ቤንጃሚን ዛልማን ፖሉን፣ ማርሴል ማላንጋ እና ታይለር ቶምፕሰን
የምስሉ መግለጫ,ቤንጃሚን ዛልማን ፖሉን፣ ማርሴል ማላንጋ እና ታይለር ቶምፕሰን በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሞት የተፈረደባቸው የአሜሪካ ዜጎች ናቸው።

ከ 4 ሰአት በፊት

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ፕሬዚደንት ከሥልጣን ለማስወገድ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በመፈፀም ሦስት አሜሪካውያን፣ እንግሊዛዊ፣ ቤልጂየማዊ እና ካናዳዊን ጨምሮ 37 ግለሰቦች የሞት ፍርድ ተበየነባቸው።

ግለሰቦቹ ግንቦት ወር ላይ በፕሬዚደንቱ ቤተ መንግሥት እና የፕሬዚደንት ፊሊክስ ታሺኬዲ አጋር መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት እንዲፈፀም በመምራት ነበር ክስ የቀረበባቸው።

መፈንቅለ መንግሥቱ እንዲፈፀም በመምራት የተጠረጠረው ትውልደ ኮንጎያዊው የሆነው አሜሪካዊው ክርስቲያን ማላንጋ በጥቃቱ ወቅት ከሌሎች 5 ግለሰቦች ጋር ተገድሏል።

ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ 51 ግለሰቦች በወታደራዊ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን ችሎቱም በብሔራዊ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ ጣቢያ ተላልፏል።

የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው አሜሪካውያን ግለሰቦች መካከል የማላንጋ ወንድ ልጅ ማርሴል ይገኝበታል።

ማርሴል ቀደም ብሎ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ላይ ካልተሳተፈ አባቱ እንደሚገድለው እንዳስፈራራው ተናግሯል።

የማርስል ጓደኛው ታይለር ቶምፕሰንም የሞት ፍርድ ተበይኖበታል።ሁለቱ ጓደኛማቾች በ20ያዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው።

ሦስተኛው አሜሪካዊ ቤንጃሚን ዛልማን ፖሉን ከክርስቲያን ማላንጋ ጋር በንግድ ሥራ ላይ የመሰማራት ፍላጎት ነበረው።

የቤልጂየም እና የኮንጎ ጥምር ዜግነት ያለው መጂን ጃኪስ ዎንዶም የሞት ፍርድ ተበይኖበታል።

ሂውማን ራይትስ ዎች ቀደም ብሎ መጂን ጃኪስን ‘በቀጠናው ፖለቲካ እና የጸጥታ ጉዳዮች ታዋቂ ተመራማሪ’ ሲል የገለጸው ሲሆን እርሱን ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ጋር የሚያገናኙ ማስረጃዎች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም ብሏል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ሞት የተበየነባቸው የእንግሊዝ እና የካናዳ ዜጎችም ትውልዳቸው ኮንጎ ነው። የእንግሊዝ ዜጋ የሆነው ዩሱፍ ኢዛንጊም በድርጊቱ ላይ የሚሳተፉ የተወሰኑ ሰዎችን በመመልመል ሲረዳ እንደነበር በፍርድ ቤቱ ተገልጿል።

ከ51ዱ ግለሰቦች 14ቱ ከጥቃቱ ጋር ግንኙነት የላቸውም ሲል ፍርድ ቤቱ ክሳቸውን አቋርጦ በነጻ አሰናብቷቸዋል።

የተፈረደባቸው ተከሳሾችም ይግባኝ ለመጠየቅ አምስት ቀናት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሞት ፍርድ ተፈፃሚ ሆኖ አያውቅም። የሞት ፍርድ የተበየነባቸው ግለሰቦች በምትኩ በእድሜ ልክ እስራት ነው የሚቀጡት።

መንግሥት የሞት ቅጣትን ያነሳው በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነበር።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምንም ዓይነት የሞት ቅጣት ተፈፅሞ አያውቅም።

የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የተፈፀመው በመዲናዋ ኪንሻሳ ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ነበር። የታጠቁ ሰዎች መጀመሪያ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ቪታል ካመርሄ ቤት ላይ ጥቃት የፈፀሙ ሲሆን ከዚያም ወደ ፕሬዚደንቱ መኖሪያ ቤት አቅንተዋል።

በወቅቱ የዓይን ምስክሮች እንደተናገሩት የጦሩን የደንብ ልብስ የለበሱ 20 ግለሰቦች ቤተመንግሥቱ ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ እና የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ነበር።

በኋላ ላይም የጦሩ ቃል አቀባይ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ሊፈፀም ታቅዶ የነበረውን መፈንቅለ መንግሥት ጦሩ ማክሸፉን አስታውቀዋል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ጥቃት ፈፃሚዎቹ ከኮንጎያዊ ፖለቲከኛ ማላንጋ ጋር የሚገናኘው ኒው ዛየር እንቅስቃሴ አባላት ናቸው።

ማላንጋ እጁን ለመስጠት ፈቃደኛ ስላልነበር በተከፈተበት ተኩስ መገደሉንም በወቅቱ የጦሩ ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ጀነራል ስይላቪን ኢኬንጌ ተናግረዋል።

መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተካሄደባቸው ፕሬዚደንት ታሺኬዲም ታኅሳስ ወር ላይ በተካሄደው አወዛጋቢ ምርጫ 78 በመቶ ድምጽ በማግኘት ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠዋል።

ዲሞክራቲክ ኮንጎ በማዕድን የበለፀገችና በርካታ ሕዝብ ያላት አገር ብትሆንም በአገሪቷ ውስጥ ባለው ግጭት፣ ሙስና እና ደካማ አስተዳደር ለበርካቶች ሕይወት ፈተና ሆኖባቸዋል።

ምንም እንኳን ፕሬዚደንቱ ግጭቶችን ለመፍታት አስቸኳይ ጊዜ ቢያውጁም፣ ከታጣቂዎች ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ቢፈፅሙም፣ የጎረቤት አገራት ወታደሮችን ቢያሰማሩም አብዛኛው የአገሪቷ ተፈጥሯዊ ኃብት የሚገኝበት ምስራቃዊ የአገሪቷ ክፍል በግጭት ውስጥ ነው የሚገኘው።