September 13, 2024 – Konjit Sitotaw 
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አራት አርሶ አደሮች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች ለዶቼ ቬለ ገለጹ ፡፡ ታጣቂዎቹ ግድያውን ትናንት ሐሙስ የፈጸሙት አርሶ አደሮቹን ለመልቀቅ በመያዣነት የጠየቁትን አንድ መቶ ሺህ ብር እና አንድ ካርቶን የትምባሆ ሲጋራ ከተቀበሉ በኋላ ነው ተብሏል ፡፡

አርሶ አደሮቹ የታገቱት ትናንት ሐሙስ ማለዳ ከብት እያሠማሩ ባሉበት ወቅት መሆኑን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ሦስት የሟች የቅርብ ዘመዶች «ታጣቂዎቹ ወደ ቀበሌው የገቡት ከአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በመነሳት ነው ፡፡ ታጋቾቹን ከያዙ በኋላ ካሊያ ተብሎ ወደ ሚጠራው ጫካ ውስጥ ነው ይዘው የሄዱት ፡፡ አንድ መቶ ሺህ ብር እና አንድ ካርቶን የትምባሆ ሲጋራ ከተሰጣቸው እንደሚለቋቸው መልዕክት ልከውብን ነበር ፡፡ በተጠየቅነው መሠረት የተባልነውን ብንልክም ገንዘቡን እና ትምባሆውን ከተቀበሉ በኋላ ገድለዋቸው ሄደዋል ፡፡ ቀብራቸውም ዛሬ ዓርብ እየተፈፀመ ይገኛል» ብለዋል ፡፡

ዶቼ ቬለ በአርሶ አደሮቹ ግድያ ላይ የኮሬ ዞን አስተዳዳሪንም ሆነ የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ የሥራ ኃላፊዎችን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አመራሮቹ ስብሰባ ላይ ናቸው በመባሉ ሊሳካ አልቻለም ፡፡ ያም ሆኖ የአርሶ አደሮቹን መገደል በተረጋገጠ የፌስ ቡክ ገጹ የገለጸው የዞኑ መስተዳድር የድርጊቱ ፈጻሚዎች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ቡድኖች ናቸው ሲል ዐሳውቋል ፡፡

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በኮሬ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴ ዶክተር ዐወቀ ሀምዛዬ እገታና ግድያውን የፈፀሙት አካላት በቁጥር 16 አካባቢ የሚሆኑ ታጣቂዎች መሆናቸውን ከነዋሪዎች ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል ፡፡ በአካባቢው ግድያና ጥቃት በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም የጠቀሱት ዶክተር ዐወቀ «መፍትኄው ሁለት ነው ፡፡ እሱም የፀጥታ ኃይሉ ጠንካራ ዘመቻ በማድረግ ታጣቂዎችን ማጽዳት ወይም ሕዝብ ራሱን እንዲከላከል በሕጋዊ መንገድ ማስታጠቅ ያስፈልጋል» ብለዋል ፡፡