ዮሐንስ አንበርብር

September 15, 2024

የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሐመድ አሊ ዩሱፍ

 ኢትዮጵያ ታጁራ ወደብን በጋራ እያስተዳደረች እንድትጠቀምበት እንጂ ጠቅልላ እንድትወስደው ወይም እንድትገዛው የጂቡቲ መንግሥት ሐሳብ አለማቅረቡን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጹ።

የጂቡቲ መንግሥት በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ በማሰብ፣ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን መቶ በመቶ በማስተዳደር እንድትጠቀምበት ምክረ ሐሳብ ማቅረቡን ለቢቢሲ የተናገሩት የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሐመድ አሊ ዩሱፍ፣ ይህ ንግግራቸው በጂቡቲ ማኅበረሰብ ዘንድ ብዥታ መፍጠሩን ተከትሎ፣ ባለፈው ሰኞ ቀን በአገሪቱ ቴሌቪዥን ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተውበታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያም፣ ‹‹ታጁራ ወደብን በጋራ ለማስተዳደር እንጂ፣ ለኢትዮጵያ አሳልፈን አንሰጥም፤›› ያሉ ሲሆን፣ ይህንምም የሚያደርጉት የጂቡቲን ጥቅም ለማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

አክለውም፣ ‹‹ታጁራም ሆነ ሌሎች በጂቡቲ የሚገኙ ወደቦች የአገሪቱ ብሔራዊ ሀብትና ንብረቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም አንዳቸውንም ለሌላ ወገን አሳልፈን የምንሰጥበት ምክንያት የለም፣ አይኖርምም፤›› ብለዋል።

ነገር ግን እነዚህን ሀብትና ንብረቶች ምሉዕ አቅም አሟጦ በመጠቀም ለጂቡቲ ተገቢውን ጥቅም እንዲያስገኙ ለማድረግ ብሔራዊ የንግድ ስትራቴጂ መቀረፁን ተናግረዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ከታጁራ ወደብ የሚገባንን ጥቅም እያገኘን አይደለም። በሁለት ወራት ውስጥ አንድ መርከብ ብቻ ነው እያስተናገደ የሚገኘው። የጂቡቲ መንግሥት ይህንን ወደብ ለመገንባት 60 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል። ከታጁራ ወደብ እስከ ባሎህ ግዛት ድረስ ያለውን መንገድ ለመገንባት ደግሞ 110 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል። በታጁራ ወደብ ሠራተኞች ደመወዝ እየተከፈለ ያለው ከዶላሬ ወደብ ከሚገኝ ገቢ ነው። ይህ መሆኑ ትክክል ነው ትላላችሁ? አይደለም፤›› ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኡመር ጉሌ የታጁራ ወደብ የሚጠበቅበትን አገልግሎት በመስጠት ገቢ እንዲያስገኝና ትርፋማ እንዲሆን አቅጣጫ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበው ሐሳብ የታጁራ ወደብን እያስተዳደረ እንዲጠቀምበት እንጂ፣ ጠቅልሎ እንዲወስደው ወይም ለኢትዮጵያ ለመሸጥ አይደለም ብለዋል።

ይህንን ምክረ ሐሳብ ኢትዮጵያ ብትቀበል ጂቡቲ ተጠቃሚ መሆኗ እንደማያጠራጥር፣ ለዚህም ኢትዮጵያና ጂቡቲ በጋራ ገንብተው እየተጠቀሙበት ያለው የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መሠረተ ልማት ህያው ምስክር መሆኑን በምሳሌነት በማንሳት አስረድተዋል።

‹‹ጂቡቲ የወደብ አማራጮቿን በማስፋት ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የወደብ አገልግሎት የማታሳድግ ከሆነ፣ ከኢትዮጵያ የምናገኘውን ጥቅም ነገ ከእጃችን ይወጣል፣ ነገ አሰብ ይከፈታል፣ ነገ ኢትዮጵያ ወደ ሶማሌላንድ ትሄዳለች። ስለዚህ የኢትዮጵያን የወደብ አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት መጣር አለብን፤›› ሲሉ ሚኒስትር ሞሐመድ አሉ ዩሱፍ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ወጪዎችን ያካተቱ በመሆናቸው፣ ዋጋቸው ውድ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፣ ጂቡቲ ለኢትዮጵያ የምታቀርበውን የወደብ አገልግሎት አማራጮች በማስፋት የኢትዮጵያን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ወጪዎች በማቅለል ዘላቂነት ያለውን የንግድ ትብብርን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በዚህ ዕሳቤ ማየት ከተቻለ የታጁራ ወደብ በአሁኑ ወቅት ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ ከሚገኘው የጂቡቲ ወደብ (ዶላሬ ወደብ) በተሻለ ሁኔታ ለሦስት የኢትዮጵያ ክልሎች (ማለትም ለትግራይ፣ ለአማራና አፋር ክልሎች) ቅርብና አዋጭ በመሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የታጁራ ወደብ በዚህ መልኩ ለኢትዮጵያ የተሟላ የወደብ አገልግሎት በመስጠት ገቢ ማመንጨት ካልቻለ፣ ወደቡን ለመገንባት የተወሰደውን ብድር ዕዳ ለትውልድ የሚሻገር መሆኑን አስረድተዋል።

ከታጁራ ወደብ በተጨማሪ የዴመርጁግ ወደብን በማልማት ኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶችን በዚህ ወደብ በማስገባት በቀጥታ በባቡር ማጓጓዝ እንድትችል የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ መያዙንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን በጋራ በማስተዳደር በብቸኝነት እንደትጠቀምበት ከጂቡቲ ለቀረበው ሐሳብ የሰጠችውን ምላሽ ለማወቅ የማሪታይም አገልግሎት ባለሥልጣንን ብንጠይቅም ጉዳዩ በመንግሥት ደረጃ ወይም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የተያዘ መሆኑን አሳውቋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ጉዳዩ ውሳኔ ሲያገኝ ወደፊት መረጃ እንደሚሰጥበት ገልጿል።