በጋዜጣዉ ሪፓርተር

September 15, 2024

የግብርና ማዳበሪያ በአገር ውስጥ ለማምረት መሠረታዊ ግብዓት የሆነውን ፖታሽ ለማውጣት ፈቃድ ወስደው ያለ ሥራ ለረዥም ጊዜ የተቀመጡ ኩባንያዎች በዚህ ዓመት (2017) ሥራ ካልጀመሩ፣ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው መንግሥት አስጠነቀቀ፡፡

በአፋር ክልል የፖታሽ ማዕድን ለማምረት ፈቃድ ለወሰዱ ኩባንያዎች፣ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉን የማዕድን ሚኒስቴር በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

ከእነዚህ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው ትልልቅ የፖታሽ አልሚ ባለፈቃዶች ውስጥ ሰርከም ሚኒራልስ፣ ያራ ዳሎልና ኢትዮ ፖታሽ የሚባሉ ይገኙበታል፡፡ ኩባንያዎቹ ፈቃድ ከወሰዱ ሰባት ዓመታት እንደሆናቸው ተገልጿል፡፡

ሰርከም በአፋር ክልል ዳሎል አካባቢ በወሰደው 365 ካሬ ኪሎ ሜትር ያለው የፖታሽ ዕምቅ ሀብት 14 ቢሊዮን ቶን ነው፡፡

በተመሳሳይ ያራ በአፋር ዳሎል የወሰደው 54 ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት 11 ቢሊዮን ቶን የፖታሽ ዕምቅ ሀብት መኖሩን ሚኒስቴሩ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ዩናይትድ ፖታሽ የተባለ ኩባንያ በዳሎል 320.5 ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት የወሰደ ሲሆን፣ ሥራ እንዳልጀመረ ታውቋል፡፡ ይህ ቦታ በፊት ለዓመታት አላና ፖታሽ በሚባል ኩባንያ በክርክር ተይዞ ነበር፡፡

ከኩባንያዎቹ ችግሮች በተጨማሪ የመንግሥትን ትኩረት የሚፈልጉ ተግዳሮቶች መኖራቸው ተገልጾ ፀጥታ፣ የፋይናንስ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና  ከደናክል ወደብ ጋር የሚያገናኙ ጥርጊያ መንገዶች አለመጠናቀቅም እንደ ችግር ተጠቅሰዋል፡፡

ፖታሽን ከተፈጥሮ ጋዝ ተረፈ ምርት ጋር በማቀናበር የግብርና ማዳበሪያ በአገር ውስጥ ማምረት ለመጀመር ጥናት እየተደረገ እንደሆነ በማዕድን ሚኒስቴር ሪፖርት ተመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የምታወጣ ሲሆን፣ በተለይ በቅርቡ ከተደረገው የምንዛሪ ለውጥ በኋላ መንግሥት በብር የሚያደርገውን ድጎማ ከፍ እንዲል ማድረጉ ይታወሳል፡፡