የፍርድ ሂደቱን የተቃወሙ ሰዎች ድምፃቸውን ለማሰማት ችሎቱ አካባቢ ተገኝተው ነበር

ከ 4 ሰአት በፊት

አራት የጥቁር አሜሪካዊያን መብት ተሟጋቾች ያልተመዘገቡ የሩሲያ ሰላዮች ሆነው ለማገልገል አሲረዋል በሚል ጥፋተኛ ሆነው እንደተገኙ የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የ82 ዓመቱ ኦማሊ የሺጥላ፣ የ78 ዓመቱ ፔኒ ሄስ፣ የ43 ዓመቱ ጄሴ ኔቬል እና የ38 ዓመቱ ኦገስተስ ሮሜይን ናቸው ጥፋተኛ የተባሉት።

ምንም እንኳ ግለሰቦቹ ጥፋተኛ ቢባሉም ቅጣታቸው ምን እንደሆነ ገና አልታወቀም። ነገር ግን ለአምስት ዓመታት ከፍተኛ ጥበቃ ወዳለበት እስር ቤት ሊላኩ እንደሚችሉ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ፍሎሪዳ ግዛት የሚገኘው ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ለመሰለል ቢያሴሩም የውጭ መንግሥት ሰላይ ሆነው ከባድ ጥፋት አልፈፀሙም ብሏል።

በወላጆቻቸው የተሰጣቸውን ጆሴፍ ዋለር የተሰኘ ስም ጥለው ኦማሊ የሺጥላ ተብለው የሚታወቁት ጥቁር አሜሪካዊ፤ የአፍሪካን ፒፕልስ ሶሻሊስት ፓርቲ እና የኡሁሩ ሙቭመንት መሥራች ናቸው።

ሄስ እና ኔቬል ደግሞ የድርጅቱ አጋር ነጭ አሜሪካዊያን ናቸው።ሮሜይንም ጆርጂያ የሚገኘው ብላክ ሐመር የተሰኘ የመብት ተሟጋች ቡድን መሪ ነው።

አቃቤ ሕግ እንደሚለው አራቱ ግለሰቦች ከአውሮፓውያኑ 2015 እስከ 2022 ባሉት ጊዜያት ለሩሲያ መንግሥት የተለያዩ ድርጊቶችን ፈፅመው አሌክሳንደር አዮኖቭ ከተባለው ሩሲያዊ ገንዘብ ተቀብለዋል።

አዮኖቭ እኚህን የጥቁር አሜሪካዊያን መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተጠቅሞ ስለሩሲያ ፖለቲካ አመለካከት፣ ስለዩክሬን ጦርነት እና ስለሌሎች ጉዳዮች አቋሙን አንፀባርቋል ይላል የአቃቤ ሕግ ክስ።

ፍትሕ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ከአዮኖቭ ድርጊት ጀርባ የሩሲያው ደኅንነት መሥሪያ ቤት የሆነው ፌዴራል ሴኪዩሪቲ ሰርቪስ (ኤፍኤስቢ) አለበት ብሏል።

አዮኖቭ እና ሁለት የኤፍኤስቢ ሰላዮች ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ክስ ቢመሰረትባቸውም በቁጥጥር ሥር ግን አልዋሉም።

የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር እንደሚለው ሁሉም ተከሳሾች አዮኖቭ ለሩሲያ መንግሥት እንደሚሠራ ያውቁ ነበር።

የፔኒ ሄስ ጠበቃ የሆነው ሌናርድ ጉድማን አራቱ ግለሰቦች ክስ የተመሰረተባቸው ለሩሲያ የሚወግን ድምፃቸውን ለማፈን ነው ብለዋል። “ይህ የፍርድ ሂደት የመናገር ነፃነት ጉዳይ ነው” ሲሉ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

የሺጥላ ከብይኑ በኋላ “ትልቁ ነገር ከጥቁር ሕዝብ ውጭ ለማንም ሰርታችኋል ብለው እኛ ላይ ፍርድ መስጠት አለመቻላቸው ነው” ማለታቸውን የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

“ለጥቁር ሕዝብ በመሥራቴ ለመከሰስም ሆነ ጥፋተኛ ሆኜ ለመገኘት ዝግጁ ነኝ።”

አራቱ ግለሰቦች ብይኑን በመቃወም ይግባኝ ሊጠይቁ እንደሚችሉ ተወካዮቻቸው አስታውቀዋል።