ቢራቢሮ

ከ 4 ሰአት በፊት

በስሪላንካ ከብሔራዊ ፓርክ 92 ብርቅዬ ቢራቢሮዎችን ጨምሮ ሌሎች ጥቃትን ነብሳትን በህገ ወጥ መንገድ ለማዘዋወር የሞከሩት ጣልያናዊ አባት እና ልጅ 60 ሚሊዮን የስሪላንካ ሩፒ ወይም 200 ሺህ ዶላር እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው።

የ68 ዓመቱ አባት ሉዊጂ ፌራሪ እና የ28 ዓመት ልጁ ማቲያ ባለፈው ግንቦት ነው ከያላ ብሔራዊ ፓርል ቢራቢሮዎቹን እና ሌሎች ጥቃትን ነብሳትን በብልቃጥ ይዘው ለመውጣት ሲሞክሩ በጥበቃዎች የተያዙት።

አባት እና ልጅ ነብሳቶቹን ለመያዝ መሳቢያዎችን የተጠቀሙ ሲሆን በተጨማሪም ብልቃጡን የኬሚካል ይዘት ያለው እንስሳቶቹን ጠብቆ ለማቆየት የሚረዳ ቅባት መጠቀማቸውን የተደረገው ምርመራ አመላክቷል።

ይህንንም ተከትሎ ነብሳቱን በህገ ወጥ መንገድ በመሰብሰብ፣ በመያዝ እና በማጓጓዝ ባለፈው ወር ተከሰው በሀገሪቱ ታሪክ ፓርኮች ውስጥ ከተፈጽሙ ወንጀሎች ከፍተኛ የሆነው ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

የፓርኩ ጥበቃ የሆነው ሱጂዋ ኒሻንታ ለቢቢሲ በሰጠው ቃል፤ አንድ ሹፌር ውጭ አጠራጣሪ የሆነ መኪና እንደቆመና ውስጡ የነበሩት ሁለት ግለሰቦች ነብሳት ማጥመጃ መረብ ይዘው ወደ ፓርኩ እንደገቡ ጥቆማ የሰጠው።

ጥበቃዎቹ ባደረጉት ክትትል የተከሳሾቹ ተሽከርካሪዎች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነፍሳትን የያዙ ብለቃጦን አግኝተዋል።

“ስናገኛቸው ሁሉም ነብሳት ሞተው ነበር። ብልቃጥ ውስጥ ኬሚካል ጨምረው ነበር” የሚለው ኒሻታ “በብልቃጦች ውስጥ ከ300 በላይ ነፍሳት ነበሩ” ሲል ጠቁሟል።

ተጠርጣሪዎቹ መጀመሪያ 810 ክሶች ቀርቦባቸው የነበረ ቢሆንም በኋላ ክሳቸው ወደ 304 ዝቅ እንዳለ ተሰምቷል።

አባት እና ልጅ እስከ መጪው መስከረም 14/2017 ዓ.ም የተበየነባቸውን ገንዘብ መክፈል ካልቻሉ 2 ዓመት በእስር ሊያሳልፉ ይችላሉ።

የጣሊያን መገናኛ ብዙኃን አባት እና ልጅ ወደ ስሪላንካ ያመሩት ለሽርሽር መሆኑን ዘግበው በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ እዚያው እንደሚገኙ ፅፈዋል።

ያላ ብሔራዊ ፓርክ በሀገሪቱ ደቡብ ምስራቅ ክፍል የሚገኝ ሲሆን በስሪላንካ ከሚገኙ ፓርኮች እጅግ ታዋቂው ነው። በፓርኩ ሊዮሌዎፓርድ የተሰኘውን የዱር ድመት ጨምሮ፣ ዝሆን እና ጎሾችን እንዲሁም በርካታ እንስሳቶች ይገኛሉ።

ሉዊጂ ፌራሪ የኦርቶፔዲክ ቀዶ ጥገና ባለሙያ ሲሆን የእግር እና ቁርጭምጭሚት ‘ስፔሻሊስት’ እንደሆነ እና ለነብሳት ልዩ ፍቅር እንዳለው ጎደኞቹን ጠቅሰው የጣልያን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በተጨማሪም በጣልያን ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ሞዴና ከተማ ውስጥ የነብሳት አጥኚዎች ማህበር አባል እንደሆነ ተዘግቧል።

ጓደኞቹ እና የሥራ ባልደረባዎቹ የተጣለበት ቅጣት እንዲቀልለት እየተማጸኑ ይገኛሉ።

አንዳንዶች ሰውዬው ይዟቸው የተገኙት ቢራቢሮዎች ለገበያ የማይውሉ እንደሆኑ ይገልጻሉ።

ሌሎች ደግሞ ይህ ቅጣት ሌሎች እንዲማሩበት ማስጠንቂያ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።