ፓፕ ፍራንሲስ

ከ 3 ሰአት በፊት

የካቶሊኩ ጳጳስ ፍራንሲስ ሁለቱም ለአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩ ሆነው የቀረቡት “ከሕይወት በተቃራኒ የቆሙ” መሆናቸውን ገልጸው፣መራጮች ድምጻቸውን በሕዳር ወር ሲሰጡ “የተሻለውን ክፉ” እንዲመርጡ ጥሪ አቀረቡ።

የሮማው ጳጳስ ስደተኞችን አለመቀበል፣ትራምፕን ማለታቸው ነው፤ “ከባድ” ሀጥያት ሲሆን ካማላ ሐሪስ የሚደግፉትን ጽንስን ማቋረጥ ደግሞ “የነፍስ ማጥፋት” ሲሉ ኮንነውታል።

ጳጳሱ በደቡብ ምዕራብ እስያ እያደረጉ የነበረውን ጉብኝት ሲያጠናቅቁ በሰጡት መግለጫ ላይ “ስደተኞችን እያካለበ የሚያስወጣውም ሆነ ሕጻናትን የሚገድለው ከሕይወት ተጻርረው የቆሙ ናቸው።” ብለዋል ።

ጳጳሱ በዚህ አስተያየታቸው ላይ ትራምፕን ሆነ ካማላ ሐሪስን በስም አልጠቀሱም።

በዓለም ላይ ከሚገኙት 1.4 ቢሊዮን ካቶሊኮች መካከል 52 ሚሊዮኑ አሜሪካውያን ናቸው።

ፖፕ ፍራንሲስ በአሜሪካ ለሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ምርጫውን አስመልክቶ ምን ምክር እንዳላቸው ተጠይቀው ሲመልሱ፣ አሜሪካዊ አለመሆናቸውን እና በምርጫው እንደማይሳተፉ ተናግረው፣ አሜሪካውያን ግን እንዲመርጡ እንደሚያበረታቱ ገልጸዋል።

“አለመምረጥ አስቀያሚ ነው።ጥሩ አይደለም።መምረጥ አለባችሁ።” ነው ያሉት።

“የተሻለውን ክፉ መምረጥ አለባችሁ።ማን ነው የተሻለው ክፉ፣ ሴትየዋ ወይስ ሰውዬው? አላውቅም።ሁሉም አስቦ እና አሰላስሎ መወሰን ይኖርበታል።” ብለዋል።

ጳጳሱ በካቶሊክ አስተምህሮ በጽኑ የሚወገዘውን ጽንስ ማቋረጥ በተደጋጋሚ በመተቸት ይታወቃሉ።

“በእናቱ ማህጸን ያለን ጨቅላ ሕይወት ማቋረጥ ነፍስ ማጥፋት ነው ምክንያቱም በእዚያ ሕይወት አለ” ብለዋል ፖፕ ፍራንሲስ።

ፓፕ ፍራንሲስ በፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይም ትችታቸውን ሲያቀርቡ የመጀመርያቸው አይደለም።

በ2016 ምርጫ ወቅት ትራምፕን “ክርስትያን አይደለም” ሲሉ ነበር የገለፁት።

ፖፑ ይህንን ሊሉ የቻሉበት ምክንያት ትራምፕ በሚጠቀሙት ፀረ ስደተኛ ቋንቋ የተነሳ ነው።

“ፍልሰተኞችን ማስወጣት፣ እንዳያድጉ፣ ሕይወት እንዳይኖራቸው ማድረግ አስቀያሚ ነገር ነው፤ ፍፁም ክፋት ነው” ነበር ያሉት አርብ እለት በመግለጫቸው ላይ።

ትራምፕ በተደጋጋሚ ሕገ ወጥ ስደተኞች ላይ ዘመቻ እንደሚከፍቱ እና እንደሚያስወጡ ይናገራሉ።

የሪፐብሊካኑ እጩ ትራምፕ አርብ እለት ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ ላይም ዳግም ከተመረጡ ሚሊዮኖች ስደተኞችን ከአገራቸው ጠራርገው እንደሚያስወጡ ቃል ገብተዋል።

ካማላ ሐሪስ በበኩላቸው በ2022 በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ጽንስን ማቋረጥ በአገር አቀፍ ደረጃ የነበረው ከለላ ከተቀለበሰ ወዲህ፣ ጽንስ ለማቋረጥ መብት በመላ አገሪቱ ከለላ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

የፖፕ ፍራንሲስ አስተያየት የተሰማው ትራምፕ እና ካማላ ለመጀመርያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተው የምርጫ ክርክር ካደረጉ በኋላ ነው።

ከምርጫ በፊት ሁለቱ ተፎካካሪዎች ዳግም ተገናኝተው ይከራከራሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ ፕዝዳንት ትራምፕ ግን ከካማላ ሐሪስ ጋር ድጋሚ ተገናኝቼ አልከራከርም ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል።