ዜና እነ ዮሐንስ ዳንኤል አውሮፕላን በቁጥጥር ሥር በማዋልና አለመታዘዝ ወንጀል ተከሰሱ

ታምሩ ጽጌ

ቀን: September 15, 2024

በቅጽን ስሙ ጆን ዳንኤል በመባል፣ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ሥራዎቹ የሚታወቀው ዮሐንስ ዳንኤልና ሌሎች አምስት ግለሰቦች፣ አውሮፕላንን ያላግባብ መያዝ (በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ የመንግሥት ሠራተኛ ኦፌሴላዊ ግዴታ እንዳይፈጸም መቃወም፣ አለመታዘዝና መልካም ስምን የሚያጎድፍ ተንቀሳቃሽ ምሥል በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካይነት ማሠራጨት ወንጀሎች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሾቹ የተጠቀሱት ክሶች የተመሠረቱባቸው፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ)፣ 35፣ 507 እና 440 (1ሀ) ድንጋጌዎችን ተላልፈው በመገኘታቸው መሆኑን፣ ከሳሽ የፍትሕ ሚኒስቴር ዓቃቤ ሕግ፣ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

እነ ዮሐንስ ዳንኤል አውሮፕላን በቁጥጥር ሥር በማዋልና አለመታዘዝ ወንጀል ተከሰሱ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት ዮሐንስ ዳንኤል፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን፣ ኤልያስ ድሪባ፣ እሌኒ ክንፈና ይዲዲያ ነፃነት የሚባሉ ሲሆኑ፣ የተጠቀሱትን የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች በመተላለፍ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በግምት ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት ላይ መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡

ተከሳሾቹ ድርጊቱን የፈጸሙት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 በሚገኘው በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግቢ ውስጥ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ለመጓዝ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሆነውና የበረራ ቁጥሩ ኢቲ-190 ቦምባርዴር ኪው 400 በሆነው የመንገደኞች አውሮፕላን ላይ መሆኑን ክሱ ያብራራል፡፡

አውሮፕላኑ ለበረራ ዝግጁ የነበረ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ክፍል፣ መቀሌ ያለው የአየር ሁኔታ ለበረራ አዳጋች እንደሆነና አውሮፕላን ለማሳረፍ ስለማይቻል፣ መብረር እንደሌለበት ለዋና አብራሪው በመነገሩና ዋና አብራሪውም ለተሳፋሪዎች ያንኑ ሲያሳውቁ፣ ተከሳሾች ችግሩን መፍጠራቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ተሳፋሪዎችን ከአደጋ ለመታደግ በረራው ተሠርዞ መንገደኞች ከአውሮፕላን እንዲወርዱ ሲጠየቁ (ሲነገራቸው)፣ ‹‹በረራው በግድ መደረግ አለበት፣ አውሮፕላኑን ይከስከስ፣ አንወርድም›› በማለት ሌሎች ተሳፋሪዎችም እንዳይወርዱ በመከልከልና በማሳደም ችግር መፍጠራቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ተከሳሾቹ ከደኅንነት ቅድመ ጥንቃቄ አንፃር አውሮፕላን ለማስነሳትና ለማሳረፍ ብቻ በተፈቀደ ቦታ ላይ ቪዲዮ በመቅረፅ፣ በተለይ ጆን ዳንኤል በቲክቶክ ማኅበራዊ ሚዲያ ሁነቱን በቀጥታ ሥርጭት በማስተላለፍ፣ ከሁለት ሰዓታት በላይ አውሮፕላኑን ተቆጣጥረው እንዳይንቀሳቀስ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

ተከሳሾቹ ለአውሮፕላኑና ለተሳፋሪዎች ደኅንነት አሥጊ መሆኑ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የበረራ ደኅንነት ባለሙያዎች ተነግሯቸው እንዲወርዱ ሲጠየቁ፣ ለመተባበር ፈቃደኛ ባለመሆንና ‹‹አንወርድም ይከስከስ›› በማለት የመንግሥት ሠራተኞችን ኦፊሴላዊ የሥራ ግዴታቸውን እንዳይፈጽሙ መቃወማቸውንና አልታዘዝም ማለታቸውንም ክሱ ያብራራል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአገሪቱ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች አንዱ መሆኑን የጠቀሰው ዓቃቤ ሕግ፣ መልካም ስሙንና ዝናውን ለማጉደፍ ተከሳሾች በተንቀሳቃሽ ምሥል በመቅረፅ፣ ቲክቶክ በተባለ ማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት በቀጥታ ለሕዝብ በማስተላለፍና ስሙ ‹‹ዮኒ ማኛ›› በመባል የሚጠራው ግለሰብ በቀጥታ ሥርጭት እንዲገባ በመጋበዝ፣ ‹‹አየር መንገዱ ደንበኞችን ለማጉላላት ያደረገው ነው፣ ጉዱን በአደባባይ እናወጣለን፤›› በማለት የአየር መንገዱን ስም የሚያጎድፍ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልጿል፡፡ በአጠቃላይ ጆን ዳንኤል አየር መንገዱ የሰው ሕይወት ለመጠበቅና ከአደጋ ለመከላከል የሰረዘውን በረራ፣ በአየር ሁኔታ እንዳልተሰረዘ፣ በተቃራኒው መንገደኞችን ለማጉላላት የፈጠረው ሰበብ እንደሆነና በሠራተኞች አማካይነት እንደታገተ በማስመሰል፣ በቲክቶክ ማኅበራዊ ድረ ገጽ በቀጥታ በማስተላለፍ የአየር  መንገዱን መልካም ስም የሚያጎድፍ ተንቀሳቃሽ ምሥል በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካይነት ማሠራጨቱን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ ክሱን በችሎት ካሰማ በኋላ የተከሾች ጠበቆች፣ ደንበኞቻቸው የተመሠረተባቸው ክስ ዋስትና እንደማያስከለክል ተናግረው፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡  

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ክሱ ዋስትና እንደማይከለክል አረጋግጦ፣ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 67 ድንጋጌ መሠረት፣ የዋስትና መብታቸው እንደማይፈቀድና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡

የወንጀል ሕግ አንቀጽ 507 ድንጋጌ ከ15 እስከ 25 ዓመታት ሊያስቀጣ እንደሚችልና እንደሚደነግግና ተከሳሾችም በዚህ አንቀጽ በአንደኛ ክስ ስለተከሰሱ ዋስትና እንዳይፈቀድላቸው ተከራክሯል፡፡

የተከሳሾች ጠበቆች ባቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ፣ ተደራራቢ ክስ ለዋስትና መቃወሚያ እንደ ምክንያት መቅረብ እንደሌለበት፣ ዓቃቤ ሕግ የጠቀሳቸው መከራከሪዎችና ለዋስትና ማስከልከያነት የጠቀሳቸው የክስ መዝገቦች ከተያዘው ክስ ጋር እንደማይገናኙ በመከራከር ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ኤልያስ ድሪባ የተባለው ተከሳሽ ቀደም ባሉት ጊዜያት ፈጽሟቸዋል የተባሉ የወንጀል ጉዳዮች፣ ከተያዘው ክስ ጋር እንደማይገናኝና ከጥፋተኝነት ፍርድ በፊት ሊጠቀስ እንደማይገባም በማስረዳት የተከሳሾች ጠበቆች ተከራክረዋል፡፡

ችሎቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በዋስትና ክርክሩ ላይ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡