September 13, 2024 

በአሰላ ከተማ እና በሲርካ ወረዳ 44 ሰዎች በሸኔ ታጣቂዎች መታገታቸው ተገለጸ

በአርሲ ዞን አሰላ ከተማ እና በሲርካ ወረዳ ትናንት ሐሙስ መስከረም 02 ቀን 44 ሰዎች በሸኔ ታጣቂዎች መታገታቸውን አዲስ ማለዳ ከአይን እማኞች ሰምታለች።

የሸኔ ታጣቂ ቡድኖቹ በአርሲ ዞን ሲርካ ወረዳ ከጎቤሳ ከተማ ወደ ተለያዩ ከተሞች በመጓዝ ላይ የነበሩ አጠቃላይ 8 የህዝብ ማመላለሻዎችን ጋለማ በሚባል ጫካ ውስጥ በማስቆም 38 ሰዎችን በመምረጥ ማገታቸውን ሰምተናል።

በሲርካ ወረዳና አጎራባች ቀበሌዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች የሸኔ ታጣቂ ቡድኖቹ በአካባቢው በስፋት የሚንቀሳቀሱና ቀን በቀን እገታ የሚፈጽሙ በመሆኑ ከእገታ ለማስለቀቅም በርካታ ገንዘብ ለመክፈል እንገደዳለን ይላሉ።

በተለይም ጋለማ የሚባለውን ጫካ አቋርጠው የሚጓዙ መንገደኞች በስፍራው የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ባለመኖራቸው ምክኒያት በታጣቂ ቡድኖቹ ለግድያ እና ለእገታ መዳረጋቸውን ነዋሪዎቹ በምሬት ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ታጣቂ ቡድኖቹ ሐሙስ ሌሊት በአሰላ ከተማ ቀበሌ 10 አካባቢ ተኩስ በመክፈት አባትና ልጅን ጨምሮ 6 ነዋሪዎችን አግተው መውሰዳቸውን አዲስ ማለዳ ከስፍራው ከሚገኙ ምንጮቿ አረጋግጣለች።

ታጣቂዎቹ ማን ከየት ነው? እና ምን አለው? የሚለውን መረጃ በማጣራት ስልክ በመደወል ከ5 መቶ ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ድረስ እንዲላክላቸው ይጠይቃሉ፤ ላኩ ያሉትን ብር መላክ ካልቻሉ በፈለጉት ሰአት በመምጣት አግተው እስከ መግደል ይደርሳሉ ሲሉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች የሁኔታውን አስከፊነት ያስረዳሉ።

አዲስ ማለዳ በዚህ ጉዳይ ላይ የአካባቢውን የስራ ሀላፊዎችንም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን ሀሳብ ለማካተት ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ያደረገች ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል።  (አዲስ ማለዳ)