ስልኮች ንዝረትን መለየት የሚችሉ ሆነው ተፈብርከወዋል

ከ 7 ሰአት በፊት

የሰው ልጅ የመጀመሪያውን የሞባይል ስልክ ጥሪ ካደረገ 50 ዓመታት በኋላ በኪሳችን የምንይዘው ቴክኖሎጂ የመሬት መንቀጥቀጥን ለመለየት እየረዳ ይገኛል።

እአአ በ2022 በካሊፎርኒያ ቤይ ኤሪያ በርዕደ መሬት መለኪያ (ሬክተር እስኬል) 5.1 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ ነበር። እንደ ዕድል ሆኖ ኃይለኛ ንዝረት እንጂ ከባድ መንቀጥቀጥ አልነበረም።

ንዝረቱ የተሰማቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ (ዩኤስጂኤስ) ጎርፈዋል። ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም። ነገር ግን የመሬት መንቀጥቀጡ በሌላ መልኩ ጉልህ ነበር። ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች መንቀጥቀጡ ከመጀመሩ በፊት በስልካቸው ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል።

ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያዎች እአአ ሐምሌ 6/2024 ምሽት ላይ ከቤከርፊልድ ከተማ በስተደቡብ ርቀት ላይ በሚገኘው እና 5.2 የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ በደረሰበት በደቡባዊ ካሊፎርኒያ የሚኖሩ ነዋሪዎች እስከ 30 ሰከንድ የቆየ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል።

አብዛኞቹ ስልኮች የመሬት መንቀጥቀጡ መኖሩን ቀድመውም ለማወቅ ችለዋል።

ጎግል ከዩኤስጂኤስ እና ካሊፎርኒያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ካሉ ምሁራን ጋር በመቀናጀት የቅድመ ማስጠንቀቂያ አሠራርን ዘርግቷል። ይህም ተጠቃሚዎች መንቀጥቀጡ ከመድረሱ ከጥቂት ሰከንዶች በፊት ማስጠንቀቂያ በመላክ ሲሠራ ቆይቷል።

የአጭር ጊዜ ማስጠንቀቂያ ቢሆንም ግን ጥቂት ሰከንዶችን ማግኘት በጠረጴዛ ስር ለመሸሸግ እንኳን በቂ ጊዜ ሊሰጥ ይችላል። ባቡሮችን ለማዘግየት፣ አውሮፕላኖች እንዳይነሱ ወይም እንዳያርፉ እና መኪኖች ወደ ድልድይ ወይም ዋሻዎች እንዳይገቡ ለማድረግ በቂ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ይህ ሥርዓት ጠንከር ያለ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰት ሕይወትን ለማዳን ያስችላል።

ለዚህም መረጃ ከሁለት ምንጮች ይገኛል። የመጀመሪያው ሥርዓቱ በ700 የርዕደ መሬት መመዝገቢያ አውታረ መረቦች ላይ የተመሠረተ ነው። እነዚህም የመሬት መንቀጥቀጥን የሚለዩ መሳሪያዎች ሲሆኑ በካሊፎርኒያ የቴክኖሎጂ ተቋም፣ በካሊፎርኒያ በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ እና በግዛቲቱ መንግሥት የተተከሉ ናቸው።

ጉግል በበኩሉ በሰዎች እጅ ላይ ባሉ ስልኮች የሚለይ እና በዓለም ትልቁን የመሬት መንቀጥቀጥ ማሳወቂያ መረብ ሲያሰናዳ ቆይቷል።

የጉግል አንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተምን የሚጠቀሙ አብዛኞቹ ስማርት ስልኮች አክሰለሮሜትርስ አላቸው። ይህም ስልኩ ሲንቀሳቀስ የሚለይ መሣሪያ ተገጥሞለታል። ይህ ዘዴ የአካል ብቃት መከታተያ በመሆንም የእርምጃ ቆጠራ መረጃን ለማቅረብ ይረዳል።

በመሬት መንቀጥቀጥ የፈራረሱ ሕንጻዎች
የምስሉ መግለጫ,የመሬት መንቀጥቀጥ ማስጠንቀቂያዎች ሰዎች በሰከንዶች ውስጥ ነፍሳቸውን ለማዳን እርምጃ እንዲወስዱ ያስችላል

የስልክ የመሬት መንቀጥቀጥ ማስጠንቀቂያዎችን እንዴት መጠቀም ይቻላል?

የአንድሮይድ ስልኮች ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ለማግኘት በስልክዎ ሴቲንግ ውስጥ ባለው የሴፍቲ ኤንድ ኢመርጀንሲ ክፍል ውስጥ ያገኛሉ። ሥርዓቱ እንዲሠራ በዋይ-ፋይ ወይም በሞባይል ዳታ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲኖረው ያስፈልጋል። በጃፓን የሚኖሩ የአይፎን ተጠቃሚዎች ኢመርጀንሲ አለርትስን በመጠቀም መረጃውን ማግኘት ይችላሉ።

መሣሪያዎቹ አነስተኛ እንቅስቃሴን ጭምር ስለሚለዩ እንደ አነስተኛ የመሬት ንዝረት መለኪያ (ሴሲሞሜትር) ሆነው ሊሠሩ ይችላሉ።

ጉግል ስልኮቹ የመሬት መንቀጥቀጡ ዋና ባህሪይ የሆኑ ንዝረቶችን ከለየ ተጠቃሚዎችን በስልካቸው በኩል የማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን እንዲልክ የሚያስችል አሠራር አስተዋውቋል።

በሺህዎች ወይም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሌሎች ስልኮች መረጃን በማጣመር የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን እና የት እንደሆነ ማወቅ ይችላል። ከዚያም ተከታታይ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊኖር በሚችልበት አካባቢ ላሉ ስልኮች ቅድመ ማስጠንቀቂያዎችን መላክ ይችላል።

የሬድዮ መልዕክቶች ከሴሲሚክ (የንዝረት) ሞገዶች በበለጠ ፍጥነት ስለሚጓዙ መንቀጥቀጡ ከመጀመሩ በፊት ማስጠንቀቂያዎቹ ሊደርሱ ይችላሉ።

በአንድሮይድ የሶፍትዌር መሐንዲስ የሆነው ማርክ ስቶጋይትስ “የብርሃን ፍጥነትን (የስልክ መረጃ የሚጓዝበት ፍጥነት) ከምድር መንቀጥቀጥ ፍጥነት ጋር እናወዳድራለን። የብርሃን ፍጥነት በጣም ፈጣን ነው” ሲል አስረድቷል።

አብዛኛው መረጃ ከሌሎች ምንጮች የተገኘ በመሆኑ ቴክኖሎጂው ውድ የሆነ የሴስሞሜትሮች በሌሉባቸው አካባቢዎች የመሬት መንቀጥቀጦች ስለመኖቸው የመከታተል ዕድልን ይከፍታል። ይህ ደግሞ የመሬት መንቀጥቀጥ ማስጠንቀቂያዎችን በሩቅ እና ድሃ በሚባሉት የዓለም ክፍሎች ጭምር ለመስጠት ዕድል ይሰጣል።

“በካሊፎርኒያ የመሬት መንቀጥቀጥ የተለመደ ክስተት ሲሆን በቀን እስከ 100 የሚደርሱ ትናንሽ ንዝረቶች ያጋጥማሉ።”

እአአ በጥቅምት 2022 የጎግል መሐንዲሶች ሳን ፍራንሲስኮ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ማዕከል ከሆነው አካባቢ መረጃው ሲሠራጭ ተመለከቱ።

ሥርዓቱ አሁን እነዚህን መንቀጥቀጦች በመደበኛነት በመከታተል መረጃዎችን ይሰበስባል። ወዲያውም መረጃው የመሬት መንቀጥቀጡ ሊያጋጥም በሚችልባቸው አካባቢዎች ላሉ ተጠቃሚዎች የሞባይል ስልኮች ላይ መልዕክት ያስተላልፋል።

መልዕክቶቹን በአንድሮይድ ስልኮች መቀበል ቢቻልም በካሊፎርኒያ፣ በኦሪገን እና በዋሽንግተን ያሉ ሰዎች በበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተሠራውን ማይሼክ መተግበሪያን በመጠቀም ማግኘት ይችላሉ። መተግበሪያው ተጠቃሚዎች ተንቀሳቃሽ ስልኮች በማይጠቀሙበት ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ጠቋሚ ይሆናል። በዚህም ስልኩ ያለበትን አካባቢ መሠረት በማድረግ መልዕክቶችን ይልካል።

በካሊፎርኒያ የመሬት መንቀጥቀጥ የተለመደ ክስተት ሲሆን፣ በቀን እስከ 100 ትናንሽ ንዝረቶች ያጋጥማሉ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ማጋጠማቸውን እንኳን ለማወቅ የማይቻሉ በጣም አነስተኛ የሚባሉ ናቸው። በካሊፎርኒያ በዓመት ከ15 እስከ 20 የሚደርሱ እና በሬክተር ስኬል ከአራት በላይ የሚመዘገቡ ብዙ ትላልቅ የመሬት መንቀጥቀጦች ይከሰታሉ።

በዓለም ላይ ጥቅም ላይ ከዋሉት 16 ቢሊዮን ሞባይል ስልኮች ውስጥ ከሦስት ቢሊዮን በላይ የሚሆኑት የአንድሮይድ ስልኮች ሲሆኑ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱ በተለይም ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ በሆኑ ከ90 በላይ አገራት እየሠራ ይገኛል።

ሥርዓቱ ውሱንነቶችም አሉት። በተለይም ጥቂት የስልክ ተጠቃሚዎች ባሉባቸው ራቅ ባሉ አካባቢዎች እና በባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች ምክንያት ሱናሚም ሊፈጠር የሚችልባቸውን ሁኔታዎችን ለመለየት አስቸጋሪ ነው።

ይህ ሥርዓት የመሬት መንቀጥቀጡ ከመከሰቱ ከጥቂት ሰከንዶች በፊት ማንቂያዎችን ለማስተላለፍ ሊረዳ ቢችልም፤ የመሬት መንቀጥቀጦች ከመከሰታቸው በፊት የመተንበይ ሳይንስ አሁንም እንደበፊቱ ቀላል ሳይሆን ይቆያል።