የኬንያው ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ እና የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ

ከ 6 ሰአት በፊት

ጀርመን ለ250 ሺህ ኬንያውያን ሠራተኞች በሯን ልትከፍት መሆኑ ተሰማ።

የኬንያ እና የጀርመን መንግሥት ባደረጉት የሥራ ስምምነት መሰረት በከፊል እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የሰለጠኑ 250 ሺህ ኬንያውያን ሠራተኞች ወደ ጀርመን ይሻገራሉ ተብሏል።

ኬንያውያን ሠራተኞችን በአውሮፓ ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤት በሆነችው ጀርመን ለመቅጠር በሚል አገሪቱ ያላትን የስደተኞች ሕግ ለማላላት ተስማማታለች።

ኬንያ በአገሯ ውስጥ ለወጣት ባለሙያዎች የሥራ እድል ለመፍጠር እንዲሁም በቂ ገቢ እንዲኖራቸው ማድረግ ሳትችል የቀረች ሲሆን በተቃራኒው ጀርመን ደግሞ ከፍተኛ የሠራተኛ ኃይል እጥረት አለባት።

አምስት የአውቶብስ ሹፌሮች በሰሜን ጀርመኗ ፍሌንስበርግ ፕሮጀክቱን ለመሞከር እንዲሄዱ መደረጋቸውም ተገልጿል።

የጀመርን መንግሥት ወደ አገሪቱ በሕገ ወጥ መልኩ የሚሰደዱ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ከያዛቸው ዋና ዋና መንገዶች አንዱ ከአገራት ጋር የሚያደርገው የስደተኞች ስምምነት ነው።

ይህ ስምምነት በጀርመን ያለ ሕጋዊ ፈቃድ እየኖሩ የሚገኙ ኬንያውያንም ተጠርዘው የሚመለሱበትን መንገድ ያቀላል ተብሏል።

በጀርመን መጤ ጠል የሆነው የፖለቲካ ፓርቲ፣ ኦልተርኔቲቭ ፎር ጀርመኒ (ኤኤፍዲ)፣ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ተከትሎ የሕገወጥ ስደተኞች ጉዳይ የአገሪቱ መንግሥት ከፍተኛ ራስ ምታት ሆኗል።

በበርሊን በተከታታይ ሥልጣን ላይ የነበሩ መንግሥታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች የመኖርያ ፈቃድ እንዲያገኝ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ጀርመን እኤአ በ2015-2016 በሶሪያ ያለውን ጦርነት ተከትሎ በተከሰተው ከፍተኛ የፍልሰተኞች ቁጥር የተነሳ 1 ሚሊዮን ሰዎችን የተቀበለች ሲሆን፣ የዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ ደግሞ 1.2 ሚሊዮን ዩክሬናውያንን አስተናግዳለች።

የሠራተኞች ስምምነቱ የተፈረመው በኬንያዊው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ እና በጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ መካከል ነው።

የበርሊን ባለሥልጣናት ኬንያውያን ሠራተኞች የተፈቀደላቸውን ሥራ ሲጀምሩ ጊዜያዊ የመኖርያ ፈቃድ ያመቻቻሉ ተብሏል።

እንደ ሁለቱ አገራት ስምምነት ከሆነ ኬንያውያን በጀርመን ለትምህርት ወይንም የሙያ ሥልጠና ለማግኘት የረዥም ጊዜ ቪዛ ማግኘት ይችላሉ።

“የረዥም ጊዜ ቪዛቸው በሚያበቃበት ወቅት ትምህርታቸውን ለመቀጠል የሚያስችል እስከ ሁለት ዓመት የሚቆይ ጊዜያዊ የመኖርያ ፈቃድ” እንደሚያገኙ ስምምነቱ ላይ ሰፍሯል።

አክሎም የጊዜያዊ የመኖርያ ፈቃዱ ኬንያውያን ወደ አገር ውስጥ የገቡበትን ዓላማ ካላሳኩ እና “በተወሰነ ጊዜ” የሚሳካ ከሆነ ሊራዘም የሚችልበት እድል አለ ይላል ስምምነቱ።

እንደ ሁለቱ አገራት ስምምነት ከሆነ ኬንያውያን የአይቲ ባለሙያዎች ምንም እንኳን መደበኛ የሆነ የብቃት ማረጋጋጫ ባይኖራቸውም ጀርመን ገብተው መስራት ይችላሉ።

ሁለቱም መንግሥታት የተማሩ ሠራተኞች፣ የሙያ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወይንም ደግሞ የዩኒቨርስቲ ዲግሪያቸው በሌላኛው አካል ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ ጀርመን ገብተው እንዲሰሩ ድጋፍ ያደርጋሉ።

ስምምነቱ ሁለቱ አገራት ዜጎቻቸውን መልሶ መቀበል ወይንም የመመለስ ስምምነትም ይዟል።

የሠራተኛ ፍልሰት፣ የጉልበት ብዝበዛ እና የሕገወጥ ሰዎች ዝውውርን ለመከላከልም የራሱን መመርያ አካትቷል።

አፍሪካውያን የሕክምና ባለሙያዎች

ሐሙስ ዕለት አምስት ኬንያውያን ሹፌሮች ፍሌንስበርግ መድረሳቸውን ተከትሎ የጀርመን ትራንስፖርት ሚኒስትር ክላውስ ሩሄ ማድሰን፣ “ጀርመን ጠንክረው የሚሰሩ እጆች እና ብሩህ አእምሮ ትፈልጋለች” ብለዋል።

ሹፌሮቹ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር አክቲቭ በተሰኘ ኩባንያ የሰለጠኑ ናቸው።

ከዚህ በመቀጠል ዶክተሮች፣ ነርሶችና መምህራን በዚህ ፕሮግራም ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የዓለምአቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ይህ ስምምነት ኬንያውያን ሠራተኞች በጀርመን ጥሩ የሚባል ሥራ እንዲያገኙ እድሎችን እንደሚጨምር በጀርመንም ያለውን የሠራተኞች እጥረትም እንደሚቀርፍ ያለውን ተስፋ ገልጿል።

የዓለም አቀፉ ድርጅት በመግለጫው “የኬንያውያን ስደተኛ ሠራተኞችን መብት እና ደኅንነት ይከላከላል፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ሥርዓት ያለው እና ውጤታማ የሆነ የስደተኛ ሥርዓት ይፈጥራል” ብሏል።

እንደ ዶክተር እና ነርሶች ያሉ የተማሩ ሰዎችን ወደ ሌላ አገር ማፍለስ አገሪቱ በተማረ ሰው ኃይል ድርቅ እንድትመታ ያደርጋል፣የአገሪቱ የሕክምና ተቋማትም በባለሙያዎች እጥረት እየተቸገሩ ነው ሲሉ ቅሬታ ያቀረቡም አሉ።

ጠበቃ እና ፖለቲከኛ የሆነው ኢኩሩ ኡኮት ለቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም “ በአገራችን ወጪ ሌላ አገርን ልናገለግል መሆኑ በጣም ያሳዝናል” ብሏል።

ከፍተኛ የውጪ ጉዳይ ባለሙያ የሆነችው ሮስሊን ንጆጉ ግን ኬንያ ለዓለም አቀፉ የሠራተኞች ገበያ ፍላጎት ምላሽ እየሰጠች ነው ስትል ትገልጻለች።

“እዚህ ኬንያ ውስጥ በርካታ ወጣት ዜጋ አለን። በየዓመቱ ደግሞ ሚሊዮኖች የአገር ውስጥ የሠራተኞች ገበያን ይቀላቀላሉ። በአገር ውስጥ የሥራ እድል ለመፍጠር ጊዜ እና ሀብት ይጠይቃል” ስትልም ታክላለች።