አንቶኒ ብሊንከን

ከ 6 ሰአት በፊት

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን “የሩሲያ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ቀኝ እጅ” ሆኗል ብለው የወነጀሉት መገናኛ ብዙኃን፣ ቻናል አርቲ ላይ አዲስ ማዕቀብ ጣሉ።

አርብ እለት የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ወቅት አርቲ በሩስያ ከሚደገፉ የሚድያ ተቋማት መካከል አንዱ እንደሆነ እና በድብቅ “በአሜሪካ ያለውን ዲሞክራሲ የሚያጣጥል” መሆኑን ገልጸው ነበር።

አክለውም የሩስያ መንግሥት “በአርቲ ውስጥ በሳይበር አቅም እና ከሩስያ ደኅንነት ተቋም ጋር ተቀናጅቷል።” ብለዋል።

አርቲ የፕሬዝዳንት ባይደንን ንግግር በኤክስ ገጹ ላይ አስተላልፎ “አዲሱ የአሜሪካ የሴራ ትንተና ‘ኮንስፓይረሲ ቲየሪ’” ሲል ዘግቦ ነበር።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆነችው ማሪያ ዛካሮቫ አሜሪካ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ በመጣል “አዲስ ሙያ መኖር አለበት” ስትል ተሳልቃለች።

አርቲ የአሜሪካ ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ይጥራል በሚል የተጣለውን ማዕቀብ አስመልክቶ የመገናኛ ብዙኃኑ ዋና አዘጋጅ ማርጋሪታ ሲሞንያን፣ በርካታ ሠራተኞቻቸው በአሜሪካ ወጪ እዚያው አገር ውስጥ የተማሩ መሆናቸውን እና ለሌሎች ጥሩ መምህራኖች ሊባሉ እንደሚችሉ ተናግራለች።

ማርጋሪታ ባለፈው ሳማንት እንዲሁ ምርጫ ላይ ያለ አግባብ ተጽዕኖ ለመፍጠር በመስራት በሚል በአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ ከተጣለባቸው የድርጅቱ ሠራተኞች መካከል አንዷ ናት።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር መሥርያ ቤቱ ከዚህ በፊት የዛሬይቱ ሩሲያ (ራሺያ ቱደይ) የተሰኘውን የመገናኛ ብዙኃን “በምስጢር ጫና ለመፍጠር፣ የመረጃ ፍሰት እንዲሁም ወታደራዊ ምልመላ ላይ” በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ እንዲሁም በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ ተንቀሳቅሷል ሲል ወንጅሎታል።

ብሊንከን በበኩላቸው አርቲን በኦንላይን የጥይት መከላከያ፣ ስናይበር፣ ድሮን እንዲሁም ሌሎች የጦር መሳርያዎችን በዩክሬን ለሚዋጉ የሩሲያ ወታደሮች ለመግዛት ገንዘብ ያሰባስብ ነበር ሲሉ ይከሱታል።

ይኸው የመገናኛ ብዙኃን ሞልዶቫ ጥቅምት 2024 ከምታካሄደው ምርጫ በፊት በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ከሩሲያ የደኅንነት ተቋም ጋር በመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።

አሜሪካ ከዚህ ቀደም ሁለት የአርቲ ተቀጣሪዎች የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ጣልቃ ለመግባት ሞክረዋል ስትል መክሰሷ እና ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።

ነገር ግን የአሜሪካ ባለሥልጣናት አርብ ዕለት መገናኛ ብዙኃኑ ሩሲያ ዲሞክራሲን ለማጣጣል በምታደርገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ሚና አለው ሲሉ ሌላ ውንጀላ አቅርበዋል።

ድርጅቱ በወቅቱ የአሜሪካ መንግሥትን ውንጀላ “2016ን እስከ የቸከ አስተያየቱ መጥራት ነው” ሲል ነበር የተሳለቀው።

“በሕይወት ሦስት ነገሮች አይቀሬ ናቸው፤ ሞት፣ ታክስ እና በአሜሪካ ምርጫ የአርቲ ጣልቃ ገብነት” ሲልም ነበር ጉዳዩን እንዴት እንደሚመለከቱት ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ ላይ የተናሩት።

ብሊንከን በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት “ለሩሲያ ውሸት መድሃኒቱ ያለን እውነት ነው።የክሬምሊን መንግሥት ጨለማን ተገን አድርጎ የሚሰራው ላይ ሁሉ ብርሃኑን ያበራበታል።”ብለዋል።

ብሊንከን አክለውም የተጣለው ማዕቀብ መገናኛ ብዙኃኑ ከሚሰሯቸው ዘገባዎች ጋር የተገናኙ አለመሆናቸውን ገልፀው፣ አሜሪካ ነጻ ጋዜጠኝነትን ትደግፋለች ሲሉ ተናግረዋል።

“በምስጢር ተጽዕኖ ለማድረግ መንቀሳቀስ ግን ጋዜጠኝነት አይደለም” ሲሉ አክለዋል።