September 13, 2024 – Konjit Sitotaw 

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ጥቅምት 23 ሁለተኛ ዓመቱን ከመድፈኑ በፊት የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተንና መልሶ የማቋቋም መርሃግብር ማስጀመር እንደሚያስፈልግ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ጋር ትናንት ተወያይተዋል።

ጌታቸውና ሐመር፣ ወደ ጦርነት መመለስ አማራጭ እንዳልኾነና የፖለቲካ ልዩነቶችን በንግግር መፍታት እንደሚያስፈልግም ተስማምተዋል።

ጌታቸው በበኩላቸው፣ የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ካልተተገበረ፣ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ላይ “ከባድ መዘዝ ያስከትላል” በማለት አስጠንቅቀዋል።

“አኹን ያለው ኹኔታ ቀጣይነት የለውም” ያሉት ጌታቸው፣ አሜሪካና ሌሎች አጋሮች ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበርና የትግራይ ተፈናቃዮችና ሱዳን ውስጥ የተጠለሉ ስደተኞች ስቃይ እንዲያበቃ “የተቀናጀ ግፊት” እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተልዕኮውን ባግባቡ እንዲወጣ አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ ሐመር ቃል መግባታቸውንም ጌታቸው ገልጸዋል።