የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር

ከ 3 ሰአት በፊት

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነቱን እንጀመረች ሁሉ አሁኑኑ ማቆም ትችላለች አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያኑ ለዩክሬን የለገሷቸው ሚሳኤሎች ወደ ሩሲያ ግዛት የሚተኮሱ ከሆነ ጦርነቱ ወደ ከፋ ሁኔታ ሊባባስ ይችላል ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ ነው።

የኪዬቭ አጋሮች ሚሳኤሎቹን በሩሲያ ግዛት ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታባቸው ለዩክሬን ፈቃድ ለመስጠት እየተወያዩ ባሉበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር አርብ ዕለት ከአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ጋር ለመወያየት ዋሽንግተን ዲሲ አቅንተዋል።

ፕሬዚደንት ፑቲን “ሚሳኤሎቹ ወደ ሩሲያ ግዛት እንዲተኮሱ መፍቀድ ማለት በዩክሬን ጦርነት የኔቶ አባል አገራት ያላቸውን ቀጥተኛ ተሳትፎ ነው የሚያሳየው” ብለዋል። ይህም የጦርነቱን መልክ እንደሚለውጠው ፑቲን ለአገሪቷ የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

ፑቲን ጨምረውም “ይህ የሚሆን ከሆነ፣ እኛ ላይ በደረሰው ዛቻ መሠረት ተመጣጣኝ ውሳኔ እናሳልፋለን” ብለዋል።

የዋሽንግተን ጉዟቸውን በተመለከተ በጋዜጠኞች የተጠየቁት ስታርመር፣ በተደጋጋሚ ‘ጦርነቱን የጀመረችው ሩሲያ ናት’ ከማለት ውጭ የሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ የለም።

“ይህንን ጦርነት የጀመረችው ሩሲያ ናት። ሩሲያ ዩክሬንን በሕገ ወጥ መንገድ ወርራለች። ሩሲያ ይህንን ጦርነት ወዲያውኑ ማቆም ትችላለች” ያሉ ሲሆን፣ በኋላ ላይም “አፅንኦት ለመስጠት ያህል. . . በመጀመሪያ ደረጃ ይህንን የጀመረችው ሩሲያ ናት። ግጭቱን የፈጠሩት እነርሱ ናቸው። ሕገ ወጥ ድርጊት እየፈፀሙ ያሉት እነርሱ ናቸው” በማለት ተናግረዋል።

የዩክሬን አጋሮች ኢራን ለሩሲያ የጦር መሣሪያ ድጋፍ እያደረገች ነው በሚለው ጉዳይ ላይ እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው እየተነጋገሩ ባሉበት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ላሚ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመፍጠር እየጣሩ ነው።

ቀደም ብሎ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር ኪዬቭን የጎበኙት ላሚ ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ይህ በጉዳዩ ላይ ያለውን ሙግት ይለውጣል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከዋሽንግተን ከተመለሱ በኋላ እሑድ ዕለት የጣልያኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒን ለማግኘት ወደ ሮም ያቀናሉ። ጣልያን አሁን ላይ የቡድን ሰባት የኢንደስትሪ አገራትን የተለዋጭ ፕሬዚደንትነት ቦታን ይዛለች።

ከአንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ ለዓመታዊው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የዓለም መሪዎች በኒው ዮርክ ይሰባሰባሉ።

ዩክሬን ከምዕራባውያኑ የተደረገላትን የሚሳኤሎች ድጋፍ ወደ ሩሲያ ግዛት መተኮሷ ጦርነቱን ያባብሳል እንዲሁም አሜሪካን እና የአውሮፓ አገራን ወደ ጦርነቱ ሊያስገባ ይችላል በሚል ፈቃዱን ለመስጠት ውሳኔ ላይ መድረስ ሳይቻል ቆይቷል።

ሆኖም የክረምት ወቅት በተቃረበበት እና ሩሲያ ከኢራን ሌላ የጦር መሣሪያ እያገኘች ባለችበት ሁኔታ ነገሮች የሚቀየሩ ይመስላል።

ፑቲን ቀደም ብለው ጉዳዩ ምዕራባውያኑ እንደሚሉት የኪዮቭ መንግሥት የሩሲያን ግዛት ዘልቆ ለመምታት ስለማገድ አሊያም ስለመፍቀድ አይደለም። ምክንያቱም በድሮንና በሌሎች መሣሪያዎች ይህንን ሲያደርጉት ቆይተዋል ብለዋል።

“በምዕራባውያኑ ስለተሰሩት ረጅም ርቀት ተወንጫፊ መሣሪያዎች ስናወራ ሁኔታው የተለየ ነው” ያሉት ፑቲን፣ የዩክሬን ሠራዊት እነዚህን ዘመናዊ መሣሪያዎች መጠቀም አይችልም።

ይህን ማድረግ የምትችለው ዩክሬን ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ አሊያም ከኔቶ ሳተላይቶች መረጃ ስታገኝ ነው። የኔቶ አባል አገራት ወታደሮች እነዚህን የሚሳኤል ሥርዓቶች ለመጠቀም የበረራ ተልዕኮዎችን መውሰድ አይችሉም።

በመሆኑም ጉዳዩ ዩክሬን በእነዚህ የጦር መሣሪያዎች ሩሲያን እንድትመታ መፍቀድ አሊያም አለመፍቀድ አይደለም።

ይልቁኑ የኔቶ አገራት በጦርነቱ ውስጥ በቀጥታ መሣተፍን በተመለከተ ውሳኔ ስለማሳለፍ፤ አለማሳለፍ ነው” ብለዋል ፑቲን።

ስታርመር ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ባሉት ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ዋሽንግተን ሲያቀኑ ይህ ሁለተኛ ጊዜያቸው ነው።

ሐምሌ ወር ላይ ለኔቶ አባል አገራት ጉባኤ ወደዚያው አምርተው የነበረ ሲሆን ዋይት ሃውስን ጎብኝተዋል።

ስታርመር በአሁኑ ጉዟቸው ምክትል ፕሬዚደንት እና የዲሞክራቲክ ፕሬዚደንታዊ እጩ ካማላ ሃሪስን እንደማያገኟቸው ተናግረዋል።

ምክንያታቸውን የተጠየቁት ስታርመር “ እንደምትጠብቁት እርሷ ሌላ ግዛት ልትሆን ትችላለች። እንደምታውቁት ከግዛት ግዛት እየዞረች ነው። . . . ጥሩ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።