የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ከወታደራዊ ኃላፊዎቻቸው ጋር የዩራኒየም ማበልፀጊያውን ሲጎበኙ
የምስሉ መግለጫ,የሰሜን ኮሪያው መሪ ከወታደራዊ ኃላፊዎቻቸው ጋር ማበልፀጊያውን ጎብኝተዋል።

ከ 1 ሰአት በፊት

ሰሜን ኮሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ኒውክሌር ለማብላላት የምትጠቀምበትን የዩራኒየም ማበልፀጊያ ማዕከል ምስል ይፋ አድርጋለች።

የሰሜን ኮሪያን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ “ለማሳደግ” ቃል የገቡት መሪው ኮም ጆንግ ኡን ማበልፀጊያውን ሲጎበኙ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ተለቋል።

የመንግሥት ጣቢያ የሆነው ኮሪያን ሴንትራል ኒውስ ኤጀንሲ አርብ ዕለት ባወጣው ዘገባ ኪም የዩራኒየም ማበልፀጊያው ምርቱን እንዲያሳድግ ጥሪ አቅርበዋል ብሏል።

የበለፀገ ዩራኒየም የኒውክሌር የጦር መሣሪያዎችን ለማምረት እጅግ ጠቃሚ ግብዓት ነው።

ኪም ጆንግ ኡን ማበልፀጊያው መሐል ቆመው ከወታደራዊ ኃላፊዎች ጋር ሲመክሩ በፎቶግራፍ ይታያሉ።

በኮሪያ ሰርጥ ያለው ውጥረት ከምንም ጊዜ በላይ በከረረበት ወቅት ነው ኪም የዩራኒየም ማበልፀጊያ ውስጥ ቆመው የሚያሳይ ፎቶ የተለቀቀው።

“ኪም በዩራኒየም ማበልፀጊያው ቁጥጥር ክፍል ተገኝተው ስለአጠቃላይ ምርት መረጃ ሰብስበው ወጥተዋል።” ይላል ኬሲኤንኤ በዘገባው። አክሎ ማበለፀጊያውን በማየታቸው “እጅግ ደስ ተሰኝተዋል” ሲል ጽፏል።

የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ሰሜን ኮሪያ የዩራኒየም ምርቷን ለማሳደግ ማቀዷን በጠንካራ ቃላት እየተቸ ይገኛል።

ኪም ይህን ጉብኝት ያደረጉት መቼ እንደሆነ አይታወቅም።ማበልፀጊያው ዮንግብዮን የኒውክሌር ማምረቻ ውስጥ ይሁን አይሁንም የሚታወቅ ነገር የለም።

ላይፍ-ኤሪክ ኢዝሊ የተባሉት የደቡብ ኮሪያው ኢውሀ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ሰሙን ኮሪያ ይህን ያደረገችው “የኒውክሌር አቅሟን ለማሳየት እና የጀመረችው የማይቋረጥ መሆኑን ለማመላከት ነው” ይላሉ።

ኪም ጆንግ ኡን ኒውክሌር እያብላሉም ቢሆን ከሩሲያ እና ቻይና ድጋፍ እያገኙ መሆናቸውን ፕሮፌሰር ኢዝሊ ያስረዳሉ።

የኮሪያ ብሔራዊ አንድነት ተቋም ነባር ተንታኝ የሆኑት ሆንግ ሚን ደግሞ ፎቶዎቹ የተለቀቁት ለሚመጣው የአሜሪካ ምርጫ “መልዕክት” ለመላክ እና ማንም ቢመረጥ ሰሜን ኮሪያን “ኒውክሌር አልባ ማድረግ አይቻልም” የሚለውን ለማሳየት ነው ሲሉ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የደቡብ ኮሪያ የአንድነት ሚኒስቴር ሰሜን ኮሪያ ማበልፀጊያውን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ድርጊቱ የተባበሩት መንግሥታት መመሪያዎችን የሚጥስ ነው ብሏል።

ሰሜን ኮሪያ ምን ያክል የኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች እንዳሏት ግልፅ ባይሆን በቅርቡ የወጣ አንድ ግምት 50 ሊኖራት እንደሚችል እና ተጨማሪ 40 የማምረት አቅም እንዳላት ይጠቁማል።