ሕጻናት የጸሎት መጻሕፍት በማንበብ ላይ
የምስሉ መግለጫ,ሕጻናት የጸሎት መጻሕፍት በማንበብ ላይ

ከ 5 ሰአት በፊት

አንድ ፍሬ ልጆች ናቸው’ኮ። ግን የማይሠሩት ሥራ የለም።

የተገፈፈ የፍየል ቆዳ ያለፋሉ። ይደጉሳሉ። ይጠርዛሉ። ካራ፣ ጉጠት፣ መጥረቢያ፣ መራመሚያ ተጠቅመው ቆዳ ያለሰልሳሉ። ቀጨም ተጠቅመው ብራና ይወጥራሉ። ተረፈ-ሥጋ ይላጫሉ።

ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ባልጠና ወገባቸው፣ በሚያሳሱ እጆቻቸው ነው።

ደግሞ በብራናው ላይ የቁም ጽሑፍ ይጽፋሉ፣ ሐረግ ይሥላሉ። ይሄ የቀን ሥራቸው ነው።

እኩለ ሌሊት ይነሱና ደግሞ ቅኔ ይሸመድዳሉ። ጸሎት ያደርሳሉ። ጠዋት ዳዊት ይደግማሉ። ሁለት ወራትን እንዲያ እንዲህ ያሳልፋሉ።

ይህን ሁሉ የሚሠሩቱ ርቆ ከሚገኝ መንደር ያሉ ቆሎ ተማሪዎች አይደሉም፤ ዘመናይ ከተሜዎች እንጂ። አንዳንዶቹ የቦሌ እና የካዛንቺስ ልጆች፤ አንዳንዶቹ የሳር ቤት እና የሲኤምሲ ተወላጆች ናቸው።

ወናፍ የሚነፉ የቦሌ ልጆችን ማሰብ ትንሽ ወለፈንዲ ቢመስልም ቅሉ።

ደግሞ ይህ ሁሉ የሚሆነው ሩቅ ተራራ ላይ በተወሸቀች ደብር ውስጥ አይደለም። በመሀል ፒያሳ ነው። በከተመዋ እንብርት ላይ፤ አሮጌው ፖስታ ቤት ግቢ።

በሐመረ ብርሃን የብራና መጻሕፍት ድርጅት ባልደረባ የሆነው አቶ ኪሩቤል ታምራት “ልጆች ይህን ማድረጋቸው ትዕግስትን፣ ሥነ ምግባርን፣ ፍቅርን እንዲያውቁ ያደርጋቸዋል” ይላል።

ልጆች በመንፈሳዊ ትምህርት ወቅት
የምስሉ መግለጫ,ልጆች በመንፈሳዊ ትምህርት ወቅት

በታብሌት ዘመን ብራና ምን ይሠራል?

ቀደምት አባቶቻችን ጽሕፈትን በሳባ ቋንቋ በድንጋይ ሐውልቶች አስቀርተዋል። በዋሻዎች ውስጥ ምሥሎችን ትተዋል።

የአሁን ዘመን ሰው ከሺህ ዓመታት በፊት እንዴት እንደተኖረ ያወቀው አንድም በዚያ ነው። እንጂማ ነገሩ ሁሉ እንደ ድንጋዩ ዝም ይሆን ነበር።

በቀደሙ አባቶቻችን ዘመን ጽሕፈት በሐውልቶች፣ በአጽም ላይ ሳይቀር እየተቀረጸ፣ እያደገ ተስፋፋ። ወደ ብራና ሽግግር የተደረገው በ4ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ከመላምት ያለፈ መረጃ አለ።

የብራና ትልቁ ትሩፋት ዕድሜ ነው። ለሺህ ዘመን ፀንቶ እንኳ ይበላሻል የማይባል ‘ማቱሳላዊ ሚዲያ’ ነው። ቫይረስ ገባበት፣ ፀረ- ቫይረስ ጫንበት፣ ‘ኮራፕት’ አደረገ ብሎ ነገር የለም።

በብራና ታሪክ ትልቁ ዕድሜ የእንዳ አባ ገሪማ የብራና ወንጌል ሳይሆን አይቀርም። ዘመናቸው 6ኛው ክፍለ ዘመን ነው።

ይህ ቅርስ 1600 ዓመት አስቆጠረ ማለት አይደል?

“ብራና ጽሑፍን ዘላለማዊ የማድረጊያ ሁነኛ መንገድ ነው” ይላል አቶ ኪሩቤል።

“አባቶቻችን ብራናን ለማዘጋጀት የለፉት ልፋት የዋዛ አይደለም። የሚወጣው ጉልበት ሁሉ መስዋዕትነት ነው። በየገዳማቱ አባቶች ለዚህ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል” ሲል የተኬደው ርቀት ቀላል እንዳልነበረ ያስገነዝባል።

ኪሩቤል እንደሚለው ብራና ጽሑፎችን፣ ታሪኮችን፣ ቅርሶችን ለረዥም ዓመታት የማስቀመጫ መንገድ ስለሆነ ነው አሁንም እየሠሩበት የሚገኙት። ሊተዉትም ያልፈለጉት።

ከአባ ገሪማ ወንጌል ሌላ ፍትሐ ነገሥትም በዚሁ በብራና ምክንያት ለዚህ ዘመን የቆየን ትልቅ ቅርስ ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወርቃማ ዘመን የሚባለው 13ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ከዚያ ጀምሮ በርካታ ጽሑፎች ተጽፈዋል። የተግባረ ዕድ ሥራዎች በየገዳማቱ ተሠርተዋል። በተለይ በወርቃማው ዘመን ብዙ ተመርቷል።

ዘመን ሲለወጥ- ዘመናዊ መጻፊያዎች መጡ። አሁን ከኮምፒውተርም እየተሻገርን ነው።

ለምን በዚህ ዘመን ብራና ያስፈልጋል ታዲያ?

ኪሩቤል እንደሚለው ፋይዳውን ለመረዳት ከሳይንሳዊ ገጽታውም በላይ መንፈሳዊ መልኩን መረዳት ያሻል።

“ብራና ለመንፈሳዊ አባቶች የሚሰጠው እርካታ ወደር የለውም።”

ከዚያ ባሻገር ደግሞ ሕያው ቅርስ ነው። ቅርስ ዘመናዊ መሣሪያ መጣ ተብሎ አይጣልም።

ሕጻናቱ እንዲማሩት የሚፈለግበት ምክንያት ይኽው ነው። ታሪካዊነቱን በልጆቹም ላይ ለማጋባት ነው። “ሙያውን እንዲያውቁት፣ ትዕግስት፣ ጥሞና እንዲሁም ሥነ ምግባር እንዲሰርጽባቸው…” ሲል በስፋት ያስረዳል።

“ይሄ ሙያ በአባቶች የቆመ ነው። ልጆች ካልተረከቡት ቀጣይነት አይኖረውም” ይላል ኪሩቤል።

ልጆች ምን ይላሉ?

የክረምቱ መርሐ ግብር ተማሪዎች
የምስሉ መግለጫ,የክረምቱ መርሐ ግብር ተማሪዎች

ሐመረ ኖህ በየዓመቱ በአንድ ዙር 80 ሕጻናት ይቀበላል፤ የልጆቹ ዕድሜ ከ7 እስከ 14 ይሆናል።

የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዘመነ ክረምት አዳር የሕጻናት መርሐ ግብር ተብሎ ይጠራል መቆያው ትምህርት ቤት።

ልጆቹ በክረምቱ ወቅት፣ ለሁለት ወራት ነው ሥልጠና የሚገቡት። እንደ ‘ሰመር ካምፕ’ መሆኑ ነው። ዘንድሮ ፍላጎት ስለጨመረ የተማሪዎቹም ቁጥር በእጥፍ አድጓል። ‘መንፈሳዊ ካምፕ’ ልንለው እንችላለን።

በእነዚህ ወራት ልጆቹ ወደ ቤተሰባቸው አይሄዱም። በዚህ የተነሳ ቤተሰብ መናፈቃቸው አይቀርም። ከወላጅ የሚገናኙት በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

ሐሙስ – ሐሙስ እግር ያጥባሉ። እሑድ – እሑድ ጉዞ ይሄዳሉ።

ከኢንተርኔት ጋ ያላቸው ግንኙነት ይቆማል። የስክሪን ሱሳቸው ይፈወሳል።

መጀመርያ አካባቢ ልጆቹ ቤተሰብ ይናፍቃሉ። ለመላመድ ይቸገራሉ። በኋላ ላይ ግን ‘የከተማ ገዳም ኑሯቸውን ይላመዱታል’ ይላል ኪሩቤል።

“ቤተሰቦቻቸው እንደሚደሰቱባቸው ስለሚያስቡ ልጆችም ደስተኞች ናቸው” ሲል ያክላል።

ይህ የብራና የልጆች ‘ገዳም’ ሕጻናቱ ሥነ ምግባርን የሚማሩበት ቤት ነው። መተሳሰብ፣ አብሮ ወንድም እህት ሆኖ መቀጠልን ያውቁበታል።

በተለይ በዚህ አእምሮ በብርቱ የስክሪን ሱሶች በተፈተነበት ዘመን ሁነኛ የስክነት ቦታ ሆኖላቸዋል።

ሥራ የሚውሉ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው መጨነቃቸው አልቀረም። ብራና ገዳም ለአንዳንዶች እፎይታ ሆኗቸዋል።

አዳጊ ተማሪዎች ምን ይላሉ?

ኬብሮን ነጻነት የ14 ዓመት አዳጊ ነው። ከዕድሜው ጋር የማይጣጣም ብስለት ይታይበታል። “ብራና ምን ይሠራልሃል?” ተብሎ ከቢቢሲ ሪፖርተር ሲጠየቅ “እንደሱ ይባላል እንዴ?” ብሎ በትዝብት ይስቃል።

“ግብፃውያን በፓፒረሳቸው ይመካሉ። እኛ ደግሞ ባንመካም በብራናችን ደስ እንሰኛለን፤ ፈጣሪን የምናገለግልበት መሣሪያ እኮ ነው፤ እንዴት ይሄ ደስ ላያሰኝ ይችላል?” ብሎ ይገረማል።

ልጅ ኬብሮን የድሮ ሰዎች ኮምፒውተር፣ ደብተር እና እስክሪብቶ በሌለበት ዘመን ብራናን መፍጠራቸው ይደንቀዋል።

ከኮምፒውተር ፈጣሪም በላይ ያስደንቀዋል። “እኔም በተራዬ ይህን ጥበብ እየተማርኩ በመሆኔ ደስ እሰኛለሁ” ይላል።

ልጆቹ በቆይታቸው ምን ያደርጋሉ?

ልጆች ስልቹ ናቸው። በዚህ ቤት ግን ሥነ ምግባር (ዲሲፕሊን) ልክ ስለሚያስገባቸው፣ ወለም ዘለም አይሉም።

ለምሳሌ ከእንቅልፋቸው ዘወትር የሚነሱት ሌሊት 10፡00 ሰዓት ነው። ይህ ዲሲፕሊን እንኳን ለልጅ ለአዋቂም ፈታኝ ነው።

የ14 ዓመቱ ልጅ ኬብሮን ይህ ሌሊት የመነሳቱ ነገር መጀመሪያ አካባቢ ፈትኖት እንደነበር አይክድም። “ስትለምደው ግን ቀላል ነው፤ ደስ ይላል፤ የቡድን መሪም ስለሆንኩ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ቀደም ብዬ ተነስቼ የምቀሰቅሳቸው እኔ ነኝ” ይላል።

የእሱና የእኩዮቹ ሕይወት በመንፈሳዊ ካምፑ ውስጥ ምን እንደሚመስል እንዲህ ያብራራል።

“ሌሊት 10 ሰዓት እንነሳለን። የአብነት ትምህርት እንማራለን። የዘወትር ጸሎት ውዳሴ ማሪያም፣ አንቀፀ ብርሃን፣ ይዌድስዋ መላዕክት፣ መልክዓ ኢየሱስ፣ መልክዓ ማሪያምን፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ስንክሳርን እናነባለን።”

እነ ኬብሮን ሲነጋ ክፋት በማያውቀው የልጅ ልቦናቸው የግል ጸሎት አድርሰው፣ ነጠላ አጣፍተው ሰግደው ወደ ትምህርት ይገባሉ።

ከቀትር በፊት ግዕዝ፣ ነገረ ሃይማኖት፣ ዝክረ ቅዱሳን፣ ሥነ ምግባር እና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እየተማሩ ያረፍዳሉ።

እስከ ተሲዓት ድረስ የማይጾሙት ምሳ በልተው፤ የሚጾሙት እግር ኳስ፣ ቴኒስ እና ሌሎች ጨዋታዎችን ተጫውተው ይቆዩና ልክ 9፡00 ሰዓት ሲደርስ የተግባረ ዕድ፣ የአንጥረኛ ሞያ እና ቅርጻ ቅርጽ ይማራሉ።

“በተለይ ይህ የአንጥረኛ ሞያ ከልጆቸ ጀምሮ አብሮ ቢያድግ ነገ ሥራው ይከበራል” ይላል አቶ ኪሩቤል፤ ሞያው ቀድሞ የነበረውን መጥፎ ታሪክ እያስታወሰ።

“ሌሊት ጅብ ይሆናል እየተባለ ስንት ዘመን መስቀሉን የሚሠራ፣ ሞፈሩንም፣ ቀንበሩንም የሚሠራ ጥበበኛ ሁሉ ስሙ እየጠለሸ ነው የኖረው። በአዲሱ ትውልድ ይህ ደዌ እንዳይዛመት እንፈልጋለን።”

በከሰዓቱ ክፍለ ጊዜ ሴት አዳጊዎች በገና ይማራሉ።

ከበገና ትምህርት በኋላ ነው የብራና ማልፋት እና ማዘጋጀት ሂደትን የሚማሩት። በዚህ ክፍለ ጊዜ በብራ እና ሥዕል መሣልን፣ ሐረግ መሣልን፣ የቁም ጽሑፍን ጠንቅቀው ይማራሉ።

ልጅ ኬብሮን “አይፓድ፣ ታብሌት ይዘው ክረምቱን በሚያሳልፉ ልጆች አትቀናም?” ሲባል ፈጠን ያለ ምላሽ ይሰጣል።

“መቅናት ያለባቸው እነሱ ናቸው እንጂ እኔ እንዴት በእነሱ እቀናለሁ?” ብሎ ይጠይቃል።

“እነ ላፕቶፕ፣ ታብሌት አላፊ ጠፊ ናቸው። ይሄ ግን ዘመን ይሻገራል። ደግሞ ኮምፒውተር የት ይሄድብኛል?” ካለ በኋላ ብራና መንፈሳዊ እርካታ እንደሚሰጠው በልጅ አንደበቱ ያብራራል።

ሕጻናት በምገባ ላይ
የምስሉ መግለጫ,ሕጻናት በምገባ ላይ

“ብራና ለማልፋት መልፋት አለብህ”

ሐመረ ብርሃን የተጀመረበት አጋጣሚ የአንድ አባትን መጽሐፍ ወደ ብራና ለመገልበጥ በተጀመረ ጥረት ነው።

አባ ፍቅረ ሚካኤል የሚባሉ አባት በንጽሕና የሚያዘጋጇቸውን መጻሕፍት በብራና ቢደረጉ ተብሎ ተጀመረ።

ከዚያ በኋላ እያደገ ሄዶ እዚህ ደረሰ። 2010 ዓ.ም. እንደ ዋዛ የጀመረ አሁን ሰፍቶ 62 ሠራተኛ ይዞ በየቀኑ በርካታ ጎብኚዎች የገኙበት ሥፍራ ሆኗል።

በዋናነት የሚታወቀው በብራና ሥራ ነው። ብራና መሥራት ያለፋል። ሂደቱም ትዕግስትን የሚጠይቅ ነው።

በታሪክ እንደሚነገረው በድኩላ ቆዳ ላይ የሚጻፉት የብራና ጽሑፎች አስማቶች እንደነበሩ ይነገራል። ከፍ ላሉ መጽሐፎች የበግ ይመረጣል።

በጠቅላላው ለትንቢት እና ከሃይማኖት ውጪ ለሆኑ ጽሑፎች ደግሞ የድኩላ ቆዳ አገልግሎት ይውል ነበር።

ግዙፍ መጻሕፍት ደግሞ በፈረስ ቆዳ ይጻፋሉ። የፈረስ ቆዳ ንጣት አለው። ምቾትም አለው። ቀለም ይቀበላል።

በብሔራዊ ሙዝየም እና ቤተ መዛግብት፣ በቅድስ ሥላሴ ሙዝየም ወዘተ በፈረስ ቆዳ ላይ የተጻፉ ግዙፍ የብራና መጻሕፍት ይገኛሉ።

ሐመረ ኖህ ግን በብዛት የፍየል ቆዳን ነው የሚጠቀሙት። በዓመት ሦስት ጊዜ (በዘመን መለወጫ፣ በልደት እና በትንሳኤ በዓላት) ላይ ከሕብረተሰቡ በችሮታ እና አንዳንዴም በግዢ ሰብስበው በጨው ዘፍዝፈው ለሳምንታት ያቆዩታል።

ብራናው ደብተር ሲሆን፣ መጻፊያው ቀለም ደግሞ ከእጽዋት ይቀመማል።

እስክሪብቶ ባልነበረበት ዘመን ረቂቅ በሆነ ኬሚስትሪ አባቶች ከእጽዋት ቀለማት ያዘጋጁ ነበር።

የብራናን ዕድሜ ከሚወስኑት ነገራት ዋናው የቀለማት ዝግጅት ነው።

ምናልባት የእነ አባ ገሪማ ወንጌል ቀለሙ አንዳች ሳይደበዝዝ ይልቁንም በዕድሜው ብዛት እየጎመራ የሄደው ለዚህ ይሆናል።

የብራና መጻፊያ ቀለም ሸጋ ሆኖ እንዲወጣ ለስድስት ወራት ፀሐይ ይፈልጋል። ጥቁር እና ቀይ ቀለም በስፋት አገልግሎት ላይ ይውላል። በቀይ ቀለም የሚጻፉት ግን የቅዱሳን ስሞች ናቸው።

የብራና ላጲሱ ምላጭ ነው። ህጸጽ ሲፈጠር ቀለሙ በምላጭ ይላጫል። በብራና ጽሑፍ ረዥም ጊዜ የሚወስደው ሥራ አርትኦት ነው። በበቁ አባቶች በጥንቃቄ ይኸው ሥራ ይፈጸማል።

አንድ ብራና ማልፋት ብዙ ያለፋል። አንድ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ጽፎ ለመጨረስ ደግሞ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል።

ልጆቹ ይህን ሁሉ ሂደት እንዲያዩ፣ እየሠሩም እንዲማሩ ይደረጋሉ።

እስከአሁን ብዙ ገጽ ያለው መጽሐፍ የቱ ነው ስንል አቶ ኪሩቤልን ጠይቀን ነበር።

“እኛ እስከአሁን ከሠራነው ተአምረ ማሪያም ነው ትልቁ። ገና ተጽፎ አላለቀም፤ 350 የፍየል ቆዳ ይፈጃል። ጽሕፈቱ ብቻ ቢያንስ ሁለት ዓመት ተኩል ይወስዳል። በትዕዛዝ ለአበርክቶ የተሠራ ነው።”

እንዲህ የተለፋበት ሥራ ዋጋው ስንት ይሆን?

“ከ600 ሺህ ብር በላይ ነው።”