቲ አርማ

ከዚህ በተጨማሪ “ግንቦት አምስት እና ሰኔ አራት ላይ የተደረጉት አስቸኳይ እና መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተወሰኑ ውሳኔዎች የኦሊምፒክ ኮሚቲውን ህግ እና ስርዓት ያልተከተሉ እና ሕገ ወጥ ስለሆኑ በሚል እንዲሻሩ ነው [የጠየቅነው]” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ለእነዚህ ምክንያት ናቸው ያልናቸው ዝርዝር ነገሮች አሉ” የሚሉት ጠበቃ አያሌው፤ “አንደኛ [ዶ/ር] አሸብር፣ [ዶ/ር] ኤደን እና አቶ ዳዊት ለሶስተኛ ጊዜ ነው በሕገ ወጥ መንገድ የተመረጡት” ሲሉ የመጀመሪያውን ምክንያት ይጠቅሳሉ።

የኦሊምፒክ ኮሚቴ የስራ ዘመን ሁለት ዓመት መሆኑን የሚያነሱት ጠበቃው፤ “ነገር ግን በሕገ ወጥ መልኩ እነሱ ለሶስተኛ ጊዜ ተመርጠዋል፤ የተመረጡትም በድብቅ በተፈጸመ ጉባኤ ነው” ይላሉ።

በተጨማሪም “በሕግ የመመረጥም ሆነ የመምረጥ ሥልጣን ሳይኖራቸው አንዳንድ ግለሰቦች ተመራጭም መራጭም ሆነው በመግባታቸው ሕገ ወጥ ያደርገዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ጠቅላላ ጉባኤውም መጠራት ከነበረበት በጣም ባጠረ ጊዜ ነው የተጠራው ስለዚህ ይሄም ሕገ ወጥ ያደርገዋል” ሲሉ አክለዋል።

ይህ አቤቱታ የቀረበለት ፍርድ ቤቱ ባለፈው ሰኞ ጷጉሜ 4፤ 2016 ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በዚህ የችሎት ውሎ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ግንቦት 5 እና ሰኔ 4፤ 2016 ዓ.ም. የተካሄዱት አስቸኳይ እና መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤዎች እና የተላለፉ ውሳኔዎች ታግደው እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ሰኔ 4 የተመረጠው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቲ ሥራ አስፈጻሚ ምርጫም “ታግዶ እንዲቆይ” አዝዟል። እነዚህን ትዕዛዞች የማስፈጸም ኃላፊነት ለባህል እና ስፖርት ሚኒስትር በፍርድ ቤት ተሰጥቷል።

በአንደኛ ተከሳሽ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቲ ስም የተከፈቱ የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች “በከሳሾች እና በተከሳሾች መካከል ባለው ክርክር ላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ሳይንቀሳቀስ ታግዶ እንዲቆይ” ችሎቱ አዝዟል።

ባለፈው ወር በተካሄደው የ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ውጤት አመርቂ አለመሆኑን ተከትሎ የኦሊምፒክ ኮሚቴው በተለይ ፕሬዝደንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ ትችት ሲቀርብባቸው ነበር።

ፕሬዝደንቱ በቅርቡ በመንግሥት ቴሌቪዥን ቀርበው “ከኃላፊነታቸው የመልቀቅ” ሐሳብ እንደሌላቸው መናገራቸው ይታወሳል።