ሔለን ተስፋዬ

September 15, 2024

የዘረመል ቴክኖሎጂ መስፋፋቱና በጤና ላይ የሚያደርሰው አደጋ መበራከቱ፣ ለሆርቲካልቸር ዘርፍ ልማት ሥጋት መሆኑን፣ የግብርና ሚኒስቴር ያዘጋጀው የሆርቲካልቸር ልማት ግብይት ስትራቴጂ አመላከተ፡፡

ስትራቴጂው የተዘጋጀው ከ2016 እስከ 2025 ዓ.ም. ለመተግበር ሲሆን፣ የሆርቲካልቸር ዘርፍ እንዳያድግ ሥጋት ይሆናሉ ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል የዘረመል ቴክኖሎጂ መስፋፋት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዓለም አቀፉ የኃይል መቃወስ ጋር ተያይዞ የዘረመል ምርምርና ማምረቻዎች ወጪ እየናረ መምጣት፣ በዘርፉ የሚገኙ ተዋንያንን እየተፈታተነ መሆኑ በስትራቴጂው ተመላክቷል፡፡

በሆርቲካልቸር ዘርፍ የዓለም አቀፍ የጥራት መሥፈርት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጠናከረ መሆኑን፣ አሁን ባለው አቅም የኢትዮጵያ ምርት ከገበያ ሊወጣ የሚችልበት ደረጃ መድረሱ ዘርፉን ሥጋት ውስጥ ከቶታል ይላል ስትራቴጂው፡፡

ወደ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ሩቅ ምሥራቅና ጎረቤት አገሮች የሚላኩ አትክልት፣ ፍራፍሬና አበባ ምርቶች 4.9 በመቶ የገቢ ድርሻ እንዳላቸው በስትራቴጂው ተገልጿል፡፡

የስትራቴጂው ዓላማ ለሚከሰቱ ሥጋቶች ምላሽ የመስጠት ሥርዓት መዘርጋት አንዱ ሲሆን፣ ለዚህም የገበያ ሥጋቶችን የመተንበይ አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ለሆርቲካልቸር ምርቶች የወጪ ገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት ሊከሰቱ የሚችሉ የገበያ ሥጋቶችን ለመቀነስ ሥርዓት መዘርጋት፣ ከመዳረሻ አገሮች ጋር የሚኖር የቢዝነስ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማሻሻል የሚረዱ ሥራዎች እንደሚከናወኑ በስትራቴጂው ተቀምጧል፡፡

በሆርቲካልቸር ዘርፍ በወጪ ንግድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ ተገልጿል፡፡

ወደ ውጭ ከተላኩት የሆርቲካልቸር ምርቶች በ2015 ዓ.ም. በአጠቃላይ 686.6 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን፣ ይህም በ2005 ዓ.ም. ከነበረው 26 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር የ660.6 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ እንዳለው ተመላክቷል፡፡

በ2016 የበጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት የወጪ ንግድ የአበባ ኤክስፖርት ገቢ 502.26 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን፣ ይሁን እንጂ የአትክልት፣ የፍራፍሬና የሥራሥሮች ድርሻ 67.39 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ስትራቴጂው ያትታል፡፡

በሰፋፊ እርሻዎች የሚመረቱት አብዛኞቹ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶች ለአገር ውስጥ ትልልቅ ከተሞች የሚቀርቡ መሆናቸውንና ወደ ሌሎች አገሮች በተለይም አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅና ጎረቤት የአፍሪካ አገሮች ኤክስፖርት እንደሚደረጉ ተጠቁሟል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2004/2005 የአትክልት፣ የፍራፍሬና የሥራሥር ምርቶች ኤክስፖርት ገቢ ከነበረበት 15.95 ሚሊዮን ዶላር በ2022/23 ወደ 117.6 ሚሊዮን ዶላር እንዳደገ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በአንፃሩ እነዚህ ምርቶች በጥሬና ተቀነባብረው ከውጭ የሚገቡ ሲሆን፣ ለዚህ የሚወጣው ወጪም ከፍተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡