ዳዊት ታዬ

September 15, 2024

የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ

ለመንግሥት ሠራተኞች የተደረገውን የደመወዝ ጭማሪ በአዎንታዊነት የሚቀበሉት ቢሆንም፣ በግል ሠራተኞችና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች መነሻ የደመወዝ ወለል በአስቸኳይ መቀመጥ እንዳለበት፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

ኮንፌዴሬሽኑ ሰሞኑን ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ይህንኑ ጉዳይ አፅንኦት ሰጥቶ ውሳኔ ያሳለፈበት ሲሆን፣ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ጫናዎችን ለመቀነስ የደመወዝ ወለል መነሻ የደመወዝ ወለል ሊቀመጥ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ እንደገለጹት፣ መነሻ የደመወዝ ወለል ማስተካከያውን በማድረግ፣ ከዚህ ቀደም በተገባው ቃል መሠረት ተፈጻሚ እንዲሆን ጥያቄያቸውን በድጋሚ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሰሞኑ ጠቅላላ ጉባዔም ኮንፌዴሬሽኑ በቀዳሚነት እንዲከታተለው የጉባዔው አባላት ስምምነት ላይ የደረሱ ስለመሆኑ፣ ከአቶ ካሳሁን ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ሲቀርብ የነበረው ‹‹የሥራ ግብር ይቀነስ›› የሚለው ጥያቄ፣ በተለይ አሁን ላይ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ይህ ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ የሚሹ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የጉዳዩ አንገብጋቢነትን በመረዳት በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ውሳኔ ከማሳለፉ ባሻገር፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት ‹‹የሥራ ግብር እንዲቀነስ›› የጠየቁበትን ደብዳቤ በድጋሚ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

በደመወዝ ግብር ጉዳይ አሉ ያሏቸውን ችግሮች በተደጋጋሚ ሲያስረዱ እንደነበር፣ ይህንን ጫና ለመቀነስ ለጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹መንግሥት ለግል ተቋማት ከካዝነው አውጥቶ ለግል ተቋማት ጭማሪ ሊሰጥ አይችልም፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ እንደሌሎች አገሮች ወይም በአሠሪና በሠራተኛ አዋጅ መሠረት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መወሰን ግን የሚችል በመሆኑ፣ በዚሁ መሠረት በአስቸኳይ ውሳኔውን ሊያሳልፍ ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይ የገንዘብ የመግዛት አቅም በቀነሰበት በዚህ ወቅት፣ የሥራ ግብርም መቀነስ ይኖርበታል፡፡ ‹‹የሥራ ግብር ይቀነሳል ማለት የገንዘብ የመግዛት አቅም መቀነንስ ባገናዘበ ሁኔታ ሊሆን ይገባል፡፡

እስካሁን ባለው አሠራር እስከ 600 ብር ያለው ደመወዝ ብቻ ከግብር ነፃ በመሆኑ፣ አሁኑ አንድ ሺሕ ብርና ከሁለት ሺሕ ብር የሚከፈው ደመወዝተኛ ግብር ተቆርጦበት በእጁ ላይ የሚቀረው ትንሽ ቀዳዳውን እንኳን የሚደፍንለት ባለመሆኑ፣ መንግሥት በዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጉዳይ ላይ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

እንደ ዓለም አቀፍ ባሉ ተቋማት ስታንዳርድ መሠረት ደሃ የሚባለው ከ57 ዶላር በታች የሚያገኝ ነው ይላሉ፡፡ 57 ዶላር ማለት ደግሞ በአሁኑ የምንዛሪ ዋጋ ስድስት ሺሕ ብር አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ግብር እየተቆረጠ ያለው ከዚህ ገቢ በታች ካለው ደመወዝተኛ ጭምር በመሆኑ ጉዳዩ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ አመላካች እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፣ የግል ተቋማት ውስጥ የደመወዝ ምጣኔው በአብዛኛው ከ2,000 እስከ 8000 ብር ነው፡፡ በአብዛኛው በኢንዱስትሪዎችና በማኑፋክቸሪዎች አካባቢ የሚከፈለው የደመወዝ መጠን ከሆነ ይህንን ደመወዝ ከሚያገኘው ሰው የደሃ ደሃ ነው፡፡ አብዛኛው በዓለም አቀፍ ደረጃ ደሃ ያገኛል ከሚባለው መሥፈርት በታች የሚያገኝ ደመወዝተኛ በመሆኑ ከደሃ ደሃ ግብር ሊቆረጥ አይገባም የሚል አቋም እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹ዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ከፍ ይበል ብለን አጠንክረን የምንጠይቀው ግብር ላለመክፈል እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ የገንዘብ አቅም በተዳከመ ቁጥር ይህንን ማስተካከል የተለመደ አሠራር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከግብር ነፃ የነበረው እስከ 150 ብር ድረስ እንደነበር በመጥቀስ፣ ከዚያ በኋላ 400 ብር፣ ከዚያም 600 ብር እንዲሆን የተደረገው የገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ በሚደረግበት ጊዜ ጥያቄ በማቅረብ የተሻሻለ ነበርም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ጋር ተያይዞ ያለው የኑሮ ሁኔታ ግብር የሚቆረጥበት ዝቅተኛው የደመወዝ መጠን ከስድስት መቶ ብር መብለጥ አለበት፡፡

በሰሞኑ የኢሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤትም በቀዳሚነት ውይይት እንዲደረግበት የተደረጉት እነዚህ ሁለት አጀንዳዎች እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

ጠቅላይ ምክር ቤቱ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ከዚህ ቀደም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቦ እንደሚስተካከል ቃል የገቡ በመሆኑ፣ ቃላቸውን እንዲፈጽሙ የኢሠማኮ አመራር ጥያቄውን እንዲገፋ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

አሁን ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር የእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች አለመመለስ ሠራተኛው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ጥያቄውን ለመመለስ ከዚህ የተሻለ ጊዜ እንደሌለም አሳስበዋል፡፡

ጥያቄዎችን ለመመለስ ቃል የተገባው ያሉትን ችግሮች በመረዳት በመሆኑ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡን ቃል እንዲፈጽሙልን ኢሠማኮ ጥያቄውን ሊገፋ ይገባልም ብለዋል፡፡

የግል ተቋማትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ደመወዝን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ አሁን ዋነኛ ጥያቄያችን ደመወዝ ይጨመር የሚል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዋነኛ ጥያቄያችን መነሻ ‹‹የደመወዝ ወለል ይስተካከል ነው›› አንድ ኩባንያ አንድ ሠራተኛ ሲቀጥር ሠራተኛው ቢያንስ በልቶ ለማደር የሚያስችለው ክፍያ ሊከፈለው ይገባል፡፡ መነሻ የደመወዝ ወለል ይሻሻል የምንለውም አንድ ሠራተኛ ቢያንስ በልቶ ለማደር የሚያስችለው እንዲሆን ያደርገዋል የሚል እምነት ስላለ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በተገባው ቃል መሠረት ተፈጻሚ ከሆነ ደግሞ የግል ሠራተኞችና የመንግሥት ልማት ድርቶችም ደመወዝ እንዲሻሻል የሚያግዝ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ስለዚህ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ማሻሻያው ጊዜ ሊሰጥ የማይገባ፣ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ በመሆኑ፣ የዜጎችን ሕይወት ለማዳን መንግሥት በእጁ የሚገኘውን ሥልጣን ሊጠቀምበት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የተገባው ቃል ሊተገበር እንደሚገባው ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡