ጡት የምታጠባ እናት

ከ 7 ሰአት በፊት

ለዓመታት እናቶች ‘የእናት ጡት ወተትን የሚተካ የለም’ ሲባል ይሰማሉ።

ይህ የሚባለው ጡት ማጥባትን ለማበረታታት ነው። ሆኖም ግን ይህንን ለማድረግ የሚቸገሩ እናቶች ላይ ጫናም ያሳድራል።

አንዳንድ እናቶች ጡት ማጥባት ቢፈልጉም በተለያየ ምክንያት ካሰቡት ጊዜ ቀድመው ለማቋረጥ ይገደዳሉ።

ይህም ሐዘን ውስጥ ይከታቸዋል። ስሜቱ ጡት ማጥባት ያለመቻል ሐዘን ወይም በእንግሊዘኛው ብረስትፊዲንግ ግሪፍ (breastfeeding grief) ይባላል።

ጡት ማጥባት ለማቆም ከወሰኑ በኋላ እናቶች ሐዘን ውስጥ የሚገቡበትን እና ሃፍረት የሚሰማቸውን ወቅት ይገልጻል።

ጀማ ሙንፎርድ ልጇ ማክስን የወለደችው በአውሮፓውያኑ 2017 ነው። ልጇን የጡት ወተት ብቻ ለመመገብ ወስና ነበር።

ሦስተኛው ቀን ላይ ግን ይከብዳት ጀመር።

“ልጄን አቅፌ ተቀምጬ ነበር። ማልቀስ ማቆም አቃተኝ” ስትል ታስታውሳለች።

በቀጣይ የመጡት ሁለት ሳምንታት “ገሀነም ነበሩ” ትላለች። እያንዳንዱን ምግብ ልጇ ሲወስድ ታዝን ነበር።

ጀማ ሙንፎርድ
የምስሉ መግለጫ,ጀማ ሙንፎርድ

አንድ ቀን ጀማ ሊጠይቋት የሄዱ ሰዎችን ከቤቷ አስወጥታ መኝታ ቤት ተደበቀች። መጋረጃዋን ዘጋች።

ልጇ ከጡቷ እንዲጠባ ለማድረግ ሞከረች።

“ጡት የማጥባት ሂደት አድካሚ እና አሳፋሪ ሆኖብኝ ነበር” ትላለች።

ልጇ ምላሱ ከአፉ ጋር የሚገናኝበት ቆዳ ከተለመደው የወፈረ ነበር። ይህ ታንግ ታይ (tongue-tie) የሚባለው እክል ስላለበት ጡት ለመጥባት ይቸገር ነበር።

ከሁለት ሳምንት በኋላ ልጇ ክብደት መቀነስ ጀመረ። ወደ ሆስፒታል እንዳይገባ ስትል ፎርሙላ ወተት ለመመገብ ወሰነች።

ከሁለት ዓመት በኋላ ሁለተኛ ልጇን ወለደች።

እንደ መጀመሪያ ልጇ የምላስ ቆዳ መወፈር ችግር ባይኖርባትም ለማጥባት መሞከር እንደማትችል አወቀች።

ከሁለት ቀናት በላይ ልጇን ማጥባት አልቻለችም። ሆኖም ግን ዛሬም ድረስ ውሳኔዋ ያሳዝናታል።

“እንደ እናት በጣም ተፈጥሯዊ የሆነውን ነገር ማድረግ ተሳነኝ። በጣም ያሳዝነኛል። እስከ ዛሬም ያሳፍረኛል” ትላለች።

አሁን ላይ ስታስበው በወቅቱ ከወሊድ በኋላ ለሚመጣ ድባቴ (postnatal depression) ተጋልጣ እንደነበር ተገንዝባለች።

ጡት ማጥባት ያለመቻል ሐዘን ምንድን ነው?

የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያ ፕሮፌሰር ኤሚ ብራውን በጉዳዩ ላይ መጽሐፍ አሳትማለች።

ጡት ማጥባት ባለመቻል የሚፈጠር ሐዘን እናቶችን እንደሚገጥማቸው ትናገራለች።

“ብዙ እናቶች ማጥባት ከሚፈልጉበት ጊዜ ቀድመው ያቆማሉ። የቀረባቸው ነገር እንዳለ ስለሚሰማቸው ያዝናሉ” ትላለች።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በርካታ እናቶች ጡት ማጥባት ይፈልጋሉ።

ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም 81 በመቶ እናቶች ጡት ብቻ ማጥባትን ይመርጣሉ። ከስድስት ወራት በኋላ ግን ቁጥሩ ወደ 26 በመቶ ይቀንሳል።

የዓለም ጤና ድርጅት ለመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ጡት ማጥባትን ይመክራል። ዩኒሴፍ ጡት ማጥባት ድንገተኛ የጨቅላ ሞትን፣ የስኳር ህመምን፣ የልብ ህመምን እና ከመጠን ያለፈ ውፍረትን እንደሚቀንስ ይገልጻል።

ዩኒሴፍ እንደሚለው ደቡብ እስያ እስከ ስድስት ወር ጡት ማጥባት ላይ ብቻ በማተኮር ቀዳሚ ቦታ አላት። ቁጥሩ 60 በመቶ ይደርሳል። ምሥራቃዊ እና ደቡባዊ አፍሪካ 58 በመቶ ሲሆን፣ ላቲን አሜሪካ እና ካረቢያን 43 በመቶ ነው።

ምዕራብ እና ማዕከላዊ አፍሪካ 40 በመቶ፣ ምሥራቅ አውሮፓ እና ማዕከላዊ እስያ 36 በመቶ ሲሆን፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ 35 በመቶ ተመዝግቧል።

እናትና ልጅ

በመላው ዓለም ከስድስት ወር በታች ያሉ ሕጻናት ጡት የማጥባት መጠን ካለፈው አሥር ዓመት የ10 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ አሁን 48 በመቶ ደርሷል።

ዲፓቲ የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ናት። ከመጀመሪያ ልጇ በተሻለ ሁኔታ ሁለተኛ ልጇን ለማጥባት አቅዳለች።

የመጀመሪያ ልጇን እአአ በ2021 ነው የወለደችው። ልጇ ምላሱ ከአፉ ጋር የሚገናኝበት ቆዳ ከተመደው የወፈረ መሆኑ ጡት ማጥባትን ፈታኝ አድርጎባት ነበር።

እክሉ ቢስተካከልም ጡት ለማጥባት ተቸግራለች። የጡት ወተቷን በጡጦ አድርጋ ለመመገብ ብትሞክርም አድካሚ ሆኖባት ነበር።

“ሂደቱ አድካሚ ነበር። ምሽትን ጨምሮ በየሁለት ሰዓቱ ወተት በጡጦ ማድረግ ነበረብኝ። መጥፎ እናት እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር” ትላለች።

በዚህ ሂደት ምክንያት ከቤት መውጣት አቆመች። ልጇ 12 ሳምንት ሲሞላው ሙሉ በሙሉ ልጇ የዱቄት ወተት (ፎርሙላ) እንዲወስድ አደረገች።

ልጇን ይዛ ወደ ሕጻናት ዕድገት ትምህርት መሄድም ጀመረች። ይህም ለልጇ ጠቅሞታል።

ከወር በኋላ የልጇ ምላስ መታከም እንዳለበት አወቀች። ሆኖም ግን በዚያ ወቅት ወደ ጡት ማጥባት ለመመለስ ዘግይታ ነበር።

ሌሎች ጓደኞቿ ጡት ሲያጠቡ እና እሷ ልጇን በጡጦ ስትመግብ ሃፍረት እና ጥፋተኝነት ይሰማት እንደነበር ትናገራለች።

“ማንም ምንም ባይለኝም ለምን እኔም ልጄን እንደሌላው እናት ጡት ማጥባት አልቻልኩም ብዬ አዝን ነበር” ትላለች።

ዲፓቲ  እና ልጇ
የምስሉ መግለጫ,ዲፓቲ እና ልጇ

እናቶች ለምን ጡት ማጥባት ያቆማሉ?

ጀማ እና ዲፓቲ ልጆቻቸው ባለባቸው ተፈጥሯዊ የምላስ እክል ምክንያት ነው ለማጥባት የተቸገሩት።

ሆኖም እናቶች ጡት ማጥባት የሚያቆሙባቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው። የጡት ማበጥ፣ መሰንጠቅ ወይም መድማት ይጠቀሳል። ልጆችን ጡት በአፋቸው በአግባቡ ይዘው ለማጥባት አለመቻል እና የወተት መጠን ማነስም የሚጠቀስ ነው።

ጡት ከመጠን በላይ በወተት ሲሞላ (Engorgement) ኢንፌክሽ ይፈጥራል።

ይህ ኢንፌክሽን (mastitis) የጡት ማበጥና ጡት በማጥባት ወቅት ህመም ይፈጥራል።

ጡት ከማጥባት ጋር በተያያዘ ችግር የሚገጥማቸው እናቶችን የምታማክረው ሊሳ ማንዴል እንደምትለው፣ እናቶች ሙያዊ የጡት ማጥባት ምክር እና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።

“ዘርፈ ብዙ ችግር ነው። አነስተኛ ወተት ያላት እናት የታይሮይድ ችግር ስላለባት ልትታከም ትችላለች። የወተት መጠንን ያስተካክላል” ትላለች።

ጨቅላ ሕጻናት በአግባቡ ከተቀመጡ እና የእናት ጡት ከያዙ ጡት ማጥባት “የሚያሳምም ሂደት” መሆን የለበትም ትላለች።

“ሂደቱ እናትየዋ የሆነ ድክመት እንዳለባት እንዲሰማት የሚያደርግ መሆን የለበትም” ስትልም ትመክራለች።

ፊድ ዩኬ የተባለው ተቋም ኃላፊ ክሌር መርፊ እንደምትለው፣ ልጆችን ጡት ማጥባት ሁሌም ቀላል አይደለም።

እናቶች ልጆቻቸውን በየትኛውም መንገድ ለመመገብ ቢወስኑ መደገፍ እንደሚያሻ ትናገራለች።

“ፎርሙላ መጠቀም ባይፈልጉም ግዴታቸው ሲሆን፣ እናቶች የጥፋተኛነት ስሜት ስለተሰማቸው እና የአእምሮ ጤናቸው ስለተጎዳ የሚጠቀም ማንም የለም። ልጆችም አይጠቀሙም” ትላለች።

ዲፓቲ ሁለተኛ ልጇን ጡት ለማጥባት ብትወስንም በመጀመሪያ ልጇ የተሰማት ዓይነት ጫና ውስጥ ራሷን እንደማትከት ትናገራለች።

“መቶ በመቶ በድጋሚ እሞክራለሁ። አሁን የተሻልኩ ነኝ” ትላለች።