የፊዚክስ ሊቁ ሚቺዮ ካኩ

ከ 5 ሰአት በፊት

አሜሪካዊው የፊዚክስ ሊቅ እና ፀሐፊ ሚቺዮ ካኩ የኳንተም ዘመን የወደፊት ሕይወታችንን እንደሚወስን እርግጠኛ ናቸው።

የ77 ዓመቱ ካኩ በቲዎረቲካል ፊዚክስ ዘርፍ እና በሳይንሳዊ ኮሙዩኒኬሽን ስመ ገናና ለመሆን በቅተዋል።

ኒው ዮርክ በሚገኘው ሲቲ ዩኒቨርሲቲ የቲዎረቲካል ፊዚክስ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ “ኳንተም ሱፐርማሲ” የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲም ናቸው።

ካኩ የኳንተም ዘመን እና ኮምፒውተሮች በሽታን ከማጥፋት ጀምሮ እየጨመረ ያለውን ሕዝብ ቁጥር እንዴት መመገብ ይቻላል ለሚሉት የሰው ልጅ ጥያቄዎች ሥር ነቀል መፍትሄዎችን እንደሚያስገኝ ያምናሉ።

የዘር ሐረጋቸው ከጃፓን የሚመዘዘው የፊዚክስ ሊቁ እንደሚሉት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በሰው ልጅ ላይ ስጋት እንደሚፈጥር ይገምታሉ…ሆኖም አሁንም ለመቆጣጠር የሚሆን በቂ ጊዜ አለ።

ቢቢሲ መቀመጫቸውን በኒው ዮርክ ያደረጉትን ካኩን ጋብዞ ስለወደፊቱ በመተንበይ በመጽሐፋቸው ስለከተቧቸው ጉዳዮች ጠይቋቸዋል።

ዓለም ዲጂታል ሳይሆን ኳንተም አዕምሮ ነው ያላት፡ ካኩ

ቢቢሲ፡ በጽሑፎችህ ውስጥ የሰው ልጅ “ሦስት አዕምሮዎች” አሉት የሚለውን ሐሳብ አንስተሃል፤ ይህን ሃሳብ ማብራራት ትችላለህ?

ካኩ፡ የሰውን አንጎል ስትመረምር ቢያንስ ሦስት አካላት እንዳሉ እንገነዘባለን። የአንጎላችን የጀርባ ክፍል በባለሦስት አውታር (3ዲ) ያለንበትን እንድናውቅ የሚረዳ እና የአደንን ቅርጽ የሚለይ የአንጎል ክፍል ነው። እየተለወጠን ስንመጣ አንጎልም ወደፊት አቅጣጫ መሻሻል ጀመረ።

ከዚያም መካከለኛው የአንጎል ክፍል አለን። እሱ ደግሞ ስሜትን የሚቆጣጠር የ“ዝንጀሮ” አንጎል ክፍል ሲሆን፣ ከማኅበራዊ ትስስሮቻችን ጋር የሚገናኝ ነው። ከእኛ በላይ ወይም በታች ያለው ማን ነው ያለው የሚለውን የሚመለከት አንጎል ነው። ያ ማኅበራዊ አዕምሮ ነው።

ከዚያ ደግሞ የአንጎል የፊተኛው ክፍል አለ። ይህ የአንጎል ክፍል የጊዜ ማሽን ነው። የወደፊቱን ያያል። የወደፊቱን ሊመስል የሚችል አስመስሎ ያለማቋረጥ ይሠራል።

ቢቢሲ፡ ሁላችንም የወደፊቱን ለማየት ተመሳሳይ ችሎታ ሊኖረን ይችላል?

ካኩ፡ የአንድን የተራ ሰው አንጎል ከሊቅ አንጎል የሚለየው ምንድን ነው? ተራው የሰው አዕምሮ እንዳገኘው ዕድል ተጠቃሚ ነው። በፊቱ ፊት ለፊት ያሉትን ዕድሎች ብቻ ይመለከታል። በጣም ትንሽ ዕቅድ ያወጣል። ለምሳሌ ተራ ወንጀለኞች የሚያዩትን ብቻ ነው የሚሰርቁት። ዕቅድ የላቸውም። ታላላቅ አሳቢዎች ይህንን የጊዜ ማሽን ይለማመዳሉ። የወደፊቱን አስመስለው ይከውናሉ። የተፈጥሮን ሕግጋት ስለሚያውቁ ስለወደፊት መዘጋጀት ይጀምራሉ።

አንድ ሰው የተወሰኑ ነገሮችን ስለሚያውቅ ብቻ ብልህ ነው ብለን ብናስብ ግን ይህ የዕውቀት መለኪያ አይደለም። የማሰብ ችሎታ ዋናው ቁም ነገር የወደፊቱን ማየት ነው። ይህ ደግሞ የሚከወነው በአንጎል የፊተኛው ክፍል ነው። የቀን ህልሞች ያልማል። አሁን የሌሉትን ግን ወደፊት የሚፈጠሩትን ሁኔታዎች ያለማቋረጥ ይፈጥራል ያስመስላል። ወደፊት፣ ለመቶ ዓመታት ወደፊት ያስባል። ይህ ተራ አንጎል የሚያደርገው ነገር አይደለም። ልዕለ አንጎል፣ ትልቅ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሰዎችን አንጎል የጊዜ ማሽን አንጎል ነው የምለው ለዚህ ነው።

ካኩ ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበ መፍሐፍ ደራሲ እና የፊዚክስ ሊቅ ነው

ቢቢሲ፡ በዚህ የወደፊቱን የመመልከት ሐሳብ ውስጥ በሚቀጥሉት 100 ዓመታት የምናገኘው ታላቅ ግኝት ምን ሊሆን ይችላል?

ካኩ፡ ያለፉት ጊዜያት ትልቆቹ ግኝቶች በጣም ጥቃቅን እና ትላልቅ ነገሮችን መተንተን ነው። በእርግጥ ትናንሹ ነገር የምንለው የሰው አንጎል እና ዘረመል ነው። በጣም ትልቅ የሆነው ነገር ደግሞ የቢግ ባንግ ቲዎሪ ነው።

አሁን ደግሞ የኳንተም ቲዎሪን በዩኒቨርስ ላይ እየተጠቀምን ነው። ቀጣዩ ትልቅ እርምጃ የሚሆነው እነዚህን ሁለቱን ስንዋሃድ ነው። ዘረመልን እና የሰው አንጎልን ለመረዳት የኳንተም ቲዎሪን ይጠቀሙ።

እዚህ ጋር ነው ኳንተም ኮምፒውተሮች የሚመጡት። ተፈጥሮ በተወሰነ መልኩ ኳንተም ኮምፒውተር ናት። ኮምፒውተር የሚሠራው አንድ እና ዜሮን ተጠቅሞ ነው። ይህ ደግሞ የተፈጥሮ ቋንቋ አይደለም። ተፈጥሮ በዜሮ እና በአንድ አታስብም። ይህ የዲጂታል አዕምሮ አሠራር ነው።

ተፈጥሮ የኳንተም አዕምሮ አላት። አተሞችን፣ ኤሌክትሮኖችን፣ የፎቶኒክ ቅንጣቶችን የሚረዳ አዕምሮ ነው ያላት። ይህ የዩኒቨርስ ቋንቋ ነው። ቀጣዩ ትልቅ እርምጃም ይህ ይሆናል።

ቢቢሲ፡ ይህ ትልቅ እርምጃ በፊዚክስ ብቻ የሚሳካ ነው ወይስ ሌሎች እንደ ህክምና ያሉ ዘርፎችን ያካትታል?

ካኩ፡ አሁን ያለው ህክምና በሙከራ እና ስህተቶችን በማረም የሚሠራ ነው። መድኃኒት ይሠራል? እንላለን። ካልሆነ ሌላ መድሃኒት እንሞክራለን።

ብዙ አስደናቂ መድኃኒቶች በአጋጣሚ የተገኙ ናቸው። የኳንተም ቲዎሪ ካለ ግን ሞለኪውሉን በዐይነ ሕሊና ማየት እንችላለን። ሞለኪውሎች እንዴት እንደሚሠሩ ማየት ይችላል።

ከዚያ ከባዶ በመነሳት አዳዲስ መድኃኒቶችን ለመፍጠር ሁሉንም ጥያቄዎች መመለስ መጀመር ይችላሉ። ይህ ማለት መድኃኒት ቀማሚዎች ከሥራ ውጪ ይሆናሉ፤ ከዚህ በኋላ መድኃኒት ቀማሚዎች አያስፈልጉንም ማለት ነው?

የወደፊቶቹ የመድኃኒት ቀማሚዎች የኬሚካላዊ ግብረመልሶችን ለመረዳት የኳንተም ቲዎሪን ይጠቀማሉ። የወደፊቶቹ ባዮሎጂስቶች ዘረመልን ለመረዳት ኳንተም ኮምፒውተሮችን ይጠቀማሉ። ኬሚስትሪን ወይንም ባዮሎጂን ብቻ የሚጠቀሙ ዶክተሮች እና ሳይንቲስቶች ከሥራ ውጭ ይሆናሉ። ምክንያቱም መጪው ጊዜ የኳንተም ሜካኒክ ይሆናል። መድኃኒት ለመሥራት ኳንተም ሜካኒክን እንጠቀማለን።

ቢቢሲ፡ አንሞትም?…ያኔ ካንሰር አይኖርም ማለት ነው?

ካኩ፡ በኮምፒዩተር እገዛ ካንሰርን ማዳን እንችላለን። ምልክቱ ከመታየቱ በፊት የታካሚውን የካንሰር በሽታ እንገምታለን። ለምሳሌ ወደ መጸዳጃ ቤት በመሄድ ብቻ ዘረመል ይነበብ እና ወደፊት እንዴት እንደሚሆን ይገመታል። ምልክቱ ከመታየቱ ከአስር ዓመታት በፊት የካንሰሩን ዘረመል ይናገራል።

በአሜሪካ ካንሰርን ለመመርመር የደም ምርመራ በማድረግ ማወቅ ይቻላል። የደም ምርመራው ካንሰር መኖሩን ወይም አለመኖሩን ያሳያል። ዕጢ የሚለው ቃል ከቋንቋችን ይጠፋል። ካንሰር ላይም ተመሳሳይ ሁኔታ ይከሰታል።

የኳንተም ዘም ለካንሰር መፍትሔ የበለጠ ያቀርበናል

ቢቢሲ፡ ኢንተርኔትም ጊዜ ያለፈበት ይሆናል። በአዕምሮ፣ በአንጎል… መገናኘት እንችላለን ብለሃል።

ካኩ፡ የወደፊቱ ኢንተርኔት ዲጂታል አይሆንም። ዲጂታል በጣም ቀርፋፋ እና ኋላ ቀር ነው። የወደፊቱ ኢንተርኔት ኳንተም ይሆን እና ከአንጎል ጋር ይዋሃዳል። ብሬይኔት (ብሬይን እና ኢንተርኔት የሚሉ የእንግሊዘኛ ቃላትን በማዋሃድ የተገኘ ነው) ተብሎም ይጠራል። አንድ ሰው ሲያስብ ሃሳቦቹ በዓለም ዙሪያ ተላልፈው ከሌሎች ነገሮች ጋር ይተሳሰራሉ። ስለዚህ ከአሁን በኋላ የግድ ሽቦዎችን እና መሰል ነገሮችን አንጠቀምም። በቀላሉ እናስባለን ብሬይኔት የቀረውን ሁሉ ያከናውናል።

ቢቢሲ፡ ብዙ ሳይንቲስቶች ስለ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ አስተውሎት) አደጋዎችን አስጠንቅቀዋል… በዚህ ዙሪያ የእርስዎ ዕይታ ምንድነው?

ካኩ፡ አንዳንድ ሰዎች አንድ ቀን ማሽኖቻችን በጣም የሠለጠኑ ይሆናሉ ይላሉ። ስጋትም ይደቀኑብናል። ሰዎችን የሚያጋጥሟቸው ሦስት አደጋዎች አሉ።

የኑክሌር ጦርነት ስጋት፣ የባዮሎጂካል ጦር መሳሪያዎች እና የዓለም ሙቀት መጨመር ስጋቶች ናቸው። በሰው ልጅ ህልውና ላይ አራተኛውን ስጋት መጨመር ካለብን ደግሞ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ይሆናል። በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚፈጠሩ ሁለት መሠረታዊ ስጋቶች ቢኖሩም እነሱ በጣም የተለዩ ናቸው።

የመጀመሪያው ስጋት በጣም ፈጣን ነው። ሰው አልባ አውሮፕላኖች የሰውን ፊት፣ የሰውን አካል መለየት ቢችሉም ሰዎችን ሳይለዩ እየገደሉ ነው። ስለዚህ አውቶማቲክ የግድያ ማሽን ይኖረናል። የሚበር፣ አካባቢውን የሚከታተል፣ የሰውን መልክ የሚለይ እና የሚገድል ማሽን አለ።

ይህ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሚሆን ነው። ትልቁ ስጋት በረጅም ጊዜ የሚከሰተው ነው። ሁለተኛው ስጋት የሰው ልጅን የማሰብ ችሎታ መቅረብ የሚጀምር አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሲኖረን ነው።

አሁን ወደዚያ ደረጃ ከመድረሳችን በፊት ብዙ ይቀረናል። ውሎ አድሮ ግን ሮቦቶቻችን እንደ አይጥ እና ጥንቸል ብልህ ይሆናሉ። ከዚያም እንደ ውሻ ወይም ድመት፤ በመጨረሻም እንደ ዝንጀሮ። ይህ ከሆነ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ምክንያቱም ጦጣዎች በጦጣ እና በሰው መካከል ያለውን ልዩነት ይረዳሉ።

ማን ያውቃል እኔ እንደማስበው ከሆነ በ100 ዓመታት ውስጥ ከሰዎች የማይለዩ ሮቦቶች ይኖሩናል። በዚያን ጊዜ የራሳቸው አስተሳሰብ እንደሌላቸው ማረጋገጥ እና እኛ ላይ ፊታቸውን እንደማያዞሩ ማረጋገጥ አለብን። ስለመግደል ማሰብ ሲጀምሩ ከጥቅም ውጪ የሚያደርጋቸውን ቺፕ በአንጎላቸው ውስጥ ማስቀመጥ አለብን።

እዚያ ደረጃ ከመድረሳችን በፊት ብዙ ጊዜ ያለን ይመስለኛል። የቅርብ ጊዜው አደጋው ያለአንዳች ልዩነት የሚገድሉት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ናቸው።

አይቢኤም እና ጉገልን የመሰሉ ተቋማት እና ቻይናን መሳሰሉ አገራት ኳንተም ኮምፒውተርን ሠርተዋል

ቢቢሲ፡ ኳንተም ኮምፒውተሮች የወደፊት ሕይወታችንን እንዴት ሊወስኑ ይችላሉ?

ካኩ፡ አንዳንድ ሰዎች የኳንተም አብዮት በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ በሽታን ያስወግዳል ይላሉ። ኳንተም ኮምፒውተሮች አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ ይችላሉ። የእርጅና ሂደትን ይፈታሉ ብዬ አስባለሁ። ወደፊት በእርጅና ምክንያት ላንሞት እንችል ይሆናል።

የእርጅናን ችግሮች መፍታት እንችል ይሆናል። የግለሰቦች ሁኔታ በኳንተም ኮምፒዩተሮች አይድንም። ምክንያቱም የሰዎች ትስስር በማኅበራዊ መስተጋብር ጋር በጣም የተቆራኘ ስለሆነ ሰዎችን በማያቋርጥ ጦርነት ሳይሆን በሠላም ለማኖር የተለየ መንገድ ያስፈልገናል።

ቢቢሲ፡ በኳንተም ዘመን ማይፈቱ ችግሮች የትኞቹ ናቸው?

ካኩ፡ እኔ እንደማስበው ከሆነ ኮምፒውተሮች ከአንድ ነገር በስተቀር ብዙ ችግሮችን ይፈታሉ። ኳንተም ኮምፒውተሮች የዓለም ሙቀት መጨመር ችግርን ለመፍታት ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ። የኑክሌር ዝቃጭን የማይፈጥሩ የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎችን ይሰጡናል። እንደ ካንሰር፣ አልዛይመር እና ፓርኪንሰንስ ላሉ በሽታዎች መፍትሔ ከመስጠት በተጨማሪ አዳዲስ የሐብት ምንጮችን እንደሚፈጥሩ ተስፋ አድርጋለሁ።

ኳንተም ኮምፒውተሮች በቅርቡ የማይፈቱት አንድ ነገር ቢኖር እንደ ጦርነት፣ ቅናት ያሉትን የሰውን ልጅ ድክመቶች ነው።

ዝግመተ ለውጥ የመታገል አቅም ሰጥቶ የእኛ የሆነውን ነገር ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም ሰጥቶናል። ዝግመተ ለውጥ ብዙ ባህሪያትን ሰጥቶናል። አንዳንዶቹ ጠቃሚ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ አይጠቅሙም። ዝግመተ ለውጥ ግድ የለውም። ዝግመተ ለውጥ በሕይወት ሊተርፉ የሚችሉ ሰዎችን መፍጠር ይፈልጋል። መትረፍ ማለት ደግሞ ሌሎች ወገኖችን መግደል ከሆነም መደረግ ይኖርበታል። ስለዚህ በሰዎች ውስጥ ብዙ ጉድለቶች አሉ።