የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት እና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር

ከ 4 ሰአት በፊት

በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ የቆዩት አምባሳደር ማይክ ሐመር በህወሓት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በንግግር እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል።

ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ማይክ ሐመር በትናንትናው ዕለት በአሜሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተሟላ መልኩ መተግበር እንደሚያስፈልግ እና ለዚህም ሁለቱም አካላት ቁርጠኛ መሆናቸውን እንዳረጋገጡላቸው ተናግረዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛው የፕሪቶሪያ ስምምነት በዘላቂነት “በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ” ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ማይክ ሐመር የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ትግበራን በሚመለከት ከፌደራል መንግሥቱ፣ ከትግራይ ክልል እና ከአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም ኢጋድ ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውንም በዚሁ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

አምባሳደር ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ወቅትም ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታዬ አጽቀሥላሴ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋዊ የኤክስ ገጹ ላይ ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካው የአፍሪካ የቀረጥ ነጻ ንግድ ስምምነት እንድትመለስ አምባሳደር ታዬ መጠየቃቸውን ገልጿል።

አምባሳደር ታዬ እና የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛው ማይክ ሐመር ትናንት ባደረጉት ውይይት፣ በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነትና በሶማሊያ ይሠማራል ተብሎ በሚጠበቀው የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ዙሪያ ኢትዮጵያ ባላት ስጋት ላይ ጭምር እንደተወያዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ከ9 ወራት በፊት ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገር መሆኗን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ከሶማሊያ ጋር ያላት ግንኙነት ሻክሯል።

ይህንንም ተከትሎ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ስትወዛገብ የነበረችው ግብጽ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ተፈራርማለች።

የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ትብብር ስጋት ውስጥ የጣላት ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታውቃለች።ይህም የአፍሪካን ቀንድ ቀጠናን ስጋት ላይ መጣሉ ይታወቃል።

በአዲስ አበባ በትናንትናው ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ በህወሃት አመራሮች መካከል ያለው አለመግባባትን በተመለከተ ሲናገሩ “የክፍፍሉ ምክንያት ምንም ይሁን ምን በንግግር እንዲፈታ አበክረን እንጠይቃለን” ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ጄነራል ታደሰ ወረደ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ መፈታት እንደሚኖርበት መናገራቸው ይታወሳል።

ጄነራሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ እየወሰደ ያለው እርምጃ በክልሉ ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት ወደ ባሰ ደረጃ ሊያሸጋግረው እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው ገልጸው ነበር።

“ተባብሶ በመቀጥል እየፈነዳ ነው ያለው።ገንፍሎ የሚፈስ የፖለቲካ ቀውስ ነው የሚታየው።” ሲሉ ነበር ያስጠነቀቁት።

አምባሳደር ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ ከህወሓት ፕሬዝዳንት ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን ሁለቱም ለፕሪቶርያ ስምምነት ተፈጻሚነት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዳረጋገጡላቸው ተናግረዋል።

አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች። ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ትብብር አስኳል ይሄ ነው ያሉት ማይክ ሐመር፣ የትግራይ ተፈናቃዮችን የመመለስ ጅምር ስራ ቢኖርም አጥጋቢ አይደለም። ይህ መጠናከር አለበት ብለዋል።

“ የቀድሞ የትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለመበተንና ወደማህበረሰቡ ለመቀላቀል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አካላት ሙሉ ፈቃደኛ ናቸው። ተዋጊዎቹም ይሄን ይፈልጋሉ። ይህ ሂደት በፍጥነት መተግበር አለበት” ያሉት ልዩ መልዕክተኛው፣ “ታጣቂዎቹ ትጥቃቸውን ለመፍታት እና ወደ ዕለት ተዕለት ህይወታቸው መመለስ ይገባቸዋል እነሱም ይህንኑ ይፈልጋሉ” በማለት አሜሪካ ለዚህ የገንዘብ ድጋፍ እያደረገች መሆኗን ገልጸዋል።

“ ከትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎች 75 ሺህ የሚሆኑት ትጥቅ በማስፈታት ወደ ሕይወታቸው ለመመለስ የሚያስችል የገንዘብ አቅርቦት እንዳለ እናውቃለን” ካሉ በኋላ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ታጣቂዎቹን ትጥቅ ለማስፈታት እና መልሶ ለማቋቀወም ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደር ማይክ ሐመር “ከትግራይ እና ህወሓት ባለስልጣናት ጋር በነበረኝ ንግግር የፕሪቶርያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ያላቸውን ድጋፍ አረጋግጠውልኛል” ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለሰላም ሲባል የትግራይ ክልል እና የኤርትራ ባለሥልጣናት ግንኙነት እያደረጉ እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል።

ማይክ ሐመር ስለዚሁ በህወሓት እና በኤርትራ ባለስልጣናት መካከል ስላለ ንግግርም ተጠይቀው ሲያብራሩ አገራቸው “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዳግም ወደ ጦርነት ገብተው ማየት አንፈልግም። . . . ወደ ኢትዮጵያም ሆነ ወደ ኤርትራ ድንበር ጥሶ መግባት እንዲኖር አንፈልግም፤ በሁለቱም ወገን” ብለዋል።

ልዩ መልዕክተኛው አክለውም አስፈላጊ ከሆነም የአልጀርስ ሰምምነት ሙሉ ትግበራ ላይ አገራቸው ማገዝ እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

“በሁለቱ አገራት መካከል ብዥታ እና ግርታ እንዳይኖር [የአልጀርስ ስምምነት ትግበራ ላይ] ልናግዝ እንችላለን” ብለዋል።

በሁለቱ አካላት መካከል ንግግር ካለም በየትኛውም አካል የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያስቆም፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት መሻሻልን ያለመ፣ እንዲሁም በተለያዩ ግጭቶች እየታመሰ የሚገኘውን የአፍሪካ ቀንድ የሚያግዝ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

አምባሳደር ማይክ ሐመር በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በቀጠለው ውጊያ ምክንያት ወደ ክልሎቹ ለመሄድ “አስቸጋሪ” መሆኑን ገልጸው፣ ሆኖም አምባሳደር ማሲንጋ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ግጭቶቹን ለማቆም የሚያስችል ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር የሚደረገውን የሰላም ንግግር በተመለከተም ሲመልሱ በዳሬሰላም የተደረገው “የሰላም ድርድር ያለውጤት ተቋጨ ማለት የሰላም ጥረታችንን አቁመናል ማለት አይደለም” ካሉ በኋላ “ከኖርዌይ መንግሥት ጋር በመሆን ጥረታችንን ቀጥለናል” ብለዋል።