መንገድ ላይ የተቀመጡ ሴት አረጋውያን
የምስሉ መግለጫ,አዲስ በፀደቀው ሕግ መሠረት ከተቀመጠው እድሜ ቀድሞ ጡረታ መውጣት አይፈቀድም።

13 መስከረም 2024, 14:33 EAT

ቻይና ከአውሮፓውያኑ 1950ዎቹ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የጡረታ መውጫ እድሜን ቀስ በቀስ ልትጨምር እንደሆነ ተገለጸ።

አገሪቷ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው በእድሜ የገፉ ሕዝቦቿ ቁጥር በመበራከቱ እና የጡረታ በጀት እየቀነሰ በመምጣቱ ነው።

አርብ ዕለት ከፍተኛው የሕግ አውጭ አካል የጡረታ መውጫ እድሜን ጉልበት በሚጠይቁ የኢንደስትሪ ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ሴቶች ከ50 ወደ 55 ዓመት እንዲሁም በአስተዳደር እና ሙያን በሚጠይቁ ሥራዎች ላይ ለተሰማሩት ከ55 ወደ 58 ዓመት ከፍ እንዲል የቀረበውን ረቂቅ ሕግ አፅድቋል።

በሕጉ መሠረት የወንዶች የጡረታ መውጫ እድሜም ከ60 ወደ 63 ከፍ ይላል።

ቻይና አሁን ላይ እተገበረች ያለችው የጡረታ መውጫ እድሜ በዓለማችን ዝቅተኛ ከሚባሉት መካከል የሚገኝ ነው።

አርብ ዕለት በፀደቀው ሕግ መሠረት የተደረገው ለውጥ ከአውሮፓውያኑ ጥር 1/2025 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንና ለሚቀጥሉት 15 ዓመታትም የጡረታ እድሜ ቀስ በቀስ እንደሚጨመር የቻይና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የአገሪቷ የዜና ወኪል ዢንዋ እንደዘገበው በሕጉ የተቀመጠውን የጡረታ እድሜ ከሦስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ማራዘም የሚቻል ቢሆንም ከተቀመጠው እድሜ በታች ጡረታ መውጣት ግን አይፈቀድም።

ከዚህም በተጨማሪ ከአውሮፓውያኑ 2030 ጀምሮ ተቀጣሪዎች ጡረታ ለመቀበል ለማኅበረሰብ ደኅንነት ዋስትና ተጨማሪ ገንዘብ መክፈል ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

በመንግሥት የሚተዳደረው የቻይና ማኅበራዊ ሳይንስ አካዳሚ ከአምስት ዓመታት በፊት በአገሪቷ በመንግሥት የሚደገፈው የጡረታ ገንዘብ ፈንድ በ2035 በቋቱ ገንዘብ እንደማይኖረው ገልጾ ነበር።

ይህ የተገለጸው ከኮቪድ -19 ወረርሽኝ በፊት ሲሆን ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ የቻይና ምጣኔ ሃብት ክፉኛ ተጎድቷል።

እንደ ዢንዋ ዘገባ ከሆነ በጡረታ የውጫ እድሜ ላይ እና በጡረታ ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ የተደረገው በሕይወት የመቆያ አማካይ የእድሜ ጣሪያ፣ የጤና ሁኔታ ፣ የሕዝብ አወቃቀር፣በትምህርት ደረጃ እና ሰራተኛ ኃይል አቀርቦት ላይ ጥናት ከተደረገ በኋላ ነው።

ሆኖም ዜናው የቻይና የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን በሁለት ጎራ ከፍሎ አሟግቷል።

አንድ የቻይና ማሕበራዊ ሚዲያ – ዌቦ ተጠቃሚ “ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ደግሞ የጡረታ የመውጫ እድሜን እስከ 80 ዓመት የሚያደርስ ሌላ ሕግ ይወጣል” ሲል ጽፏል።

ሌላ ተጠቃሚም በበኩላቸው “ ምን ዓይነት ምስቅልቅል ዓመት ነው።በመካከለኛ እድሜ ላይ የሚገኙ ሰራተኞች ደመወዛቸው የመቆረጥ አደጋ ተጋርጦበታል፤ የጡረታ መውጫ እድሜ ደግሞ ተጨምሯል።ተቀጣሪ ያልሆኑት ደግሞ ሥራ ማግኘት ፈተና ሆኖባቸዋል” ሲል የተሰማውን ገልጿል።

ሌሎች በበኩላቸው ዜናው ሲጠብቁት የነበር እንደሆነ ተናግረዋል። “ ይህ ሲጠበቅ የነበረ ነው።ምንም ውይይት የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም” ብለዋል።

አንድ ሌላ የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚም “በአብዛኛው የአውሮፓ አገራት ወንዶች ጡረታ የሚወጡት 65 እና 67 ዓመት ሲሆናቸው ሲሆን ፣ ሴቶች ደግሞ በ60 ዓመታቸው ነው።ይህ በእኛም አገር ሊለመድ ይገባል” ብለዋል።

የቻይና ግዙፍ ሕዝብ ለሁለት ተከታታይ ዓመት እየቀነሰ ሲሆን የውልደት ምጣኔዋም ቀንሷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሕይወት የመቆያ አማካይ የእድሜ ጣሪያ ደግሞ ወደ 78.2 ከፍ ማለቱን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።