September 13, 2024 – BBC Amharic 

ኢትዮጵያ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ቀጠናው ላይ ውጥረት ተፈጥሯል።ጂቡቲ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የገባችውን ውጥረት ለማርገብ በሚል የታጁራ ወደብን “በጋራ እናስተዳድር” ስትል የአማራጭ ሀሳብ ማቅረቧን በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ተናግራለች።
በርግጥ ሚኒስትሩ፣ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ ለቢቢሲ የተናገሩት “ሙሉ በሙሉ…

… ሙሉውን ለማየት ወይም ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

በአማራጭነት ከቀረበው የጂቡቲው ታጁራ ወደብ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች

የታጁራ ወደብ

12 መስከረም 2024

ኢትዮጵያ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በፈረመችው የባህር በር መግባቢያ ስምምነት የተነሳ ከሶማሊያ ጋር የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ እንዲሁም የኢትዮጵያን የባህር በር መዳረሻ ችግር ለመቅረፍ በሚል ጂቡቲ አማራጭ ያለችውን ሀሳብ ያቀረበችው ባለፉት ሳምንታት ነበር።

የጂቡቲው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ ቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ላይ በቀረቡበት ወቅት፣ የታጁራ ወደብን ኢትዮጵያ “ሙሉ በሙሉ እንድታስተዳድር” ለማድረግ የሚያስችል አማራጭ አገራቸው ማቅረቧን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ከአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ጂቡቲ ያቀረበችው አማራጭ “ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ለመገንባት ያላትን ፍላጎት እንደማያካትት” አመልክተዋል።

ይህንን ቃለምልልስ ተከትሎ ለሌሎች መገናኛ ብዙኀን፣ ለኢትዮጵያ ያቀረብነው አማራጭ ሃሳብ በሰሜናዊ ጂቡቲ የሚገኘውን ታጁራ ወደብ “በጋራ ማስተዳደርን የሚመለከት ነው” በማለት መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

የጂቡቲ አማራጭ ሃሳብ “ታጁራ ወደብን ለኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ለማስተላለፍ ወይም ለመሸጥ” አለመሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፣ ወደቡን መጠቀም የሚቻለው ለገቢና ወጪ ንግድ ብቻ መሆኑንም አብራርተዋል።

ምንም እንኳ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን “ሙሉ በሙሉ” እንድታስተዳድር ሲሉ ያቀረቡትን አማራጭ ሃሳብ እንዴት “በጋራ ወደ ማስተደዳር” የሚል እንደቀየሩ ባያብራሩም፣ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የቀረበ አማራጭ ሃሰብ መሆኑን ግን ደግመው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ጂቡቲ አቀረብኩት ባለችው አማራጭ ሀሳብ ዙርያ ያለችው ነገር የለም።

ጂቡቲ ይህንን አማራጭ አሁን ለምን አቀረበች?

ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው 95 በመቶ የገቢ ዕቃ የሚያልፈው በጂቡቲ ወደብ ነው።

በአፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ እና ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን ስትፈልግ ቆይታለች።

ጂቡቲ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ለተፈጠረው ውጥረት “አስታራቂ ወደብ” አድርጋ ያቀረበችው ታጁራ ከሁለቱ አገራት ድንበር የሚርቀው 100 ኪሎ ሜትር ነው።

የአፍሪካ ቀንድ ተንታኝ የሆኑት እና በጀርመን ላይፕዚግ ዩኒቨርስቲ የሚገኙት አቶ ነገራ ጉደታ፣ ጂቡቲ ይህንን አማራጭ ያለችውን ሀሳብ በዚህ ጊዜ ያቀረበችው በሁለት ምክንያቶች ነው ይላሉ።

ቀዳሚው ምጣኔ ኃብታዊ ነው የሚሉት አቶ ነገራ፣ ኢትዮጵያ ላለፉት 25 ዓመታት ከ95 በመቶ በላይ ለሚሆነው የወጪና ገቢ ንግዷ የምትጠቀመው የጂቡቲን ወደብ መሆኑን መዘንጋት እንደማይገባ ያስረዳሉ።

ይህ ማለት ደግሞ የወደብ ኪራይ አገልግሎት ለጂቡቲ ኢኮኖሚ “የጀርባ አጥንት” ነው ማለት ነው።

ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊላንድ ፊቷን የምታዞር ከሆነ ይህንን ገቢዋን ስለምታጣ የታጁራን ወደብ እንድታስተዳድር ለመፍቀድ መወሰኗን አቶ ነገራ ይናገራሉ።

ሁለተኛው ፖለቲካዊ መሆኑን የሚጠቅሱት ተንታኙ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ቀጣዩ ሊቀመንበር ምርጫ በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ እንደሚካሄድ አስታውሰው፣ ጂቡቲ እጩዎቻቸውን ካቀረቡ አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ማየት እንደሚገባ ይጠቅሳሉ።

የጂቡቲ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ለኮሚሽኑ ሊቀመንበርነት ዕጩ ሆነው መቅረባቸውን ላስተዋለ፣ ይህንን ውጥረት ለማርገብ በሚል ሰበብ፣ ለቀጠናው ሰላም እየሰሩ መሆኑን ለማሳየት እና የመመረጥ እድላቸውን ለማስፋት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ መገመት እንደሚቻል ይጠቅሳሉ።

የጂቡቲ ወደብ

የጂቡቲ አማራጭ ሀሳብ የተፈጠረውን ውጥረት ማርገብ ይችላል?

በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ የጂቡቲ አማራጭ ሀሳብ መፍትሄ የመሆን እድሉ ግን “ጊዜያዊ መሆኑን” የአፍሪካ ቀንድ ተንታኙ አቶ ነገራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ውል እስካልሰረዘች ድረስ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ይረግባል ብሎ መገመት ከባድ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ ደግሞ ይህንን ታደርጋለች ብዬ አላምንም” የሚሉት አቶ ነገራ፣ ጂቡቲ ለገቢ እና ለወጪ ንግድ ብቻ በሚል ያቀረበችው የአማራጭ ሀሳብ የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል ጦር ሠፈር የመገንባት ፍላጎት እንደማያሳካ በማየት ስኬታማነቱን መተንበይ እንደሚቻል ያብራራሉ።

አክለውም ሶማሊያም ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ካላቸው አገራት ጋር ወታደራዊ ስምምነት ማድረጓ በራሱ ውጥረቱ እንዲባባስ እንዳደረገው ገልጸዋል።

ቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚገኘው የባብል ኤል-ማንደብ ሰርጥ የዓለማችን 15 በመቶ ያህል የንግድ መርከቦችን እንቅስቃሴ የሚያስተናግድ መሆኑን የሚጠቅሱት ባለሙያው ግብጽ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ሌሎች አገራት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በዚህ ወሳኝ የንግድ መስመር ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖረው ላይፈልጉ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያን የሚያካትተው የአፍሪካ ቀንድ የዓለማችችንን ትልቁን የባሕር ላይ የንግድ መስመርን ይዟል።

የአፍሪካ ቀንድን ወሳኝ ስፍራ እንዲሆን ያስቻለው የቀይ ባሕር፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ነዳጅ፤ ከእስያ ደግሞ የኢንዱስትሪ ምርቶች ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ የሚተላለፉበት በመሆኑ ነው።

ይህ ምክንያት ሆኗቸው ከዓመታት በፊት ጀምሮ ኃያላን አገራት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካሉ አገራት ጋር ወዳጅነትን በመመሥረት ተጽዕኗቸውን እና ቁጥጥራቸውን ማጠናከር ይፈልጋሉ።

አንዳንዶችም በቀጠናው የጦር ሠፈሮችን አቋቁመው ወታደሮቻቸውን አስፍረዋል።አሜሪካ፣ፈረንሳይ ሩስያ፣ ቻይና እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በጂቡቲ የጦር ሰፈር ካላቸው ኃያላን ተርታ ናቸው።

እነዚህ ኃያላን አገራት የጦር ሠፈሮች፣ የባሕር ኃይል ወደቦች፣ አየር ኃይል እና ማስልጠኛ ማዕከላትን ጭምር በጂቡቲ ገንብተዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘው እና በሕዝብ ብዛት፣ በታሪክ፣ በኢኮኖሚ ትልቅ አገር የሆነችው ኢትዮጵያ የምትገነባው የባሕር ኃይልም ትልቅ የመሆን እና ተጽዕኖ ማሳረፉ እንደማይቀር አገራቱን ስጋት ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል አቶ ነገራ ይጠቅሳሉ።

ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ጦር ሠፈር በቀላሉ ካገኘች እንደ ማንኛውም ኃያል አገር ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ፣ ተቀባይነቷ እንደሚገዝፍም ይናገራሉ።

በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሠፈራቸውን የገነቡ አገራትን የሚያሳይ ካርታ

የጂቡቲን ጥያቄ ኢትዮጵያ ልትቀበለው ትችላለች?

የባሕር በር አልባዋ ኢትዮጵያ የንግድ መተላለፊያ ወደብ ለማግኘት እና የባሕር ኃይሏን ለማጠናከር ካላት ፍላጎት የተነሳ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት ፈርማለች።

ይህም ሶማሊያን ያስቆጣ ሲሆን በቀጠናውም ውጥረት ፈጥሯል።

የአፍሪካ ቀንድ ተንታኝ የሆኑት አቶ ነገራ ጉደታ ኢትዮጵያ፣ ይህንን የጂቡቲን አማራጭ ሀሳብ ልትቀበል ትችላለች ይላሉ።

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያስቀምጡት፣ ምንም አንኳ የወደብ አስተዳደሩ በጂቡቲ ስር ሆኖ ቢሆንም ባለፉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያ ስትጠቀም የቆየችው የጂቡቲን ወደብ መሆኑን ነው።

ጂቡቲ አስተዳደሩን ለኢትዮጵያ መንግሥት እሰጣለሁ ማለቷ “እንደ በጎ ነገር” እንደሚታይም ጨምረው ገልጸዋል።

“ይህ የኢትዮጵያ ገቢ እና ወጪ ንግድን ሊያሳልጥ ይችላል። ቢሮክራሲ ያስቀራል” ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ጂቡቲ በርካታ ኃያላን አገራት የጦር ካምፖቻቸውን መስርተው የሚገኙባት አገር ናት የሚሉት ባለሙያው፣ አንዳንዶቹ ኃያላን አገራት እርስ በእርስ የጎሪጥ የሚተያዩ መሆናቸውን በመጥቀስ ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ጋርር ወደብን በተመለከተ የምትገባው ማንኛውንም ስምምነት በጥንቃቄ ማየት ይኖርባታል ሲሉ ይመክራሉ።

ከዚህ በፊት ይላሉ አቶ ነገራ፣ “የባህር በር ለሌላት ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ በኩል የገቢ እቃዎች መተላለፊያ ከፍቷል” በሚል ዲፒ ወርልድን አባራ ያስተዳድር የነበረውን ወደብ ተረክባለች።

ኢትዮጵያ መንግሥት ወደፊት እንዲህ ዓይነት ጉዳይ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ይመክራሉ።

አለመግባባት ከተፈጠረም እንዴት ሊፈታ ይችላል? ምን ዓይነት አለመግባባቶችስ ሊገጥሙ ይችላሉ? የሚለው ቅድሚያ በደንብ ቢታይ መልካም መሆኑን ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ ሶማሊላንድን ትታ ታጁራ ላይ ልታተኩር ትችላለች?

እኤአ በ2017 የኢትዮጵያን የገቢ ዕቃዎች ለማስተናገድ ታልሞ ማስፋፍያ የተሰራለት እና 40 ሄክታር የሚሸፍነው የታጁራ ወደብ፣ በይበልጥ የፖታሽ ማዕድንን ለመላክ እንዲያስችል ተደርጎ ነው የተዘጋጀው።

በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል በስፋት የሚገኘውን ፖታሽ ማዕድን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እንዲያስችል ተደርጎ የተሰራው የታጁራ ወደብ በሰዓት 2000 ቶን ፖታሽ ማቀነባበር ያስችላል።

በታጁራ ወደብ ላይ ያሉትን ዘመናዊ ማሽኖች ለመግጠም 60 ሚሊየን ዶላር ያህል አውጥታለች የምትባለው ጂቡቲ፣ አጠቃላይ የኢትዮፕያን የገቢ እና የወጪ እቃዎችን ለማስተናገድ እንዲያስችል አድርጋ ነው ያዘጋጀችው።

አቶ ነገራ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችው ስምምነት በይበልጥ የጦር ሠፈር ለመገንባት የሚያስችላት መሆኑን ጠቅሰው የገቢ እና የወጪ ንግድ የሚስተናገድበት ወደብንም እንደሚያካትት ያስታውሳሉ።

ወደ ኢትዮጵያ ከውጪ የሚገባውን ዕቃ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የምታሸጋግረው ጂቡቲ ደግሞ አሁን ያቀረበችው አማራጭ የገቢ እና የወጪ ንግድን የሚያስተናግድ ወደብ ለመስጠት በመሆኑ፣ “ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት ልትሰርዝ የምትችልበት እድል ጠባብ” መሆኑን ያነሳሉ።

“ለአጭር ጊዜ ማዘግየት ይታሰብ ይሆናል። ለረዥም ጊዜ ግን የባህር ኃይሏን ለማቋቋም ስለምትፈልግ” የመሰረዝ እድል አይኖርም ይላሉ።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነድ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ነው የፈረመችው።

በዚህ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ 20 ኪሎ ሜትር ገደማ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር እና የንግድ ወደብ መገንባትን የሚያስችላት ወደብ ታገኛለች። በምትኩ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ እንደ አገር እውቅና ለማግኘት ትጠብቃለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አሊያም ከኢትዮ ቴሌኮም የተወሰነ ድርሻ እንደምታገኝ ገልጧል።